ጀርመናዊው እና የኢትዮጵያ ሙዚቃ ፍቅራቸዉ | ባህል | DW | 28.08.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

ጀርመናዊው እና የኢትዮጵያ ሙዚቃ ፍቅራቸዉ

ቡሄን አስታከን ሆያ ሆዬን ይዘን ብቅ ያልነዉ ዘግየት ብለን ቢሆንም፤ እንደ ባህላችን አዲስ ዓመት ጠብቶ መስቀል በዓል እስኪከበር ሆያሆዬን መጨፈራችን የታወቀ ነዉና፤ ዛሬም ጀርመናዉያኑ ሆያ ሆዬ ባስጨፈሩበት የኢትዮጵያ ባህላዊ የቡሄ ዜማ የዕለቱን ዝግጅት ለመጀመር ወሰን። ሆያሆዬ ያስጨፈሩት ጀርመናዉያኑ የሙዚቃ ባንድ ካሪቡኒ አዲስ ይባላል።

በርካታ የአማርኛ ሙዚቃን ከጀርመንኛ እና ከእንግሊዘኛ ጋር በማቅረብ መሃል አዉሮጳ ላይ የሚታወቁት «ካሪቡኒ አዲስ የሙዚቃ ባንድ»፤ ባለፈዉ ሳምንት መጨረሻ እዚህ በቦን ከተማ መሃል አደባባይ የሙዚቃ ድግሳቸዉን አቅርበዉ፤ በተለይ ስለኢትዮጵያ ባህላዊ ሙዚቃ ክራርና ቅኝት እንዲሁም ስለሃገሪቱ ባህላዊ ጉዳዮች ለሙዚቃ እድምተኞች አቅርበዋል። በዛሪዉ ዝግጅታችን በተለይ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃን ለምዕራቡ ዓለም በማስተዋወቃቸዉ የሚታወቁትን ጀርመናዊ እንግዳ አድርገን ጋብዘናል። በጀርመን የታወቁ ሙዚቀኛ ናቸዉ፤ ፒት ቡደ። በጀርመን ስለ ኢትዮጵያ ባህላዊ ሙዚቃ ሲነሳም ስማቸዉ የሚነሳዉ የፒትቡደ ነዉ። ከኢትዮጵያ ባህላዊ ሙዚቃ ጋር ከተዋወቁ ሶስት አስር ዓመታት ሊሆናቸዉ እንደሆን የሚናገሩት ፒት፤ ከኢትዮጵያ ባህላዊ ሙዚቃ ጋር ብቻ ሳይሆን ፍቅራቸዉ ከኢትዮጵያ አየርዋ አፈርዋ ህዝቧና ባህሏ ጋርም እንደሆን በኩራት ይናገራሉ። ስለኢትዮጵያ ሙዚቃዋ ባህልዋ እና ስለሀገሪቷ «WDR» እና ሄስሸ ሩንድ ፉንክ ለተሰኙት ታዋቂ የጀርመን ብዙሃን መገናኛዎች፤ የተለያዩ ዘገባዎችን አቅርበዋል። የስድሳ ሁለት ዓመቱ ጀርመናዊ ፒት ቡደ ፤ ኢትዮጵያን እና ሙዚቃዋን እንዲት ለመጀመርያ ግዜ እንዴት ለመተዋወቅ በቅተዉ ይሆን፤

« ከኢትዮጵያ ሙዚቃ እና ከኢትዮጵያ ጋር የተዋወኩት በባለቤቴ በጆሴፊኒ በኩል ነዉ። ባለቤቴ ኢትዮጵያዊት ናት።ከባለቤቴ ጋር ወደ ኢትዮጵያ ሄጄም ብዙ የኢትዮጵያ ሙዚቃን ለማድመጥ፤ በርካታ ሙዚቀኞችን ለመተዋወቅ በቅቻለሁ። ከዝያ በኃላ ነዉ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ያለኝ ስሜት እየጨመረ የመጣዉ፤ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ሙዚቃ እኔ ከዚ ቀደም ከማዉቀዉና ከሰማሁት ለየት ያለ ሆነ ነበር ያገኘሁት። ያንን ስል ከሌሎች የአፍሪቃ ሃገራት ሁሉ ለየት ያለ ሆኖ አግንቸዋለሁ። በዝያም ምክንያት ነዉ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ስሜት እያደረብኝ የመጣዉ»

