ጀርመንና አፍሪቃ | የጋዜጦች አምድ | DW | 05.11.2003
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

ጀርመንና አፍሪቃ

ጀርመን ከአፍሪቃ ጋር ለመቀራረብ ያላት ፍላጎት የቀድሞዎቹ ቅኝ-ገዥዎች ብሪታንያና ፈረንሳይ ስለ አፍሪቃ ከሚከተሉት የፖለቲካ መርሕ ጋር የሚነፃፀር አይደለም። ሆኖም፣ ያው አህጉር ዛሬ እንደገና ትርጓሜ ያገኘ መስሎ ነው የሚታየው። ይህም አሁን በተለይም በዓለም አቀፉ ሽብርፈጠራ አንፃር በሚደረገው ትግል ረገድ ነው የሚጎላው።

አፍሪቃ ዛሬ የጀርመንን ልቡና በመሳብ ላይ የምተገኝ ነው የሚመስለው። ለዚሁም ዓይነተኛ ማስረጃ የሚሆነው፥ ከዐበይቱ ጀርመናውያን ፖለቲከኞች መካከል ጥቂቶቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ አፍሪቃን እየዞሩ የሥራ ጉብኝት የሚያከናውኑበት ሁኔታ ነው። በዚህም መሠረት፣ የጀርመን መራሔመንግሥት ጌርሃርት ሽረደር በመጭው ጥር አፍሪቃን ለመጎብኘት አቅደዋል፣ ከዚያ ቀጥለው ብዙ ሳይቆዩ የጀርመን ርእሰብሔር ዮሐንስ ራው ወደ አፍሪቃ ይጓዛሉ። ጀርመናዊቱ የልማት ትብብር ሚኒስትሪት ሃይደማሪ ቪቾረክ-ትሶይል ከቅርብ ጊዜ በፊት ኬንያ ውስጥ ነበሩ፤ ውጭ-ጉዳይ ሚኒስትር ዮሽካ ፊሸር ደግሞ ባለፈው ሣም’ንት ደቡባዊውን የአፍሪቃ ከፊል ጎብኝተው ነው የተመለሱት። ፊሸርን አጅበው ወደ አፍሪቃ የተጓዙት፣ ለአፍሪቃ ጥናት የቆመው ተቋም ኃላፊ አንድሪያስ ሜለር እንደሚያስረዱት፣ ጀርመን ስለ አፍሪቃ ስትከተለው የነበረው ፖለቲካ-መርሕ የጀርመን የውጭ ፖለቲካ ዐቢይ ከፊል አልነበረም፣ አሁን ግን ሁኔታው እየተቀየረ ነው፣ የጀርመን ውጭ-ጉዳይ ሚኒስትር ዮሽካ ፊሸር አፍሪቃ ውስጥ አምስት የጉብኝት ቀናት ያሳለፉበት ድርጊት ራሱ አፍሪቃ የጀርመንን ልቡና የምትስብበት ሁኔታ እንዲጠናከር ሊያደርገው ይችላል።

ግን ጀርመን አፍሪቃ ውስጥ የሚታያት ጥቅም የትኛው ነው? ከኤኮኖሚው አንፃር ስትታይ አፍሪቃ ትርጓሜ እያጣች ነው የተገኘችው። ከጀርመን ወደ አፍሪቃ የሚላኩትም ሆኑ ወይም ከአፍሪቃ ወደ ጀርመን የሚገቡት ሸቀጦች ይዘት በጣም ነው የተቀነሰው። አፍሪቃ ውስጥ የኤኮኖሚ ክብደት ያላቸው ሀገሮች ደቡብ አፍሪቃና ናይጀሪያ ብቻ ናቸው። ሌሎቹ እምብዛም የሚዳዱ አይደሉም። ሆኖም፣ ውጭ-ጉዳይ ሚኒስትር ፊሸር እንደሚያስገነዝቡት፣ አጽናፋዊው ትሥሥር በሚጎላበት በ21ኛው ምእተ-ዓመት አፍሪቃውያኑ ሚናቸውን የሚጫወቱ ይሆናሉ፣ መጫወትም አለባቸው። “ ግዙፍ ይዘት ያለው ይህ ጎረቤት አህጉር ከዓለም ኤኮኖሚ ትሥሥር ተላቆና ተፈንጥሮ መቅረት የለበትም፣ ይህ እንዳይሆን የጋራውን ጥረት ማጠናከር አለብን” ይላል የውጭ-ጉዳይ ሚኒስትር ፊሸር ማስገንዘቢያ። የጋራው ጥረት ታዲያ፣ የዓለም ገበያው በር ለአፍሪቃ ክፍት እንዲሆን የሚደረግበትንም ርምጃ ነው የሚመለከተው። ይህ ሲሆን ብቻ ነው አህጉሩ የኤኮኖሚ ዕድገት ዕድል የሚኖረው። ከዚህም በላይ፣ የአፍሪቃ ጥናቱ ተቋም ኃላፊ አንድሪያስ ሜለር እንደሚሉት፣ አፍሪቃ ውስጥ ከኤኢኮኖሚው ጥቅም ውጭ ሌላም ጥቅም ነው የሚታየው፥ ጀርመን ውስጥ በሕገመንግሥት የጠበቀው እሴት አፍሪቃም ውስጥ እንዲከበር ይፈለጋል፥ ዴሞክራሲ፣ ሰብዓዊ መብት......ወዘተ እዚያም መከበር አለባቸው። በመስከረም አንድ፣ አሜሪካ ውስጥ የተጣለው ከባድ የሽብ’ርተኞች አደጋ እንዳሳየው፣ የጋራው ደኅን’ነት፣ የጋራውን ርምጃ ይጠይቃል። ድህነት፣ የትምህርት ጉድለት ተሥፋአልባነት...ይህ ሁሉ ለሽብረተኛነት መንገድ ይሰጣል። በዚህ አንፃር ትግሉ የጋራ መሆን አለበት።

አፍሪቃ ውስጥ የውዒሎተንዋይ ተሳትፎ ማድረግና ለዚያው አህጉር ትኩረትና ትርጓሜ መስጠት ምኑን ያህል ፍሬኣማ ሊሆን እ’ንደሚችል ምዕራብ አፍሪቃዊቱ ሀገር ማሊ አንድ ምሳሌ ትሆናለች። የማሊው ፕሬዚደንት ጣልቃ ባይገቡና ድጋፍ ባይሰጡ ኖሮ፣ ሰሐራው በረሃ ውስጥ በእግት ተይዘው የነበሩት ፲፬ቱ ቱሪስቶች ምናልባት እስካሁኑ ጊዜ ድረስ ነፃነታቸውን እንደተቀሙ በቆዩም ነበር። “ጀርመን ሁልጊዜ ሰጭ ሆና ነው የቆየችው፣ አሁን ግን እኛም በበኩላችን አንድ ጊዜ እንኳ ጀርመንን ለመርዳት በመቻላችን ክብር ይሰማናል” ይላል የማሊው ፕሬዚደንት አማዱ ቱማኒ ቱሬ ቱሪስቶቹን ከአጋቾቹ አክራሪዎች እጅ ባስለቀቁበት ወቅት በእርካታ ያሰሙት ቃል።