1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፍራንክ ፋርያን በጀርመን ዉስጥ ትልቅ የሙዚቃ ጥበብተኛ እንደሆነ የታወቀ ነገር ነዉ።

ዓርብ፣ ሐምሌ 15 2008

በተለያዩ ሆቴሎችና ምግብ ቤቶች ምግብ በማብሰል ስራ ያገለገለዉ ታዋቂዉ ጀርመናዊ የሙዚቃ ደራሲ ፍራንክ ፋርያን የሰዎችን ፍላጎት በደንብ ያዉቃል ይላል፣ ባለፈዉ ሰኞ 75ኛ የልደት ቀኑን በማስመልከት የወጣዉ ዘገባ። Bonny M. ስለተባሉት ሙዚቀኞችና ሙዚቃዎቻቸዉ ምን ያዉቃሉ?

https://p.dw.com/p/1JTvs
Deutschland Musik Pop Hitproduzent Frank Farian
ፍራንክ ፋርያን ከቦንየም የሙዚቃ ቀንቃኞች ጋርምስል picture-alliance/dpa

ጀርመናዊዉ የ«ቦኒ ኤም» ዎች መስራችና ሥራዎቹ

በ1970 ዎቹ ታዋቂ የነበሩት በተለይ በዝያን ዘመን በዓለም ዙርያ ዲስኮ በማስጨፈራቸዉ የሚታወቁት የ« ቦኒ ኤም» የሙዚቃ ባንድ መሰራች ጀርመናዊ የሙዚቃ ደራሲና ቀማሪ ፍራንክ ፋርያን መሆኑን ስንቶቻችን እናዉቅ ይሆን? የእዉቁን ጀርመናዊ የሙዚቃ ደራሲ የፍራንክ ፋርያንን ሙዚቃዎች ይዘን ታሪኩን እንቃኛለን ። ታዋቂዉ ጀርመናዊ የሙዚቃ ደራሲና ቀማሪ ፋራንክ ፋርያን በያዝነዉ ሳምንት 75 ኛ ዓመት የትዉልድ ቀኑን አክብሮአል። በጀርመን በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃኖች ሙዚቃዎቹ በተደጋጋሚ ተደምጠዉለታል። በርካታ የሙዚቃ አልበምን በዓለም ዙርያ በመሸጡ የሚታወቀዉ ፋራንክ ፋርያን « ቦኒ ኤም» ዎች ጨምሮ በጀርመን ታዋቂ የሆነችዉን ሙዚቀኛ ኢቮን ካታፊልድ እንዲሁም አሜሪካዊዉን የሮክ ሙዚቃ አቀንቃኝ ሚት ሎፍን በሙዚቃዉ መድረክ እዉቅና እንዲያገኙ ያደረገም ነዉ።

በጎርጎረሳዉያኑ 1941 ዓ,ም ሐምሌ 18 ፤ በጀርመን በራይንላንድ ፋልዝ ግዛት ኬርን በምትባል አነስተኛ ከተማ የተወለደዉ ጀርመናዊዉ ሙዚቀኛ ፍራን ፋርያን፤ የትዉልድ ስሙ ፍራንክ ሮይት ይባል ነበር። ፋራንክ በሆቴል ቤት ምግብ አብሳይነት ይተዳደር ሳለ ከስራዉ ዉጭ ይኖርበት በነበረዉ ቤት ጣርያ ላይ ባለች ክፍል ዉስጥ የራሱን ሙዚቃ መቀመርያ ክፍል አዘጋጅቶ፤ ሙዚቃን በመቀመር ይለማመድ፤ የሙዚቃ ፍቅሩንም ይወጣ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ። ፍራንክ የመጀመርያና ይግሉ የሆነዉን ጊታር ይዞ፤ መጫወት የጀመረዉ በ12 ዓመቱ ነበር። ፍራንክ ሙዚቃን ከልጅነቱ ጀምሮ ይጫወት እንጂ፤ በተለያዩ የምግብ ቤቶች እየተዘዋወረ ምግብ ያበስል ነበር። ፍራንክ ለምን ምግብ አብሳይ እንደነበር ሲጠየቅ « ሁሌ ይርበኝ ስለነበር ነበር» ሲል ፤ ለንግግር መጀመርያ ያህል መልስ በመስጠት ይጀምራል ከዝያም ምክንያቱን እንዲህ ያስረዳል።