በስዋሂሊ ቋንቋ "Karibuni" እንኳን ደህና መጣችሁ የሚል መጠርያን የያዘዉ የሙዚቃ ቡድን መስራቾቹ ጀርመናዊዉ ፒት ቡደ እና በእናትዋ ኢትዮጽያዊት የሆነችዉ ባለቤቱ ጆሴፊነ ክሮንፍሊ በጀርመን ለመጀመርያ ግዜ የዓለም ሙዚቃ ለህጻናት በሚል የሙዚቃ አልበም በማቅረባቸዉ ይታወቃሉ። እስከዛሪም ከአስር በላይ ሙዚቃ አልብምን አሳትመዋል። ፒት ቡደ ከኢትዮጵያን ለመጎብኘት ለመጀመርያ ግዜ ወደ ኢትዮጵያ መቼ ይሆን የሄዱት፤ «ኢትዮጵያን ለመጀመርያ ግዜ ያየሁት ባልሳሳት በጎአ በ1988 ዓ,ም አልያም በ1989 ዓ,ም ነዉ።»

ታድያ ኢትዮጵያን ጎብኝቶ ለማያዉቅ ጀርመናዊም ሆነ ምዕራባዊ፤ ኢትዮጵያን እንዴት ይገልጿት ይሆን?ፒት ቡደ መልስ አላቸዉ፤

« ስለ ኢትዮጵያ የምገልፀዉ በጣም በአድናቆትና በጉጉት ነዉ። ገልፆ ማሳመኑም በርግጥ እጅግ ከባድ ነዉ። ለምሳሌ መጀመርያ ወደ ኢትዮጵያ ተጉዤ አዲስ አበባ ቦሌ አየር ማረፍያ እንደደረስኩ፤ የሃገሪቱ አየር ልዩ ሆኖ ነዉ ያገኘሁት ፤ በርግጥ አዲስ አበባ በዝያን ግዜ ሁኔታዉ ሁሉ ልዩ ነበር እንደአሁን አይደለም። አዲስ አበባን መጀመርያ እንዳየኋት በተራራ የተከበበች ዉብ አየርዋ ንጹህ ሆና ነዉ ያገኘሁት። በከተማዋ የሚታየዉ ዛፍ እፅዋት እና አዋፋት ልዩና ማራኪ ሆነዉ ነበር ያገኘኻቸዉ። ከዝያ ቀደም ብዬ ሌላ አፍሪቃ ሃገራትን ጎብኝቻለሁ፤ ግን ኢትዮጵያን ያገኘኋት ከሌሎቹ ሃገሮች ሁሉ ለየት ያለች ሆና ነዉ። ኢትዮጵያ ታይታ የማትጠገብ ሁሌም ለጉብኝት አጓጊ ሆና ነዉ ያገኘኻት። በርግጥም፤ ይህ ለኢትዮጵያ ያለኝ አይነቱ ስሜት ደሞ ኢትዮጵያን የጎበኙ የዉጭ ዜጎች ሁሉ ስሜት ነዉ»

ለአንድ ምዕራባዊ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ለመጀመርያ ግዜ በጆሮ መንቆርቆሩ እጅግ አጠራጣሪ ነዉ፤ ግን የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃን አፍቃሪዉ ፒት ቡደ መጀመርያ ያደመጡት ሙዚቃ የትኛዉን ነበር?

«በርግጥ መጀመርያ ያደመጥኩት ይሄኛዉን የኢትዮጵያ ሙዚቃ ነበር ብሎ ማለቱ እጅግ ይከብደኛል። ግን በመጀመርያዎቹ ወቅቶች ያደመጥከዉ የየትኛዉን ከያኒ ሙዚቃ ነበር ብባል ለመመለስ ይቀለኛል። መጀመርያ ወቅት የሰማሁት አንጋፋዉን ሙዚቀኛ መሃሙድ አህመድን ነበር። ከዝያም የአስቴር አወቀን ብዙነሽን በቀለን ነበር። ከባህላዊ ደግሞ ዉብዋ የክራር እመቤት የአስናቀች ወርቁን፤ የካሳ ተሰማን ሙዚቃ ነበር የተዋወኩት፤ ይህን ነዉ እንግዲህ በመጀመርያዎቹ ወቅቶች የማስታዉሰዉ»

ታድያ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ምን የተለየ ነገር አገኙበት? ሌላዉ ለፒት ያቀረብኩት ጥያቄ ነበር፤

