ዶ/ር መረራ የመሰረቱት ክስ አንደምታ | አፍሪቃ | DW | 18.07.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ዶ/ር መረራ የመሰረቱት ክስ አንደምታ

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተላልፈዋል፣ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ ተንቀሳቅሰዋል ተብለው በእስር ላይ የሚገኙት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ባለፈው ሳምንት ክስ መስርተዋል፡፡ ዶ/ር መረራ ክሱን የመሰረቱት በአፍሪካ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መድረክ ነው፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:32

የኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጫና ለማድረግ ይረዳል ተብሏል

ዶ/ር መረራ በተወካያቸው አማካኝነት ክሱን የመሰረቱት በሶስት ፍሬ ነገሮች ላይ አትኩረው ነው፡፡ የመጀመሪያው ፍሬ ነገር የቀረበባቸው ክስ እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸው የአፍሪካ ቻርተርና ከሌሎችም ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች ጋር የሚጋጭ እንደዚሁም የኢትዮጵያ ህገ መንግስት መስፈርቶችን የሚያሟላ አይደለም የሚል ነው፡፡ በእስር ከዋሉ ጀምሮ የተፈጸመባቸው ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ ሌላው የክስ ጭብጥ ነው፡፡ ሶስተኛው ፍሬ ነገር ደግሞ በኦሮምያ በአማራ እና በደቡብ ክልሎች ተነስተው በነበሩ ህዝባዊ አመጾች የመንግስት ታጣዊዎች በዜጎች ላይ የወሰዱት አላስፈላጊ የኃይል እርምጃ በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ የሚጠይቅ ነው፡፡

የዶ/ር መረራን ውክልና በመውሰድ ክሱን የመሰረተው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ እና የዲሞክራሲያዊ መብቶች ማዕከል ኃላፊ ዶ/ር አዎል አሎ ለዶይቸ ቬለ እንደገለጹት የአፍሪካ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ክሱን ለመመስረት ተገቢ ቦታ ነው፡፡ ዶ/ር አዎል “ከኢትዮጵያ ጋር በተያያዘ ልንሄድ የምንችልባቸው ብዙ መድረኮች አልነበሩም” ይላሉ፡፡

“የተባበሩት መንግስታት ውስጥ የተወሰኑ መድረኮች አሉ፡፡ እነዚህ መድረኮች ግን የአፍሪካ ኮሚሽን ከሚሰጠው አማራጭ ጋር ሲታይ የተሻሉ አይደሉም፡፡ ይህ ጉዳይ ከሚያነሳቸው ፍሬ ነገሮች ጋር በተያያዘ ስናይ የአፍሪካ ኮሚሽን የተሻለ ዕድል ይሰጣል፡፡ የአፍሪካ ኮሚሽንን ኢትዮጵያ በተወሰነ ደረጃ በቁም ነገር እንደምትወስደም የምናያቸው አንዳንድ ነገሮች አሉ፡፡ ምክንያቱም ሀገሪቷ በአፍሪካ ህብረት ውስጥ ማንጻባረቅ የምትፈልገው ምስል አለ፡፡ ከዚያም አንጻር ሊሆን ይችላል ቢያንስ ከሱ በሚቀርብበት ጊዜ መልስ የመስጠት እና ከኮሚሽኑ ጋር የመስራት የቀደሙ ተሞክሮዎች አሉ፡፡ ኮሚሽኑ አነዚህን ጉዳዮች ፍርድ ቤቶች ጉዳዮች በሚመለከቱበት መልኩ መርምሮ ነው ውሳኔ ላይ የሚደርሰው” ይላሉ ዶ/ር አዎል፡፡

ክሱን መመስረቱ እና በቀጣይ የሚገኘው ውሳኔ ሊሰጠው የሚችለውን ጠቀሜታ በተመለከተ የተጠየቁት ዶ/ር አዎል ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ “ይህ የክስ መዝገብ የሚያደርገው አንድ ነገር የታሰሩ ሰዎች ጉዳያቸው እንዳይረሳ ያደርጋል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ የክስ ሂደቱ የራሱ ደረጃዎች አሉት፡፡ እዚያ ደረጃዎች ላይ በሚደርስበት ጊዜ የእነዚህ ሰዎች ስም የመታወስ ዕድል ይኖረዋል፡፡ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች እዚህ ላይ ተመስርተው የዲፕሎማሲ ስራ መስራት ይችላሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጫና ለማድረግ ዕድል ይሰጣል፡፡ ስለዚህ ከህግ ሂደቱ ያለፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው፡፡ ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ማለት ነው” ሲሉ የክሱን አንደምታ ይዘረዝራሉ፡፡

የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ፕሮጀክት አስተባባሪ ሶልያና ሽመልስ መሰል ክሶች በአህጉራዊ እና ዓለምአቀፋዊ መድረኮች መመስረታቸው በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ ለሚሰሩ የቅስቀሳ ስራዎች የጎላ ሚላ እንደሚኖራቸው ታሰምርበታለች፡፡ “ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ለዓለም አቀፍ ተቋማት ማሳየት ይቻላል፡፡ እንደዚያ ለማሳየት ሰብዓዊ መብት  ተቋማት የተለያዩ መንገዶችን እንጠቀማለን፡፡ አንደኛው መገናኛ ብዙሃንን [መጠቀም] ሊሆን ይችላል ሌላኛው ደግሞ እንዲዚህ ዓይነት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት መድረኮች በመጠቀም ሀገሪቱ ውስጥ ያለውን የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ማሳየት ይቻላል፡፡ የዶ/ር መረራ ጉዳይ እንደ አንድ ማሳያ ሆኖ ለሌሎች ሀገሪቷ ውስጥ ላሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መገለጫ ሊሆን ይችላል ተብሎ ስለሚታሰብ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ግንዛቤ ስለሚጨምር አንደኛው ጥቅሙ እርሱ ነው፡፡”

“ሁለተኛው ደግሞ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት እንቅስቃሴዎች በተለይ የዓለም አቀፍ ቅስቀሳ በሚሰራበት ቦታ ላይ ሀገር ቤት ያለውን የመንግስት ጭቆና [ለማሳየት ይረዳል]፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ መንግስት የሚሰራቸው የህዝብ ግንኙነት ስራዎች አሉ፡፡ ‘የሰብዓዊ መብት ዘገባዎች ትክክል አይደሉም፣ የሚባሉት ዘገባዎች የሚወጡባቸው ተቋማት ራሳቸው የነጮች ናቸው፣ ርዕዮተ ዓለማዊ ምክንያት አላቸው’ የሚለውንም የመንግስት ክርክር ለማፍረስ ይረዳል” ስትል ታብራራለች፡፡

የአፍሪካ የሰብዓዊ እና የህዝቦች መብት ኮሚሽን በአፍሪካ ቻርተር አማካኝነት እንደጎርጎሮሳዊው 1987 በአዲስ አበባ የተመሰረተ እና መቀመጫውን ጋምቢያ መዲና ባንጁል ያደረገ አህጉራዊ ተቋም ነው፡      

 

አክመል ነጋሽ 

ተስፋለም ወልደየስ

አዜብ ታደሰ         

Audios and videos on the topic