«ለሦስት ዓመታት ዴልብሩክ ዉስጥ በምግብ አብሳይነት አገልግያለሁ። ጥሩ ገንዘብም አገኝ ነበር። እናቴም በሥራዬ በጣም ደስተኛ ነበረች። ከእለታት አንድ ቀን በአንድ የሙዚቃ ድግስ ላይ ድንገት አንድ የሮክ የሙዚቃ ባንድ ድንቅ የሆነ ሙዚቃን መድረክ ላይ ሲያቀርብ አየሁ። በጣም የተደነቀ ዝግጅት ነበር። ከዝያ በኋላ በአዕምሮዬ ያለ ሙዚቃ ሌላ ነገር መኖሩን ማሰብ አቃተኝ። ይህንኑ የሙዚቃ ባንድ ለማየት በአንድ ለሊት ወስኜ ጉዞዬን ወደ ሃንቡርግ ከተማ አደረኩ። እዝያም የሙዚቃ ባንዱን ከአየሁ ከግማሽ ዓመት በኋላ የራሴን የሙዚቃ ባንድ አቋቋምኩ።»

የታዋቂዉን የቦንየሞች የሙዚቃ ባንድ መስራች ፍራንክ ፋርያን የሮክ ሙዚቃ ፍቅር ያደረበት ታዋቂዉን አሜሪካዊ ሙዚቀኛ ኢልቪስ ፕሪስሊንና ቢል ሃሌን በመድረክ ላይ ካየ በኋላ እንደነበር ይናገራል። ከዝያም ነዉ ፍራንክ ፋርያም በምግብ ማብሰል ሞያ ሲያገለግል ያጠራቀመዉን ገንዘብ የሙዚቃ መጫወቻ መሳርያን ገዝቶ በስድስት ወሩ የራሱን ባንድ አቋቋሞ በመድረክ ላይ እራሱ በማዜም በአንድ ምሽት እስከ 300 ማርክ ድረስ ያገኝ የነበረዉ። ፍራንክ በከብቶች ጋጣ ዉስጥ ያቀናበረዉና የመጀመርያ ሙዚቃ በሸክላ ያሳተመዉ ሙዚቃ ወደ 1000 ሺህ ቅጅ ተሸጦለታል። ከዝያም በጎርጎረሳዊዉ 1960ዓ,ም ጀርመናዊዉ የሙዚቃ ቀማሪ ፍራንክ ፋርያን ከሙዚቃ አሳታሚ ድርጅት ጋር ዉል ለመፈራረም በቃ። ፋራንክ ዉሉን ካገኘ በኋላ ትልቅ የሙዚቃ ዝግጅት የተባለለትን የመጀመርያዉን የአገር ባህል ሙዚቃን «ZDF» በተሰኘዉ የጀርመን ቴሌቭዥን ጣብያ መድረክ ላይ አቀረበ።

ፍራንክ ፋርያን ይህን የጀርመን ባህላዊ ሙዚቃን በአቀረበበት ግዜያት ነበር ታዋቂዉን የ« ቦኒ ኤም» የሙዚቃ ባንድ ያቋቁመዉ። በጎርጎሳዉያኑ 1975 ዓ,ም « ቦኒ ኤም»» በሚል ስም የተቋቋመዉ የፍራንክ ፋርያን የሙዚቃ ቡድን በካረብያን ተወልደዉ አዉሮጳ ዉስጥ ካደጉ ሦስት ሴቶችና አንድ ወንድ አቀንቃኞች ያሉበት የሙዚቃ ባድን ነዉ። «Daddy Cool» ለቦንየሞች የመጀመርያ ነጠላ ዜማ ሲሆን፤ በተለይ ቦቢ ፋሪል የተባለዉና በልዩ ዉዝዋዜዉና ዳንሱ የሚታወቀዉ የቡድኑ አቀንቃኝ መድረክ ላይ ከልዩ ዳንስና ከንፈሩን እንደሚዘፍን ያህል ከማንቀሳቀስ በበስተቀር ሲያዜም የሚሰማዉ የራሱ ሙዚቃ ቀማሪዉ የጀርመናዊ ፍራንክ ፋርያን ድምፅ ነዉ። ፍራንክ ይህን የሚያደርገዉ ከስቱድዮ እንደነበርና ቆየት ብሎ በመድረክ ከማዜም ይልቅ ስቱድዮ ቁጭ ብሎ ሙዚቃ መቀመርን መምረጡን ተናግሮአል።

« የሙዚቃ ባንዴን ይዤ ከአንድ ቦታ ወደሌላ ቦታ መዘዋወርን አልቻልኩም፤ በየጊዜዉ ባንዱ ሲጫወት ቦታዉ ላይ በመገኘት የሙዚቃ መሳርያዎቹን ሁሉ መድረክ ላይ መግጠም መንቀሉ ሁሉ ደከመኝ፤ በጣም ታከተኝ ፤ አልቻልኩም ። ከዝያ በኋላ ነዉ ስቱድዮ ዉስጥ ሆኜ ሙዚቃ መቀመርና፤ ስቱድዮ የማረፍያ ክፍሌ መሆኑን የተረዳሁት። በኋላም ከዚሁ የማረፍያ ክፍሌ ሙዚቃን መሥራት ጀመርኩ። » « ቦኒ ኤም» ሙዚቃ በተለይ በተለይ ደሞ የመጀመርያዉ ሙዚቃ ዳዲ ኩል ከጀርመን አልፎ በዓለም ዙርያ ተወዳጅነትን ያገኘ ነጠላ ዜማ ነበር። ሙዚቃ ቡድኑ ከጎርጎረሳዉያኑ 1975 እስከ 1988 ዓ,ም ድረስ በዓለም የሙዚቃ መድረክ በተደማጭነትና ተወዳጅነት የመጀመርያዉን ስፍራንም ይዞ ነበር። « በድንገት ከሚስገድዱኝ ነገሮች ተላቀኩና ነጻ ሆንኩ። ከሙዚቃ አልበም አሳታሚዎች አለቃ ይህን ሥራ ይህን ሥራ ከሚል ትዕዛዝ ተላቅቄ ለራሴ ራሴ አለቃ ሆንኩና የምፈልገዉን መስራት ጀመርኩ። »
ከመድረክ በስተጀርባ በሙዚቃ ሞያ ያለዉን ተሰጦ ተጠቅሞ ከዓለም የሙዚቃ አፍቃሪዎችና የሙዚቃ ድርጅቶች የተለያዩ ሽልማቶችንና እዉቅናን ያገኘዉ ጀርመናዊዉ ፍራንክ ፋርያን፤ ኢትዮጵያ ዉስጥም በዘመኑ የ« ቦኒ ኤም»ና ሚሊ ቫኒሊ ሙዚቃ ታዋቂዎች ነበሩ ፤ ግን ከበስተጀርባ ሆኖ የነዚህ ሙዚቀኞች ተወዳጅ ሙዚቃ ደራሲና ቀማሪ ማን እንደሆን የሚያዉቀዉ እጅግ ጥቂቱ ሳይሆን አልቀረም። በበርሊን ነዋሪ የሆኑት አቶ ኤልያስ ይመር ለትምህርት ወደ ጀርመን ከመምጣታቸዉ በፊት አዲስ አበባ ላይ የ« ቦኒ ኤም» ሙዚቃ ተማርከዋል፤
« ጀርመን ከመምጣቴ በፊት ስለዚህ ሰዉ ሰምቼ አላዉቅም ማን እንደሆን የማዉቀዉም ምንም ነገር የለኝም ነበር። ግን ኢትዮጵያ ሳለሁ እሱ የደረሳቸዉን ያቀናበራቸዉን ሙዚቃዎች የነ« ቦኒ ኤም»ን የሚሊ ቫኒሊ ሙዚቃዎች በጣም አዳምጥ ነበር፤ አገር ቤትም በየጊዜዉ የሚሰሙ ሙዚቃዎች ነበሩ፤ ምንም እንኳ የየ« ቦኒ ኤም» ሙዚቃዎች በ 1970ዎቹ የወጣ ሙዚቃ ቢሆንም፣ እኔ እስከ 80ዎቹ 90 ዎቹ መጨረሻ ድረስ በየቦታዉ የምሰማዉ ሙዚቃ ነበር። እዚህ ጀርመን ከመጣሁ በኋላ ነዉ ፍራንክ ፋርያን ስለሚባለዉ ሰዉ ይበልጥ ያወኩት። የየ« ቦኒ ኤም» ሙዚቃ የሱ እንደሆነ እንደሁም በድምፅም እሱ ራሱ ይጫወት እንደነበር፤ በተለይ በሚሊ ቫኒሊ ጊዜ የበለጠ ይህን ሰዉ ለማወቅ ችያለሁ። ማነዉ ከዚህ ቡዚቃ በስተጀርባ የሚለዉን ሰዉ ማወቅ ችያለሁ። »
እዚህ ከመጣህ በኋላስ እንዴት አገኘኸዉ ስለሱስ ጀርመናዉያን ምን አይነት አስተያየትን ነዉ የሚሰጡት? « ፍራንክ ፋርያን በጀርመን ዉስጥ ትልቅ የሙዚቃ ጥበብተኛ እንደሆነ የታወቀ ነገር ነዉ። እኔ እዚህ ከመጣሁ በኋላ መድረክ ላይ ወጥቶ ሲጫወት አይቼዉ አላዉቅም። ከመድረክ በስተጀርባ ግን በርካታ ሙዚቃዎችን እንደሰራ አዉቃለሁ። እኔ በዉል የማላቃቸዉን በርካታ ሙዚቃዎች ሰርትዋል። ከ« ቦኒ ኤም» ሌላ ሌሎች የኪነጥበብ ሰዎችን ለትልቅ ደረጃ ለዉቅና ያደረሰ የጥበብ ሰዉ ነዉ። በተለይ የማስታዉሰዉ ግን በ« ቦኒ ኤም»ና በሚሊ ቫኒሊ ሙዚቃ ባንዶች ነዉ።»

ፍራንክ ፋርያን ከቦንየሞች በመቀጠል ሚሊ ቫኒሊ የተባለ የሙዚቀኞች ባንድ መስርቶ በ 1980 ዎቹ መጨረሻ ዳግም የተወዳጅነትን ቦታ ያዘ። ለብዙ ጀርመናዉያን ምኞት የሆነዉ ለፍራንክ ፋርያን በቀላሉ የተሳካለት ደግሞ በዝያን ጊዜ ሚሊ ቫኒሊ ይዞ በአሜሪካ የሙዚቃ መድረክ ከፍተኛ ቦታን ማግኘቱ ነበር። የሚሊ ቫኒሊ በተለይ « ገርል ዩኖዉ ኢትስ ትሩ» የተሰኘዉ ሙዚቃ በአሜሪካዉ የተወዳጅ ሙዚቃ መዘርጥር ላይ ለሰባት ሳምንታት የአንደኝነቱን ቦታ ተቆጣጥሮ መዝለቁ ነዉ። በዚህም በዝያን ወቅት የጀርመን የሙዚቃ ባንድ በአሜሪካ ታሪክ የመጀመርያን ስፍራ ማግኘቱ ነበር። የጀርመን የሙዚቃ ቀማሪ ሙዚቃ በአሜሪካ የመጀመርያዉ ስምረት ብዙም ሳይቆይ 1990 ዎቹ ላይ ትልቅ ቅሌት ዉስጥ ተዘፈቀ። ይኸዉም ሚኒ ባኒሊ ራሳቸዉን አሳምረዉ በካሜራ ፊት ዉዝዋዜን ከማሳየትና ከንፈራቸዉን ከማነቃነቅ ይልቅ በድምፅ እንደማይዘፍኑ ታወቀ። ለነገሩ በአሜሪካ ይኽ አይነቱ ድርጊት አሜሪካዉያኑ የማይሆን ነገር «ኖ ጎ» እንደሚሉት ይሁንጂ በጀርመን የ« ቦኒ ኤም» ባንድ ዳዲ ኩል ላይ ወንዱን ተክቶ የሚያዜመዉ ራሱ ፍራንክ ፋርያን ነዉ። በዚህም ሚሊ ቫኒሊ የወሰዱትን በዓለም አቀፉ መድረክ የወሰዱትን ሽልማት እንዲመልሱ፤ ለሸጡት ለየአንዳንዱ የሙዚቃ አልበምም ከነቅጣጡ ገንዘብ እንዲመልሱ ተደርጎአል።