« ኦ በጣም ብዙ ነገር ነዉ ያገኘሁበት። በጣም በጣም ብዙ ነገር። እንደምታዉቂዉ እኔ ራሴ ሙዚቀኛ ነኝ። ወደ ኢትዮጵያ ከመሄዴ በፊት ከተለያዩ ሃገራት ከመጡ ሙዚቀኞች ጋር ሰርቻለሁ። እናም የኢትዮጵያን ሙዚቃ ለመጀመርያ ግዜ ስሰማ በጣም የተለየ ሆኖ ነዉ ያገኘሁት። በመጀመርያ ደረጃ ሃገሪቱ በቅኝ ግዛት እጅ ስር ባለመዉደቅዋ፤ ያልተበረዘ ያልተቀላቀለ ንፁህ ባህላዊ ነገሮችዋን ነዉ ይዛ የምትገኘዉ። በሙዚቃ ረገድም ቢሆን፤ ንጹህ የኢትዮጵያ ባህላዊ ዜማን እና ሙዚቃን ነዉ የምናገኘዉ። ያንን ሥል፤በኢትዮጵያ ሙዚቃ ዉስጥ የምዕራቡ የሙዚቃ ቅኝት ገብቶ የሚደመጥበት አጋጣሚ እጅግ ኢምንት ነዉ። ያንን ሥል ግን የምዕራባዉያኑ የሙዚቃ ቅኝት አልገባም ማለቴ ሳይሆን፤ በኢትዮጵያ ባህላዊ ቅኝት እና ሙዚቃ በማንኛዉም አይነት ሙዚቃዋ ላይ መሰረት ሆኖ ይደመጣል። በርግጥ በአሁኑ ሰዓት በአፅናፋዊዉ ትስስር ማለት በግሎባላይዜሽን ምክንያት፤ የምዕራባዉያኑ የሙዚቃ ቅኝት በኢትዮጵያ ሙዚቃ ዉስጥም እጅግ እየሰፋ መምጣቱ ይታያል። እንድያም ሆኖ ታድያ በማንኛዉም የኢትዮጵያ ሙዚቃ ዉስጥ ባህላዊ ቅኝቶች ጥቅም ላይ ዉለዉ ይደመጣሉ። በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ ሙዚቃ ባህላዊ ቅኝቶቹን ይዞ በመጓዙ ከሌሎቹ ሃገራት ሙዚቃ እጅግ ልዩ እንዲሆን ያደርገዋል። በሌሎች ሃገራት ግን የምዕራባዉያኑ የሙዚቃ ቅኝት እጅግ አመዝኖ ነዉ የሚታየዉ»

ፒት ቡደ ከባለቤታቸዉ ጋር ያቋቋሙት ካሪቡኒ የሙዚቃ ቡድን የዓለም ሃገራት የተለያዩ ባህሎችን በማጣመር ሙዚቃን በማዉጣቱ በጀርመን ሀገር የተለያዩ ሽልማቶችን አግኝቶአል፤ በተለይም ለህጻናት የሚሆን ሙዚቃዎችን በማሳተሙም ቡድኑ እጅግ ይታወቃል። ፒት ቡደ፤ ለመጀመርያ ግዜ የተዋወቁት የኢትዮጵያ ሙዚቀኛ ማን ይባል ይሆን ? ፒት ይመልሳሉ፤

መጀመርያ የተዋወኩት መሃሙድ አህመድን ነዉ። መሃሙድን ባለቤቴ ጆሴፊን ከልጅነት ጀምሮ ታዉቀዋለች። የባለቤቴ አባት አዲስ አበባ ዉስጥ አንድ የምሽት ጭፈራ ቤት ነበራቸዉ፤ እና በዚህ ጭፈራ ቤት ጥላሁን ገሰሰ፤ መሃሙድ አህመድ እነ ብዙነሽ በቀለ ሁሉ በመድረኩ ለመጫወት ይመጡ ነበር። በዚህ ምክንያትም መሃሙድን ብዙ ግዜ አግንቸዋለሁ። ለጀርመን እና የተለያዩ የመሃል አዉሮጳ ሃገራትንለማስተዋወቅ በራድዮ መፅሄት ቃለ ምልልስ አድርጌለታለሁ። በአፅህሮት WDR የተሰኘዉ በጀርመን ታዋቂ የሆነዉ የብዙሃን መገናኛ እንዲጋብዘዉ አድርጌ ወደ ጀርመን መጥቶ ራሱን አስተዋዉቆአል። ከያኒ ሙላቱ አስታጥቄንም ተዋዉቄዋለሁ። ስለ ኢትዮጵያ ሙዚቃ እሱ ስላለዉ የስራ ልምድ ሁሉ ተጨዋዉተናል። በጣም ዝነኛ የሆነዉ የዋሽንት ተጫዋች፤ ዩሃንስ አፈወርቅንም አዉቀዋለሁ፤ በጣም የሚደነቅ ሙዚቀኛ ነዉ። ሌላዉ የያሪድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት በመምህርነት ሲያገለግሉ ሳለ የተዋወክዋቸዉ፤ ሙዚቀኛ አለማየሁ ፋንታም አሉ። አለማየሁ ፋንታን እዚህ ጀርመንም ጋብዣቸዉ ነበር። የክራርዋ እመቤት አስናቀች ወርቁንም በቅርብ ለመተዋወቅ እድል አግንቼ ነበር። ለመጀመርያ ግዜ ያየኋት በብሄራዊ ትያትር መድረክ ላይ ሆና ነበር። ከዝያም ቤትዋ ሄጄ ተዋዉቅያት ፤ ወደዚህ ወደ ጀርመን ለተደጋጋሚ ግዜ ጋብዣት ነበር። ሙዚቃዎችዋንም እዚህ በጀርመን አሳትማለች፤ በርካታ መድረኮች ላይ ቀርባም እጅግ ተደንቃለች። ሌላዉ ታዋቂዉ በገና ደርዳሪ አለሙ አጋንም በደንብ አዉቃቸዋለሁ። አቶ አለሙ በተደጋጋሚ ወደ ጀርመን መጥተዉ በተለያዩ መድረኮች ከበገናቸዉ ጋር ቀርበዋል። ከወጣቶችም ቢሆን በርካቶችን አዉቃለሁ። ከዘመናዊ ሙዚቃ ታዋቂዉ ወጣት ሙዚቀኛ ግሩም መዝሙር አንዱ ነዉ»

