ዶ/ር አቢይ እና «እስረኞቹ ይፈቱ» | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 06.04.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዶ/ር አቢይ እና «እስረኞቹ ይፈቱ»

ኢሕአዴግ አዲስ ስለሾማቸው ጠቅላይ ሚንሥትር ዶ/ር አቢይ አኅመድ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚሰጡ አስተያየቶች እንደቀጠሉ ናቸው።  የታሰሩ ይፈቱ ጥያቄም በሳምንቱ ተስተጋብቷል።  በዳግማዊ ዓጼ ቴዎድሮስ ዘመነ-መንግሥት ከመቅደላ አምባ በብሪታንያውያን የተመዘበሩት የሀገር ቅርሶች ጉዳይም ሌላኛው ርእስ ነበር።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:06

የዶ/ር አቢይ ንግግር፣ «እስረኞች ይፈቱ»ና የኢትዮጵያ ቅርሶች በብሪታንያ

ገዢው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) በቀድሞው ጠቅላይ ሚንሥትር ምትክ አዲስ የሾማቸው ጠቅላይ ሚንሥትር ዶ/ር አቢይ አኅመድ ማንነት እና የበዓለ-ሢመት ንግግር የበርካቶች መነጋገሪያ ኾኖ ቆይቷል። በሣምንቱ ሌላው የመነጋገሪያ ርእስ ኾኖ የዘለቀው ጠቅላይ ሚንሥትሩ ከመሾማቸው ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ስለ ታሠሩ ሰዎች የሚስተጋባው ጥያቄ ነው። 

ሰኞ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ዶ/ር አብይ አኅመድ ጠቅላይ ሚንሥትር ኾነው በምክር ቤት መሠየማቸው የማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች አብይ መነጋገሪያ ኾኗል። ድጋፍ እና ተቃውሞም ተስተጋብቷል። ድጋፋቸውን የሰጡ ሰዎች ዶ/ር አብይ የሕዝብ ትግል ውጤት ያመጣቸው ናቸው ወደ ፊትም ጥሩ ነገር ያመጣሉ ሲሉ መልካም ተመኝተዋል።

ሌሎች በተቃራኒው ኢሕአዴግ የሰየማቸው የኢሕአዴግ ሰው በመኾናቸው ነገሩ ሁሉ «ስልቻ ቀልቀሎ፣ ቀልቀሎ ስልቻ ነው» ሲሉ ብዙም ቁብ እንዳልሰጣቸው ተናግረዋል። «የአንድ ፓርቲ የበላይነት ያስተነገደዉ የሥልጣን ሸግግር እንጂ የመንግሥትን ሕግ የሚቀይር የሥልጣን ሽግግር አየደለም» ያሉት ሁሴን አክመል ናቸው በፌስቡክ መልእክታቸው።

ከትችት እና ተቃውሞ በፊት ጊዜ ያስፈልጋቸዋል ሲሉም አስተያየት የሰጡ አሉ። «ከመቸው ለወቀሳ በቃችሁ፤ አይ ያገሬ ሰው እንደው ምን ይሻላችሁ ይሆን?» በማኅደር ከበደ የቀረበ የፌስቡክ መልእክት ነው። ቃለአብ ኢዮብ በበኩላቸው፦«በአንድ ቀንና ባንድ ለሊት እሚሞላ ነገር የለም ሁሉም በትእግስት ሲጠብቅ ሊሞላ ይችላል» ብለዋል በፌስቡክ።

ጊዜ መስጠቱ ግን እስከመቼ እንደሆነ እሸቱ ሆማ ቄኖ በትዊተሩ ጠይቋል። «አንዳንድ ወዳጆቻችን ምክንያት ጊዜ ስጡትን ወደ ምክንያት አላሠራ አሉት እስኪቀይሩት ድረስ ደስታቸውን ላለማደፍረስ ቀን መቁጠር ያቆምን መሆኑን እንገልፃለን» በማለት።

 

ድጋፋቸውን ከሰጡት መካከል፦ አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ ትዊተር ላይ የሚከተለውን ጽፈዋል።  «ኢትዮጵያ ሰላማዊ በኾነ በሰለጠነ መንገድ ከአንዱ ጠቅላይ ሚንሥትር ወደሌላኛው የሥልጣን ሽግግርን አስመስክራለች» ሲሉ።

ምሥጋና ያለው በተቃራኒው ቀጣዩን አስፍረዋል፦ «ምንም የሐሳብ መጠነኛ ልዩነት ቢኖርም ከወያኔ ወደ ወያኔ እንዴት የሥልጣን ሽግግር ይባላል?» ሲሉም ጠይቀዋል።