በሚሊ ቫኒሊ ሙዚቃ በዩኤስ አሜሪካ የተወዳጅ ሙዚቃ መዘርዝር ላይ ለሳምንታት አንደኝነትን ተቆጣጥሮ የነበረዉና ቆየት ብሎ ግሪሚ ሽልማትን የተቀበለዉ ቡድን፤ በቅሌቱ ዳግም ቅጣቱን መልሶአል። ፍራንክ ፋርያን ዛሬ በ75 ኛመቱ ሚሊ ቫኒሊን ያስታዉሳል፤ «የሚኒ ቫኒሊ ስህተት፤ አላስፈላጊ ስህተት» ሲልም ይገልፀዋል። ፍራንክ ፋርያን የቦንየሞችን ከ 800 ሚሊዮን በላይ ሙዚቃ አልበምን ሸጥዋል። ፍራንክ ፋርያን በሁለቱ የሙዚቃ ቡድኖች ብቻም ሳይሆን የሚታወቀዉ ፤ በ 1995 «No Mercy» በሚል ያቋቋመዉ የፖፕ ሙዚቃ ቡድንም ተጠቃሽ ነዉ። ፍራንክ ፋርያን ዩኤስ አሜሪካ ማያሚ ባህር ዳርቻ ባለ ቡና ቤት በሙዚቃዉ ድንገት ለተማረከበት ለሙዚቀኛ ማርቲ ሲንትሮን ቆየት ብሎ የዚሁ ሙዚቀኛ ጓደኞች የሆኑትን መንታዮች በጎርጎረሳዉያኑ 1995 ዓ,ም ወደ ጀርመን አምጥቶና ሦስቱን ሙዚቀኞች በጋራ በማጣመር የሙዚቃ ማሳተም ዉልን ፈርሞ «ኖ ሜርሲ » የተሰኘ የሙዚቃ ቡድን መጠርያ እንደሰጣቸዉ ይታወቃል። «ኖ ሜርሲ » የሙዚቃ ቡድን በተለይ «Where Do You Go» በተሰኘዉ ሙዚቃቸዉ በተለያዩ የዓለም ሃገራት በሙዚቃዉ መድረክ የተወዳጅነትና ተደማጭነት መዘርዝር ላይ ለሳምንታት የመጀመርያን ቦታ ይዘዉ ቆይተዋል። በጀርመንና በዩኤስ አሜሪካም ሽልማትን ተቀብለዋል።

በጎርጎረሳዉያኑ 2006 ዓ,ም «ዳዲ ኩል» የተሰኘዉ ፍራንክ ፋርያን ያዘጋጀዉ ሙዚቃዊ ተዉኔት ለመጀመርያ ጊዜ በለንደን ትያትር ቤት ታይቶአል። ሙዚቃዊ ተዉኔቱ በቦንየሞች ሙዚቃ ላይ ብቻ ያተኮረ ሳይሆን ስለ ሚኒ ባኒሊና ኢረብሽን ሰለተባለዉ ባንድም የተዘጋጀ ታሪኩ በተለይ ፍቅር ላይ ያተኮረ በተለይ ደግሞ የራሱ የሙዚቀኛዉን የፍራንክ ፋርያን የሙዚቃ ሕይወት ታሪክ ላይ የሚያዉጠነጥን መሆኑ ተዘግቦአል። 75 ዓመት የሆነዉ ታዋቂዉ ጀርመናዊ የሙዚቃ ደራሲና ቀማሪ ሚኒ ቫኒሊ የሙዚቃ ስራዉን አሁንም አላቋረጠም፤ በመጭዉ የፈረንጆች አዲስ ዓመት አጥብያ አዲስ የሙዚቃ አልበምን ይዞ ለመቅረብ ስራ ላይ መሆኑ ተነግሮለታል። ሙዚቃን ስሰራ ይላል ፍራንክ ፋርያን
« በሙዚቃዎቼ እጅግ ካልተደሰትኩና ካልረካሁ ለኔ ሥራዉ ትክክል አይደለም። ስለዚህም በሥራዬ በመጀመርያ ራሴ የእርካታ ስሜትን ማግኘት ይኖርብኛል እንዳያ ካልሆን አይሆንም። »
ፍራንክ ፋርያን በሙዚቃ ድርሰቱ ከትዉልድ ትዉልድ ስኬታማ የሆነበትን ሚስጥር ሲጠየቅ ትልቅ የሙዚቃ ደራሲም ሆነ አቀናባሪ አይደለሁም ግን የተለያዩ ነገሮችን በማሰባሰብ ጥሩ ገጣጣሚ ነኝ ሲል እንደሚገልፅ ተዘግቦለታል። ጀርመናዊ የሙዚቃ አቀናባሪ የፍራንክ ፋርያን 75ኛ ዓመት በማስመከት ያዘጋጀነዉን ሙሉ ቅንብር የድምፅ ማድመጫዉን ማዕቀፍ በመጫን ይከታተሉ።

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሰ

21.09.2012 DW popXport No Mercy
ፍራንክ ፋርያን የመሰረተዉ የሙዚቃ ቡድን «ሚሊ ቫኒሊ »ምስል 2007 daddy cool · the musical
Deutschland Musik Pop Milli Vanilli
« ኖ ሜርሲ » የተባሉት ፍራንክ ፋርያን የመሰረተዉ
Musical "Daddy Cool"
ምስል picture-alliance/dpa
Frank Farian Musikproduzent wird 75
ጀርመናዊዉ የ«ቦንየሞች» መስራች ፍራንክ ፋርያንምስል picture-alliance/dpa/M.Segieth
50 Jahre Diskothek
ምስል picture-alliance/ dpa