ታዋቂዉ ሙዚቀኛ ፒት ቡደ፤ ከኢትዮጵያ ሙዚቀኞችን ወደ ጀርመን መድረክ ሲጋብዙ ምን አይነት መስፈርቶችን በማሰብ ይሆን? የኢትዮጵያ ጃዝ የኢትዮጵያ ባህላዊ ሙዚቃም እጅግ ማራኪ ነዉ ሲሉ የሚናገሩት ፒት በመቀጠል፤ የኢትዮጵያ ጃዝ የኢትዮጵያ ባህላዊ ሙዚቃም እጅግ ማራኪ ነዉ። ግን ለጀርመን እና ለሌሎች ምዕራባዉያን ሃገሮች ማራኪ የሚሆነዉ ለየት ያለዉ የሙዚቃ መሳርያ እና የሙዚቃ ቅኝቱ እንዲሁም ዜማዉ በመሆኑ በአብዛኛዉ የምጋብዘዉ ባህላዊ ሙዚቀኞችን ነዉ። ለምሳሌ ከዚህ ቀደም ያደረኩት በተለያዩ የጀርመን ከተሞች አለማየሁ ፋንታንአስናቀች ወርቁን እንዲሁም አለሙ አጋን ጋብዤ የኢትዮጵያን ባህላዊ የሙዚቃ መሳርያ እና የሙዚቃ ቅኝቶችን ለማስተዋወቅ ሞክርያለሁ። ጀርመናዉያን የኢትዮጵያ ሙዚቃመሰረቱ ጥንታዊ በመሆኑ፤የሙዚቃ መሳርያዉምጥንታዊ በመሆኑ እጅግ ማራኪ ሆኖ ነዉ የሚያገኙት።

ጀርመናዉያን ይላሉ ፒት በመቀጠል ጀርመናዉያን ወደዚህ ወደጀርመን በተጋበዙት ከያንያን አማካኝነት የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ካዳመጡ ባህላዊ የሙዚቃ መሳርያዉን ከተዋወቁ በኋላ እጅግ ይገረማሉ። ስለ ጥንታዊ ታሪክዋም ይበልጥ ለማወቅ ፍላጎት ሲያድርባቸዉ ይታያል ሲሉም ይገልፃሉ። የአስናቀች ወርቁን እና የዓለሙ አጋን የሙዚቃ ስራዎች በሲዲ ያሳተሙት ፒት ቡደ የክራርዋ እመቤት አስናቀች ወርቁ ፊርማዋን ያኖረችበት የግል ክራርዋን እንደሰጠቻቸዉ ሲናገሩ በኩራት ነዉ። ፒት ቡደ በመጭዉ ጎርጎረሳዊ 2015 ዓ,ም እንደባተ WDR በተሰኘዉ የጀርመን የብዙሃን መገናኛ በኩል የተለያዩ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ከባህላዊ መሳርያዎቻቸዉ ጋር መጋበዛቸዉንና በተለያዩ ከተማ በሚገኙ ግዙፍ የሙዚቃ መድረኮች በክራር እና በማሲንቆ የታጀበ የኢትዮጵያ ባህላዊ ሙዚቃ እንደሚደዘጋጅ አጫዉተዉናል።

ዓመት አዉዳመትና ድገምና ዓመት የመቤቴን ቤት ድገምና ዓመት ወርቅ ይፍሰስበት ይላሉ በጀርመንኛ ቋንቋ ያዜሙት የኢትዮጵያ ባህላዊ ዜማ። ጀርመናዊዉ የኢትዮጵያ ባህላዊ ሙዚቃን አፍቃሪ ፒት ቡደን ያስተዋወቅንበት የለቱን ዝግጅት እዚህ ላይ አጠናቀቅን። ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን ያድምጡ!

አዜብ ታደሰ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic