ጀርመኑ የትምህርት ልዉዉጥና ወጣቶች   | ወጣቶች | DW | 30.06.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ወጣቶች

ጀርመኑ የትምህርት ልዉዉጥና ወጣቶች  

ከጀርመን ዓለም አቀፍ የልማትና የተራድኦ ድርጅቶች አንዱ የሆነዉ የጀርመን የትምህርት ነክ ልዉዉጥ አገልግሎት ተቋም ለበርካታ ኢትዮጵያዉያን ወጣቶች የትምህርት እድል በመስጠት ይታወቃል። በዚህ ተቋም  ድጋፍ አግኝተዉ የተማሩና እዚሁ ጀርመን ሀገር በሙያቸዉ  የሚሰሩ ሁለት ወጣቶችን በእንግድነት ጋብዟል፤ የዛሬዉ የወጣቶች ዓለም ዝግጅት።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:14

በቴክኖሎጅና በባህል ሽግግር ረገድ አስተዋጽኦ ያበረክታሉየጀርመን የትምህርት ልዉዉጥ አገልግሎት በምህፃሩ DAAD  ኢትዮጵያን ጨምሮ የበርካታ ታዳጊ ሀገራት ወጣቶች የከፍተኛ ትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ድጋፍ ያደርጋል። ተቋሙ የዉድድር መስፈርቱን አሟልተዉ ለተመረጡ ወጣቶች  ከመጀመሪያ  እስከ ዶክትሬት ዲግሪ  በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች  ጀርመን በሚገኙ የተለያዩ ዩንቨርሲቲወች ገብተዉ እንዲማሩ በገንዘብ ይደግፋል። DAAD በጎርጎሮሳዊው 2015 ብቻ ከ127 ሺህ በላይ ለሆኑ ወጣቶች ድጋፍ አድርጓል።ሥራዉን  ከጀመረበት ከጎርጎሮሳዊዉ 1925 አ/ም አንስቶ  በዓለም ዙሪያ  ለ2 ሚሊዮን ወጣቶች የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል። ባጋመስነዉ  የጎርጎሮሳዊዉ 2017 ብቻ  ከ700 በላይ ለሆኑ ወጣት  ኢትዮጵያዉያን  ድጋፍ ማድረጉም  በድህረ ገጹ ሰፍሯል።
ወጣት ትግስት ካሳ በዚሁ ተቋም የትምህርት ዕድል ካገኙ ወጣቶች አንዷ ናት።ከባህርዳር ዩንቨርሲቲ በሲቭል ምህንድስና የመጀመሪያ ዲግሪዋን አግኝታለች።በጎርጎሮሳዊዉ  2012 አ/ም ባገኘችዉ ነፃ የትምህርት ዕድል ለሁለተኛ ዲግሪዋ ወደ ጀርመን መምጣቷን ገልጻለች።በጅኦቴክኒክ ምህንድስና ሁለተኛ ዲግሪዋን ከሀንፈር ዩንቨርሲቲ  ከያዘችበት ከ 2014 አ/ም ወዲህ ደግሞ እዚሁ ጀርመን ሀገር፤ ላለፉት 4 አመታት በአንድ የግል አማካሪ ድርጅት ዉስጥ እየሰራች ነው።
« ወደ ጀርመን የመጣሁት የማስተርስ ፕሮግራም ለመካፈል ነዉ። ሙሉ ኮርሱ በጀርመንኛ ነበር።ቋንቋዉን ብዙም «ፐርፌክት» ስላልነበርኩ ተቀባይነት አገኛለሁ ብዬ አላስብም ነበር ።ግን ብዙወቹ ነገሮች በተግባር የሚሰሩ መሆናቸዉ  ነዉ  ወደ ስራዉ ዓለም እንድመጣ ያደረገኝ ፤በተግባር ብዙ ነገር የምማር ስለመሰለኝ ነዉ።እናም ትንሽ ሰርቼ ወደ ኢትዮጵያ እመለሳለሁ በሚል ነዉ ወደ ስራ የገባሁት»
ዕድሜዉ በ30 ወቹ መጀመሪያ ላይ እንደሚገኝ የገለፀልን ወጣት ጌታሰዉ መልኬም በጎርጎሮሳዊዉ  2009  አ/ም በዚሁ ተቋም ድጋፍ ከተደረገላቸዉ ወጣቶች አንዱ ነዉ።እዚሁ ጀርመን ሀገር ከሚገኘዉ ባዋስ ዩንቨርሲቲ  በስትራክቸራል ምህንድስና ሁለተኛ  ዲግሪዉን ይዧል።ከዚህ ቀደም አርባ ምንጭ ዩንቨርሲቲ ያስተምር ነበር።ላለፉት 6 አመታት ደግሞ ሁለተኛ ዲግሪዉን በያዘበት ጀርመን፤ በምህንድስና ሙያ ተቀጥሮ እየሰራ ነው።
«የምሰራዉ «አይኩም ኢንተርናሽናል» በተባለ በተለያዩ ዘርፎች በሚሰራ  ዓለም ዓቀፍ ድርጅት ነዉ።በዚህ ድርጅት ዉስጥ  2 ዓመት አልፎኛል።ከዚህ በፊት« አሬቫ »በሚባል መስሪያ ቤት ነዉ።«በኒዉክሌር ፓወር ፕላንት»ማመንጫ ጣቢያወች ዙሪያ ነዉ የሚሰራዉ ከዚህ መስሪያ ቤት ወደ 2 ዓመት ሰርቻለሁ።»
የተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና  የባህል ድርጅት  «ዩኔስኮ » በጎርጎሮሳዊዉ 2010 ባወጣዉ ዘገባ የተማረ የሰዉ ሀይል ፍልሰት በታዳጊ ሀገራት በተለይም በአፍሪካ ከፍተኛ

መሆኑን አትቷል።ከአፍሪካ  ተመራማሪወች ዉስጥም አንድ ሶስተኛወቹ በዉጭ ሀገራት ይገኛሉ።ይህንን ችግር በመገንዘብ ይመስላል የጀርመኑ የትምህርት ልዉዉጥ አገልግሎት(DAAD)   ወጣቶች በሠለጠኑበት ሙያ በሀገራቸዉ እንዲሰሩ ማበረታታት ከአላማወቹ ዉስጥ አንዱ የሆነው። ወጣቱ መሃንዲስ ተምሮ በሀገር ውስጥ በመስራት የሚስማማ ቢሆንም የተማረዉን በተግባር ለመተርጎም እና የተሻለ  ቴክኖሎጅን  በመቅሰም ረገድ ግን በጀርመን  ያገኘዉ ልምድ ቀላል እንዳልሆነ ገልጿል።
ቢሆንም  በእርግጠኝነት አንድ ነገር ይናገራል በጀርመን የተማረዉን ሙያና በተግባር ያገኜዉን ልምድ ይዞ  ወደ ሀገሩ እንደሚመለስ።ትዕግስትም ብትሆን በሀሳቡ ትስማማለች ። ጀርመን ለመስራት ስትወስን ልምድ መቅሰም  ምክንያቷ ነበርና።
ለመሆኑ በወጣትነት ዕድሜ ከቤተሰብ ተለይቶ በማያዉቁት  ባህልና  ቋንቋ  መስራት ምን ይመስላል? ለሁለቱም ወጣቶች የቀረበ ጥያቄ ነበር።
በማያዉቁት ባህል፣ ቋንቋና ማህበረሰብ ዉስጥ ሆኖ መስራት የሚያጋጥመዉ ፈተና ቀላል ባይሆንም፤  ከዚህ ባሻገር ግን ከጀርመኖቹ የተማርናቸዉ ብዙ ነገሮች አሉ።  የሁለቱም ወጣቶች መልስ ነበር።
በቴክኖሎጅ ሽግግርና በባህል ልዉዉጥ ረገድ ጀርመን የተማሩና የሰሩ ኢትዮጵያዉያን የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ቀላል ባይሆንም ኢትዮጵያዉያኑ የስራ ልምድና  ሙያ ይዘዉ ወደ ሀገራቸዉ ሲመለሱ እነሱን የሚያሰባስብና አካልና አሰራር አለመኖር በአንዳንዶች ዘንድ አሁንም ድረስ በችግርነት ይጠቀሳል።የጀርመኑ የቴክኒክ ተራድኦ ድርጅት ጅ አይ ዜድ ሰሙኑን ጀርመን ለተማሩና ለሰሩ እትዮጵያዉያን ባለሙያወች በአዲስ አበባ ከተማ ባዘጋጀዉ አዉደ ጥናት በተሳታፊነት  የተገኙት ዶክተር ደረጀ  ፈይሳ ችግሩን ይጋሩታል።
« እኔ ብዙ ጌዜ የሰራሁትና ረጅም ልምድ ያለኝ ጀርመን ሀገር ነዉ።ግን ወደ ኢትዮጵያ ስመለስ ከጀርመን ተቋማት ጋር ግንኙነት አልነበረኝም። ጀርመን እንደመስራታችንና እንደ መማራችን በሁለቱ ሀገራት መካከል መቀራረብ መፍጠር ስንችልና የባህልም ፣የትምህርትም፣ከስራም አኳያ የባህል አምባሳደር መሆን ስንችል አለመሆኑ ትንሽ ቅር ይለኛል።ለዚህ ነዉ እዚህ ስብሰባ ስጠራ ቶሎ የመጣሁት።»
ወጣት ኢትዮጵያዊ ባለሙያዎች በጀርመንም ይስሩ በኢትዮጵያ ፤ህዝብንና ሀገርን ማገልገል ቅድሚያ የሚሰጡት አላማ ከሆነ፤ መልካም ነዉ የሚሉም ጥቂቶች አይደሉም።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን ያዳምጡ።
 

ፀሐይ ጫኔ 

ነጋሽ መሀመድ

 

Audios and videos on the topic