ዶክተር ካሬላ ኢሽዋራን | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 20.03.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

ዶክተር ካሬላ ኢሽዋራን

ዶክተር ካሬላ የህጻናት ህክምና ባጠኑበት በጀርመን የራሳቸውን ክሊኒክ ከፍተው አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ 20 ዓመታት ተቆጥረዋል። ክሊኒካቸው በምዕራብ ጀርመንዋ በኮሎኝ ፣ ሱልዝ በተባለው ደቡብ ምዕራብ የከተማይቱ ክፍል ውስጥ ነው የሚገኘው ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:13

ዶክተር ካሬላ ኢሽዋራን

ዶክተር ካሬላ ኢሽዋራን ጀርመን ሲኖሩ 30 ዓመታት ተቆጥረዋል። የህጻናት ጀርመን ከመምጣታቸው በፊት ከኢትዮጵያ የነጻ ትምህርት እድል አግኝተው በሄዱበት በሀንጋሪ ነው ህክምና የተማሩት። የተወለዱት ያደጉት እና የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምሕርታቸውን የተከታተሉት በአዲስ አበባ ነው። በሃንጋሪ ትምህርታቸውን በከፍተኛ ማዕረግ ወይም «ኩም ላውደ» ካጠናቀቁ በኋላ ጓደኛቸውን ተከትለው ወደ ጀርመን መጡ። ጀርመን ከመጡ  በኋላ በህክምናው ትምህርት ቀጥለው ምኞታቸውን ለማሳካት በቅተዋል። እዚህ እንደመጡ ግን ወዲያውኑ አልነበረም በህክምና ሞያ የተሰማሩት።

የዶክተር ካሬላ እናት ኢትዮጵያዊ አባታቸው ደግሞ ህንዳዊ ናቸው። የዶክተር ካሬላ ስም የህንድ ስም ነው። ህንዳዊው አባታቸው በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በኋላም በደርግ ዘመነ መንግሥት በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በጋዜጠኝነት ይሰሩ ነበር። በሳንፎርድ የአንደኛ እና ከፊል የሁለተኛ ደረጃ ትምሕርታቸውን የተከታተሉት ወጣቷ ካሬላ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በንፋስ ስልክ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በጥሩ ውጤት ነበር የጨረሱት። ከዚያ በኋላ ነበር የነጻ ትምህርት እድል አግኝተው ሃንጋሪ የሄዱት። ህክምና አስቀድሞም ሲመኙት የነበረ ሞያ ነበር። የህጻናት ህክምናን የመረጡትም ጀርመን መጥተው በሌሎች የህክምና ዘርፎች ለመሰልጠን ከሞከሩ በኋላ ነው። በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ዶክተር ካሬላ የውጭ ዜጎች ጀርመን ውስጥ ውጤታማ ለመሆን ቋንቋውን ጠንቅቀው ማወቃቸው እጅግ አስፈላጊ ነው ይላሉ። ወደ ክሊኒካቸው ለሚመጡት ኢትዮጵያውያን እና ኤርታራውያን እናቶች ይህንኑ እንደሚመክሯቸው ይናገራሉ።  

ዶክተር ካሬላ ከዛሬ 30 ዓመት አንስቶ መኖሪያቸው ያደረጓት ጀርመን በህጻናት ህክምና እና አስተዳደግ ከዓለማችን ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው ሀገሮች አንዷ ናት። በሀገሪቱ ህጻናት እኩል የጤና አገልግሎት አግኝተው የሚያድጉ ቢሆንም ችግሮች የሉም ማለት አይደለም። ዶክተር ካሬላ እንደሚሉት የልጆች የጤና ችግሮች አሳሳቢ ባልሆኑባት በጀርመን ወላጆች ስለ ልጆቻቸው ጤንነት ማሰብ መጨነቃቸው አይቀርም። ይህ ዓይነቱ ጭንቀት ግን የህጻናት የጤና ይዞታ ከጀርመን ጋር ለውድድር በማይቀርብባት በኢትዮጵያ እንደሌለ ይህ ደግሞ በጥሩ ልምድነት ሊወሰድ የሚችል  እንደሆነ ይናገራሉ።ከዚህ የጀርመን ህብረተሰብ ጭንቀት በመነሳት የ53 ዓመትዋ ዶክተር ካሬላ Das Geheimnis gesunder Kinder «የጤናማ ልጆች አስተዳደግ ሚስጥር» የተሰኘ መፀሃፍ አሳትመዋል። በዚህ ዓመት በጥር ወር ለህትመት የበቃው እና ለወላጆች ምክር የሚሰጠው ይህ መፀሀፍ ሰሞኑን በብዛት ከተሸጡት መጻህፍት መካከል አንዱ ነው።

በዚህ መጸሀፍ አንድ ያሉት ዶክተር ካሬላ ፣ሌላ መፀሀፍ ለማውጣትም እየተዘጋጁ ነው።  በትውልድ ሀገራቸው ማስተማር እና መስራትም ይፈልጋሉ። ከህክምና ስራቸው ጎን ለጎን ሊያካሂዱ ያሰቧቸው ሌሎች እቅዶችም አሏቸው።

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic