ዶክተር ፍቅሩ ማሩና አግባው ሰጠኝን ጨምሮ እስረኞች ተፈቱ | ኢትዮጵያ | DW | 15.05.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

ዶክተር ፍቅሩ ማሩና አግባው ሰጠኝን ጨምሮ እስረኞች ተፈቱ

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የቀረበባቸውን ክስ ካቋረጠላቸው መካከል በዛሬው ዕለት አምስት ሰዎች ከእስር ተለቀዋል። ከእስር ከተፈቱት መካከል የልብ ሕክምና ባለሙያው ዶክተር ፍቅሩ ማሩ እና አግባው ሰጠኝ ይገኙበታል። የጥብቅና ባለሙያዎች ከአራት ተከሳሾች በቀር ሌሎች ደንበኞቻቸው ይፈታሉ የሚል ተስፋ አሳድረዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:21

"ከፍተኛ የሆነ ስቃይ ደርሶብናል" አቶ አግባው ሰጠኝ

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የቀረበባቸውን ክስ ካቋረጠላቸው መካከል በዛሬው ዕለት አምስት ሰዎች ከእስር ተለቀዋል። ከእስር የተፈቱት የልብ ሕክምና ባለሙያው ዶክተር ፍቅሩ ማሩ እና አግባው ሰጠኝ፤ ሲሳይ ባቱ እና ከበደ ጨመዳ በአንድ የክስ መዝገብ የተከሰሱ ነበሩ ናቸው። ዛሬ ከተለቀቁት መካከል ፋሲል አለማየሁ የሚባሉ አምስተኛ እስረኛ ይገኛሉ።

የፌድራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ግንቦት 3 ቀን 2010 ዓ.ም. ዶክተር ፍቅሩ ማሩ እና አቶ አግባው ሰጠኝን ጨምሮ በ62 ኢትዮጵያውያን ላይ ያቀረበውን ክስ ማንሳቱን አስታውቋል። ከእነዚህ መካከል አምስቱ በኢትዮጵያ የእስልምና እምነት ተከታዮች እንቅስቃሴ ወቅት ታስረው የነበሩ ናቸው። ጠበቃ ሰዒድ አብዱራሕማን የአምስቱ ደንበኞቻቸው መፈቻ ለማረሚያ ቤት መድረሱን ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል። እስከ ትናንት ቂሊንጦ የነበሩት አምስቱ ተከሳሾች ወደ ቃሊቲ ተዘዋውረው እንደሚፈቱ እንደተነገራቸው ጠበቃ ሰዒድ አስረድተዋል።

ጠበቃ ወንድሙ ኢብሳ በበኩላቸው ወደ 34 ገደማ ደንበኞቻቸው እንደሚፈቱ ተስፋ አድርገዋል። ጠበቃ ወንድሙ "እኔ ከያዝኳቸው ጉዳዮች አራቱ ልጆች በነፍስ ጉዳይ እንዲከላከሉ ከተደረጉት ውጪ 34ቱም ዛሬ፤ ነገ ከፍ ሲል እስከ ረቡዕ ድረስ ይለቀቃሉ ብዬ አምናለሁ" ሲሉ ተናግረዋል።

የልብ ሕክምና ባለሙያው ዶክተር ፍቅሩ ማሩ በዛሬው ዕለት ለስዊድን የቴሌቭዥን ጣቢያ በስልክ በሰጡት አጭር አስተያየት ከእስር በመፈታታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው አገሬ ወደሚሏት ስዊድን ለመመለስ ማሰባቸውን ተናግረዋል። የሙስናና የሽብር ክሶች ቀርበውባቸው ለአምስት አመታት በእስር የቆዩት ዶክተር ፍቅሩ ዛሬዉኑ ወደ ስዊድን ኤምባሲ ተጉዘዋል።

በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት ስዊድናዊው ዶክተር ፍቅሩ ማሩ "የኦነግ፣ የግንቦት ሰባት እና የአል-ሸባብ የሽብር ቡድን ዓላማ በመቀበል" የሽብር ወንጀል ፈፅመዋል በሚል ኅዳር 13 ቀን 2009 ዓ.ም ክስ ከቀረበባቸው መካከል ናቸው። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በእነ ማስረሻ ሰጤ የክስ መዝገብ የተካተቱ 38 ግለሰቦችን ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም. በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ለተነሳው ቃጠሎ ተጠያቂ አድርጓቸዋል። ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ተከሳሾቹ "23 የሚሆኑ ታራሚዎች በከባድ ሁኔታ ተደብድበው በእሳት እንዲቃጠሉ እና ሕይወታቸው እንዲያልፍ" አድርገዋል ብሎ ነበር።

መቀመጫውን ከኢትዮጵያ ውጪ ላደረገው የኢሳት ቴሌቭዥን በሰጡት ቃለ-መጠይቅ ሳቢያ ተከሰው እስር ቤት የነበሩት አቶ አግባው "ቂሊንጦ ሲቃጠል እኔ ከጭለማ ቤት ወጥቼ ዞን አንድ የሚባለው ማረፊያ ቤት ነበርኩ" ሲሉ ይናገራሉ። በቂሊንጦ የተነሳው የእሳት ቃጠሎ በማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ጥፋት እንደሆነ የሚናገሩት አቶ አግባው " እኛን በማናውቀው አላችሁበት ብለው እነ ዶክተር ፍቅሩን፣ እነ መቶ አለቃ ማስረሻን ከሌሉበት ማግለያ ቤት ወይም ጨለማ ቤት አውጥተው  በሸዋሮቢት ምርመራ ጣቢያ ብለው ከፍተው ከፍተኛ የሆነ ስቃይ አደረሱብን፤ ሰብዓዊ ክብራችን ሞራላችንን የሚነካ ነገር" እንደተፈጸመባቸው አስረድተዋል። አቶ አግባው ተፈፅሞብናል የሚሉት ድብደባ እና ሥቃይ በሸዋሮቢት እና በዝዋይ በሚገኙ የማረሚያ ቤቶች ጭምር ነው።

በቂሊንጦ ማረሚያ ቃጠሎ ሰበብ በተመሳሳይ የክስ መዝገብ የተከሰሱት መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ እና ፍቅረ ማርያም አስማማው አሁንም እስር ላይ ናቸው። አቶ አግባው እንደሚሉት መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤን ጨምሮ በርካታ ተከሳሾች አሁንም ጭለማ ቤት ይገኛሉ።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ

 

Audios and videos on the topic