የዶ/ር አብይ ጠቅላይ ሚንሥትር መኾንን ከስኬት ጋር ያዛመዱም አልታጡም። ብሩክ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ፦ «የኢንተርኔት አገልግሎቱ ዛሬ ጥሩ በመኾኑ በርካታ ሥራዎችን በጊዜ ለመከወን ችያለሁ» ሲሉ ዶ/ር አብይን አመስግነዋል።  ‏

ሉሲ በሚል ቅጽል የሚጠራው የኢትዮጵያ የሴቶች ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን የሊቢያ አቻውን ሰሞኑን ስምንት ለዜሮ ማሸነፉን በተመለከተ አዱኛ የተባሉ ግለሰብ፦ «ዶ/ር አብይ በእግር ኳዋሱም ለዉጥ አመጣለዉ ብለዋል እንዴ ?» ሲሉ ጽፈዋል።

«የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ንግግር እጅግ አርኪ እና ብዙዎችን የማረከ ነው ብዬ እገምታለሁ። እጅግ ብዙ ሥራ ይጠብቃቸዋል፤ ሆኖም ህዝቡን ከጎናቸው ማሰለፍ ከቻሉ ብዙ ለውጥ ሊየመጡ ይችላሉ። ችግሩ ሕዝቡ ሳይሆን ኢህአዴግ ነው። ትግሉ በተለይ ለውጥ ፈላጊ በሆኑና ለውጥን በሚገዳደሩ ወገኖች መካከል ነው።» በኋትስአፕ የደረሰን መልእክት ነው። ተጨማሪ በዋትስአፕ የደረሱንን የድምፅ መልእክቶች እናስከትል።

‏የዶ/ር አብይ ጠቅላይ ሚንሥትር የመኾናቸው ዜና ለጊዜው ጋርዶት የነበረው ጥያቄ ዳግም ማስተጋባት ጀምሯል «የታሠሩ እስረኞች ይፈቱ» በሚል።

የእስረኞች በተደጋጋሚ መታሰር እና መፈታት ዜና ያሬድ ለገሰን ያታከተው ይመስላል። «ተፈቱ፤ ታሰሩ፤ ተፈቱ፤ ታሰሩ፤ ተፈቱ፤ ታሰሩ......ኡፍፍፍፍ» በማለት ነው የትዊተር መልእክቱ የሚንደረደረው። ያሬድ በመቀጠል፦ «በሆነ ባልሆነው ማሰር የማይሰለቸው መንግሥት፤ በሆነ ባልሆነው መታሰር የማይሰለቸው "ነጻ አውጭ"...ሁለቱም ይኸ ነገር በጣም ነው የሚመቻቸው፤ በመሀል እኛ ተሰቃየን» ብሏል።

ሶሊያና ለያሬድ በሰጠችው መልስ እንዲህ ብላለች፦  «አንተ በዜና ተሰቃይተህ ሌላው ሰው ቶርቸር እንደሚመቸው ካሰብክ ለምን ታስረህ አትሞክረውም?  በወሬ ከምትሰቃይ አማራጭ ይሆናል» ብላለች።

«እስራቸው በቀላሉ እና ያለብዙ ቢሮክራሲ ነበር» ያለችው ሲያኔ አንለይ፦ «ሰዎችን ማሰር ከመፍታት በላይ የቀለለባት ሀገር» ስትል ጽፋለች። ባሕርዳር ውስጥ ለ12 ቀናት ታስረው የቆዩት  19 ሰዎች መፈታታቸውንም የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች ጠቅሰዋል።

‏እዛው ትዊተር ላይ አብዱረሂም በእስር ቤት ውስጥ ፖሊሶች የታሳሪዎች ንግግርን ጭምር እንደሚቆጣጠሩ የሚገልጽ ጽሑፍ አስፍሯል። «እነ ስዩም ተሾመ በታሰሩበት ቦታ ከጠያቂዎች ጋር አይዳ ስለተባለች ታሳሪ ሲያወሩ ፖሊሱ ጣልቃ ገብቶ ስለ idea (ሃሳብ) ማውራት አትችሉም አለ አሉ» ሲል ይነበባል። አይዳ የሚለውን ስም በእንግሊዝኛ ቃል አይዲያ ወይንም ሐሳብ መባሉንም «የጉድ ሀገር» ሲል ገልጦታል።

የአብዱረሂም የትዊተር መልእክትን በመውሰድ የራሱን ያከለበት ዘላለም ክብረት በበኩሉ በሳቅ ምልክት ጽሑፉን ይጀምራል። «እኔም አንድ መርማሪ ‘East Africa Branch’ የሚል ማስታዎሻ ላይ የተገኝ ሐረግን " 'የኢሳት የአፍሪካ ቅርንጫፍ' ለማለት ነው። ማን እንደሚመራው ንገረኝ?" ብሎኝ ነበር።» በማለት ጽፏል።

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና ተመስገን ደሳለኝን ጨምሮ የታሰሩ 11 ግለሰቦች መፈታታቸውን ትናንት በትዊተር ገጹ «ተፈቱ» በሚል አጭር ጽሑፍ ይፋ ያደረገው ጋዜጠኛ በላይ ማናዬ ነው። ይኽንኑ ለዶይቸ ቬለ በስልክ አረጋግጧል። 

ምናልባትም በበርካታ ኢትዮጵያውያን የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች ዘንድ ለጊዜው እምብዛም ትኩረት የሳበ አይደለም። ኾኖም ጉዳዩ በሺህዎች በሚቆጠሩ የውጭ ሃገር ነዋሪዎች ዘንድ አነጋግሯል። በዳግማዊ ዓጼ ቴዎድሮስ ዘመነ-መንግሥት ከመቅደላ አምባ በብሪታንያውያን የተመዘበሩት የሀገር ቅርሶች 150 ዓመታት ቢያስቆጥሩም ዛሬም ድረስ የብሪታንያ ቤተ-መዝክሮችን አድምቀው የገቢ ምንጭ ኾነዋል። ሰሞኑን ታዲያ የብሪታንያው ዘ ጋርዲያን ጋዜጣ እነዚህ የተዘረፉ የኢትዮጵያ ሐብቶች በተመለከተ ያወጣው መልእክት እጅግ አስደማሚ ነው። እንዲህ ይነበባል የጋዜጣው ርእስ፦ «ብሪታንያ የሚገኙ የተመዘበሩ የኢትዮጵያ ቅርሶች በረዥም ጊዜ ውሰት ሊመለሱ ይችላሉ»። የቪክቶቲያ እና አልበርት ቤተ-መዘክር ዳይሬክተር ቅርሶቹ በረዥም ውሰት አፍሪቃ እንዲመለሱ ይፈልጋሉ ይላል የጋዜጣው መልእክት አክሎ።

ከአምስት ሺህ በላይ ሰዎች የወደዱት ከኹለት ሺህ አምስት መቶ በላይ ተጠቃሚዎች የተቀባበሉት ኢ ቶንግ በተባለ የትዊተር ተጠቃሚ የቀረበ የእንግሊዝኛ መልእክት በአንጻሩ እንዲህ ይላል። «ሄይ ጋርዲያን፤ ርእሳችሁን እኔ አስተካክዬላችኋለሁ» በማለትም ይንደረደራል። የኢቶንግ መልእክት ዘጋርዲያን ርእስ ላይ የሚገኙ ቃላትን በመቀየር የቀረበ ነው። ኢቶንግ ጋዜጣው የተጠቀመውን ርእስ በማሻሻልም የሚከተለውን ጽፏል።«ብሪታንያ የሚገኙ የተመዘበሩ የኢትዮጵያ ቅርሶች በፍላጎት ሊመለሱ ይገባል» ይላል።  ይኽን የትዊተር መልእክት በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተቀባብለውታል።

በብሪታንያ የተዘረፈው የኢትዮጵያ ቅርስ ጉዳይን በተመለከተ ሜጋህና በሚል የትዊተር ስም የቀረበ ጽሑፍ እንዲህ ይሳለቃል፦ «የሚያስቀው ነገር፤ ብሪታንያ ለኢትዮጵያ የተዘረፈችውን ቅርሶቿን ለመስጠት ማቅረቧ ነው፤ በውሰት» በሚል።

«ብሪታንያ ከኢትዮጵያ ለሰረቀችው ቅርስ ካሳ መክፈል አለባት እናም ሁሉንም ከይቅርታ ጋር መመለስ» ያለው ደግሞ ሳሌህ ነው።

‏በነገራችን ላይ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1868 ዓጼ ቴዎድሮስ ያሰሩዋቸውን አውሮጳውያን ለማስፈታት ብሪታንያ የላከችው ጦር እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ ያስወጣ በልዩ ኹኔታም በጥንቃቄ የተዘጋጀ ነበር። 13,00 ዘመናዊ ጦር እና 40,000 እንስሳትን ያካተተው የብሪታንያ ዘማች የተመራው በሌውተናንት ጄኔራል ኋላ ላይ ፊልድ ማርሻል ሮበርት ናፒየር ነበር። መድፎችን እና ግዙፍ ጦር መሣሪያዎችን ለመሸከም የሰለጠኑ 44 ዝኆኖችም በዘመቻው ተሳትፈዋል። ዝኆኖቹ ዓጼ ቴዎድሮስ ራሳቸውን ካጠፉ በኋላ በመቅደላ አምባ የተመዘበሩትን የሐብት ክምችቶች ጭነው ተመልሰዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ 

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic