ጀርመንና ውኅደቷ፣ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 02.10.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

ጀርመንና ውኅደቷ፣

ከ2ኛው የዓለም ጮርነት ፍጻሜ በኋላ በምዕራባውያን ተጓዳኝ መንግሥታትና በሶቭየት ኅብረት ከ 2 ተከፍላ 44 ዓመታት አንድነቷን አጥታ የነበረችው ጀርመን ፣ በቀዝቃዛው ጦርነት ፍጻሜ ላይ፣ እ ጎ አ በ 1989 ዓ ም፣

default

የጀርመን ሰንደቅ ዓላማ፣ በርሊን ውስጥ፣ከ ምክር ቤቱ ህንጻ ፊት-ለፊት ሲውለበለብ፣

ምዕራቡንና ምሥራቁን ከፍሎት የነበረው የብረትና ግንብ አጥር ፈርሶ፣ አንድነቷ ተመልሶ ለመዋኻድ መብቃቷ የታወቀ ነው። ነገ ለ 20ኛ ጊዜ የሚከበረው ብሔራዊ የአንድነት ቀን የታወጀው፣ ለውኅደቱ መንገድ የጠረጉ ድራማ መሰል አያሌ ጉዳዮች፣ እ ጎ አ ከመስከረም 1989 ዓ ም አንስቶ አንድ ዓመት ያህል ከተከናወኑ በኋላ ነው።---

የጀርመን ብሔራዊ የአንድነት ቀን እ ጎ አ ጥቅምት 3 ቀን ነው በአገሪቱ በመላ ተከብሮ የሚውለው። 20ኛው የዘንድሮው የአንድነት በዓል፣ በነገው ዕለት ተከብሮ የሚውል ሲሆን፣ ለይፋው የአከባበር ሥርዓት ዘንድሮ ተረኛ አስተናጋጅ፣ ከ 16 ቱ ፌደራል ክፍልተ- ሀገር መካከል በምዕራባዊው ጫፍ፣ ፈረንሳይና ጀርመን አዋሳኝ ላይ የምትገኘው ዛርላንድ ናት። የዝችው ንዑስ ክፍለ-ሀገር ርእሰ-ከተማ Saarbrücken የማስተናገድ ዕድል ሲያጋጥማት እ ጎ አ ከ 1993 ዓ ም ወዲህ የነገው 2ኛዋ ጊዜዋ ይሆናል ማለት ነው። የመጀመሪያው የጀርመን ብሔራዊ የአንድነት በዓል፣ ይፋ ሥነ ሥርዓት አ ጎ አ ጥቅምት 3 ቀን 1990 ዓ ም በመዲናይቱ በበርሊን ፣ ከዚያም በዓመቱ በ 2ኛይቱ የአገሪቱ ግዙፍ የወደብ ከተማ ፣ በሐምበርግ መከናወኑ ይታወሳል። በነገው ይፋ የአከባበር ሥርዓት ከዚህ ቀደም ይደረግ እንደነበረው ሁሉ፣ የአገሪቱ ከፍተኛ የአመራር አባላት፣ ፕሬዚዳንት ሆርስት ከዐለርና መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል እንዲሁም የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤትና ፣ የፌደራል ክፍላተ-ሀገር መማክርት አባላት ይሳተፋሉ።

ምዕራብና ምሥራቅ ጀርመን ከመዋኻዳቸው በፊት በጀርመን ፌደራል ሪፓብሊክ(ምዕራብ ጀርመን)የአንድነት ቀን የሚከበረው እ ጎ አ ሰኔ 17 ቀን ነበረ። እርሱም ፣ የምሥራቅ ጀርመን ሠርቶ አደሮች በሥርዓቱ ላይ አምጸው የተነሱበትንና ይኸው መነሣሣታቸው በወታደራዊ ኃይል የከሸፈበትን ዕለት ነበረ የሚያዘክረው።

የጀርመን የውኅደት ቀን ሆኖ መከበር የነበረበት ዕለት፣ እ ጎ አ ኅዳር 9 ቀን ነበረ፣ በርሊንን ከሁለት ከፍሏት የነበረው የግንብ አጥር የተገረሰሰው በ 1989 ዓ ም፣ በተጠቀሰው ዕለት ነበረ። የአንደኛው የዓለም ጦርነት እንደተደመደመ፣ የመጀመሪያው የጀርመን ትክክለኛ ሪፓብሊክ የታወጀውም እ ጎ አ ኅዳር 9 ቀን 1918 ዓ ም ነበረ። የሂትለር የመጀመሪያው የመፈንቅለ-መንግሥት ሙከራ፣ እ ጎ አ በ 1923 ዓ ም የከሸፈውም፣ ኅዳር 9 ቀን ነበረ። ይሁን እንጂ እ ጎ አ በ1938 ዓ ም፤ የጀርመን አይሁዶች ጭፍጨፋ የተጀመረው ፣ ምኩራቦቻቸውንና ሱቆቻቸው የጋዩበት ፣ (ክሪስታልናኽት) አየተባለ የሚጠቀሰው ዕለት የዋለው ኅዳር 9 ቀን ነበረ። በዚህ ምክንያትም ነው ጀርመን የውኅደቱን መታሰቢያ ዕለት እ ጎ አ ጥቅምት 3 ቀን ላይ እንዲከበር የወሰነች።

በውጭ የፖለቲካ አመራር ዘይቤዋ፣ ለአውሮፓ አንድነት ዐቢይ ግምት በመስጠት የበኩሏን ጥረት ስታደረግ የቆየችው ጀርመን፣ የራሷን ውኅደት ካጠናቀቀች በኋላም ቢሆን ስለ አውሮፓ ውኅደት አስፈላጊነት ከመወትወት የቦዘነችበት ጊዜ የለም። ከ 20 ዓመት በፊት ፕራግ ውስጥ በሚገኘው የጀርመን ፌደራል ሪፓብሊክ ኤምባሲ፣ ተገን የጠየቁ 4,500 ያህል የምሥራቅ ጀርመን ዜጎች፣ ወደ ምዕራብ ጀርመን እንዲጓዙ ከያኔው የቼኮዝሎቫኪያ መንግሥት ጋር ተደራድርው ፣ ወደ ምዕራብ ጀርመን እንዲገቡ ያበቁት የያኔው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሐንስ ዲትሪኽ ጌንሸር ነበሩ፣ ምሥራቅ ጀርመናውያኑ ተገን ጠያቂዎች የወሰዱት ደፋር እርምጃ፣ ጌንሸር ያሳዩት የዲፕሎማሲ ችሎታ፣ እነዚህና የመሳሰሉት ተደማምረው የቀዝቃዛው ጦርነት እንዲያከትምና፣ የጀርመን ውኅደትም እውን እንዲሆን አብቅተዋል።

«ልናሳውቃችሁ ወደ እናንተ የመጣነው ፣ ከዚህ ወደ ምዕራብ ጀርመን መግባት የሚያስችለውን ቪዛ --»

የአሁኑ ፣ የ 82 ዓመት አዛውንት ጌንሸር፣ 20 ዓመት የሆነውን የያኔውን ድርጊት ለማስታወስ ከሰሞኑ ወደ ፕራግ ብቅ ብለው ነበር። በዚያም፣ ያሰሙት መልእክት የአውሮፓ አንድነት ዛሬም እጅግ ተፈላጊ መሆኑን የሚስገነዝብ ነበር።

የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች ከ 12 አሁን ቁጥራቸው ተበራክቶ 27 ደርሰዋል። 3 አገሮች ኅብረቱ ይበልጥ ወደ አንድንት የሚያመራበትን ሁኔታ የፈቀዱት አይመስልም። ቼክ ሪፓብሊክ ረቂቁን ውል እንዳታጸድቀው 17 የምክር ቤት አባላት በህገ-መንግሥታዊው ፍርድ ቤት ክስ አቅርበዋል። የፖላንድ ፕሬዚዳንት አየርልንድ ከተስማማች፣ በመጪው ሳምንት በፌርማዬ ረቂቁን ውል አጸድቃለሁ ነው ያሉት።

ከ 16 ወራት ገደማ ወዲህ እንደገና፣ ዛሬ፣ አደባባይ ወጥቶ ድምፁን ሲሰጥ የዋለው የአየርላንድ ህዝብ፤ በሊዝበን ፣ ፖርቱጋል፣ ስምምነት የተደረገበትን የአውሮፓን አንድነት የሚያጠናክረውን የተሃድሶ ረቂቅ ውል ይቀበለዋል ተብሎ ነው ተስፋ የሚደረገው። የደምፅ አሰጣጡ ሥነ-ሥርዓት እስከ ምሽት የሚካሄድ ሲሆን ውጤቱ ነገ ከቀትር በኋላ ተጣርቶ እንደሚታወቅ ነው የተገለጠው። የደምጽ ቆጠራው ውጤት ፣ ለአውሮፓ አንድነት የሚበጅ ይሁንታ ካለበት፣ የነገው የጀርመን ብሔራዊ የአንድነት ክብረ በዓል፣ ይበልጥ የደመቀ እንደሚሆን ነው የሚታመነው።

ተክሌ የኋላ/አርያም ተክሌ