ዶክተር ግርማ ቀልቦሮ በ«ZEF» ከፍተኛ ተመራማሪ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 20.02.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

ዶክተር ግርማ ቀልቦሮ በ«ZEF» ከፍተኛ ተመራማሪ

በደቡብ ክልል በአንዲት ትንሽ የገጠር መንደር ከአርሶ አደር ቤተሰብ ለተወለዱት ለዶክተር ግርማ አሁን ምርምር የሚያካሂዱበት የተፈጥሮ ሀብት አያያዝ፣የብዝሀ ህይወት እና የምግብ ዋስትና ጉዳዮች ሩቅ አይደሉም። ይሁንና በዚህ ሙያ የመሰማራት ፍላጎቱ ያደረባቸው ግን በስተመጨረሻ ላይ ነበር።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:46

ከፍተኛ ተመራማሪው ዶክተር ግርማ

በጀርመንኛው ምህጻር «ZEF» የተባለው በጀርመኑ የቦን ዩኒቨርስቲ ስር የሚገኝ «የልማት ምርምር ተቋም» ከልማት ጋር ለተያያዙ ጥያቄዎች ሳይንሳዊ መፍትሄ ለመፈለግ የዛሬ 22 ዓመት የተመሰረተ የምርምር ተቋም ነው። በማደግ ላይ ካሉ ሀገራት የምርምር ማዕከላት ምሁራን እና ሳይንቲስቶች ጋር በትብብር ከሚሰራው ከዚህ ተቋም ተግባራት ውስጥ ተማሪዎችን ከመላው ዓለም መልምሎ የሚያስተምርበት የዶክትሬት ዲግሪ መርሃግብር አንዱ ነው። በምዕራብ ጀርመንዋ ከተማ ቦን ከሚገኘው ከዚህ ተቋም ሠራተኞች ገሚስ ያህሉ ከተለያዩ ሀገራት የተመለመሉ ናቸው። ከመካከላቸው ዛሬ የምናስተዋውቃችሁ ኢትዮጵያዊ ሳይንቲስት ይገኙበታል።

ዶክተር ግርማ ቀልቦሮ ይባላሉ። በጥናት እና ምርምር ተቋሙ «ZEF»  ከፍተኛ ተመራማሪ ናቸው። የተፈጥሮ ሀብት አያያዝ፣ ብዝሀ ህይወት፣ ዘላቂ ልማት፣ የምግብ ዋስት፣ የህብረተሰቡ ባህላዊ እውቀት ምርምር ካካሄዱባቸው ጉዳዮች ውስጥ ይካተታሉ። ዶክተር ግርማ የዛሬ 10 ዓመት ነበር ለዶክትሬት ዲግሪ ትምሕርታቸው ጀርመን የመጡት። አራቱን ዓመት እዚያው «ZEF» 

ለዶክትሬት ዲግሪያቸው ምርምር በማካሄድ አሳለፉ። ትምሕርታቸውን እንደጨረሱም  ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ተዘጋጅተው የነበረ ቢሆንም ያኔ የገጠማቸው ሌላ እድል ግን እቅዳቸውን አስቀየራቸው።

የዶክተር ግርማ የዶክትሬት ዲግሪ መመረቂያ ጥናት ለብዝሀ ህይወት ጥበቃ በሚከለሉ አካባቢዎች የህብረተሰቡ ፍላጎት እና የምግብ ዋስትና ጥያቄ ፣ ከጥበቃው የሚያገኘው ጥቅም እንዲሁም ለዘላቂ ልማት እና ጥበቃ መከናወን ያለባቸው ተግባራት ላይ ያተኮረ ነበር ። ከዚያ በቀጠለው የድህረ ዶክትሬት ጥናታቸው ደግሞ ህብረተሰቡ ስለ ምግብ ዋስትና ያለው ባህላዊ እውቀት እንዲሁም የህብረተሰቡን እውቀት ከሳይንሳዊው እውቀት ጋር በማጣመር ለውጥ ማምጣት ይቻላል ወይ የሚሉ ጥያቄዎችን ያነሳ ነበር። በደቡብ ክልል በአንዲት ትንሽ የገጠር መንደር ከአርሶ አደር ቤተሰብ ለተወለዱት ለዶክተር ግርማ አሁን ምርምር የሚያካሂዱበት የተፈጥሮ ሀብት አያያዝ የብዝሀ ህይወት እና  የምግብ ዋስትና ጉዳዮች ሩቅ አይደሉም። ይሁንና በዚህ ሙያ የመሰማራት ፍላጎቱ ያደረባቸው ግን በስተመጨረሻ ላይ ነበር።

በያኔው አጠራር ከአለማያ ዩኒቨርስቲ በደን ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸው ካገኙ በኋላም በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስር በሚገኘው የወንዶገነት የደን ሳይንስ ኮሌጅ ለ7 ዓመት በደን ሳይንስ መምህርነት አገልግለዋል። ሆላንድ ያገኙት ሁለተኛ ዲግሪያቸው ደግሞ ፣ሞቃታማ አካባቢ ደን ላይ ያተኮረ ነበር።ዶክተር ግርማ እንደሚሉት የልማት ጉዳዮችን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ከሚካሄዱ ምርምሮች አባዛኛዎቹ  ተግባር ላይ ሳይውሉ ለዓመታት ይቀመጣሉ ። ይህ የገንዘብ ጊዜ እና የእውቀት ብክነት በአሁኑ ጊዜ እንደ ዶክተር ግርማን የመሳሰሉ ተመራማሪዎችን የሚያሳስብ ጉዳይ ሆኗል። የምርምር ውጤቶች ሳይተገበሩ የቤተ መጻህፍት መደርደሪያ ማድመቂያ ሆነው እንዳይቀሩ አሁን አሁን ተመራማሪዎች እየተነጋገሩበት ያለ ጉዳይ መሆኑን ዶክተር ግርማ ይናገራሉ።  

ጀርመን ውስጥ ፣ከህብረተሰቡ ጋር ተቀራርቦ እና ተዋህዶ ለመኖር አስፈላጊ የሆነውን የጀርመንኛ ቋንቋ ለመማር እና ለመረዳት ብዙ ጥረት ማድረጋቸውን ይናገራሉ ዶክተር ግርማ። ቋንቋው ከብዶኝ ነበርም ይላሉ። ከዚህ ሌላ ለአገሩ እንግዳ ለሰዉ ባዳ በነበሩባቸው በመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ከህብረተሰቡ ባህርይ በጣም ያስገረማቸውም ነበር ።

ከጎርጎሮሳዊው 2013 ዓም አንስቶ በ«ZEF» ከፍተኛ ተመራማሪ እና መምህር ዶክተር ግርማ በቦን ዩኒቨርስቲ እና በአቅራቢያዋ በሚገኘው በቦን ራይንዚግ ዩኚቨርስቲም ያስተምራሉ።  ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት ዶክተር ግርማ ቤተሰባዊ ሃላፊነታቸውን እና ሥራቸውን አጣጥመው ለማስኬድ እንደሚጥሩም ይናገራሉ። 

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic