ዶቼ ቬለ፤ የመገናኛ ብዙኀን መድረክ | ዓለም | DW | 10.06.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

ዶቼ ቬለ፤ የመገናኛ ብዙኀን መድረክ

ዓመታዊዉ የዶቼ ቬለ የመገናኛ ብዙኀን መድረክ በሚቀጥሉት ቀናት ይካሄዳል። ቀዉስ በበዛበት እና ቅድመ ምርመራ በተጠናከረበት ዓለም የመገናኛ ብዙሃን ሚና ምን ሊሆን እንደሚችል የሚወያየዉ ይህ መድረክ፤ መረጃ ማዛባት ላይም ያተኩራል። ዘጠነኛዉ የመገናኛ ብዙኀን መድረክ ከዚህም ሌላ በተቃራኒዉ መገናኛ ብዙኀን ላይ የሚታየዉን እምነት ማጣትም ይፈትሻል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:18

ዶቼ ቬለ

ከፊታችን ሰኞ እስከ ረቡዕ ድረስ ዶቼ ቬለ በሚያካሂደዉ ዓመታዊ የመገናኛ ብዙሃን መድረክ የሚሳተፉ 2300 ገደማ እንግዶችን ያስተናግዳል። ከ100 ሃገራት የተዉጣጡት የመገናኛ ብዙኀን ሠራተኖች እና ተመራማሪዎች፤ ፖለቲከኞች እንዲሁም የኪነጥበብ ሰዎች፣ የመብት ተሟጋቾች እና ባለራዕዮች ሰፋ ብለዉ በተሰናዱ 40 የተለያዩ ዝግጅቶች በሚቀርቡበት መድረክ በአንድነት ተቀምጠዉ ይወያያሉ። የዶቼ ቬለ ዋና ሥራ አስኪያጅ ፒተር ሊምቡርግ የጉባኤዉን ይዘት በአጭሩ እንዲህ ይገልጻሉ፤

«በዚህ ዓመት 40 የሚሆኑ የተለያዩ ዝግጅቶች አሉ። በጉባኤዎች እንደተለመደዉ ዉይይትና አዉደ ጥናት ይኖራል። በዘንድሮዉ ጉባኤ በፊልም መልክ የተለያዩ ዝግጅቶች የሚቀርቡበትም መድረክ ይኖረናል፤ በዚህም በማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን ፕሮጀክቶች የተሠሩ ልዩ ልዩ ሥራዎች ይቀርባሉ፤ ከአዘጋጆቹም ጋር የመነጋገር ዕድልም ይኖራል። ከዚህ በተጨማሪም ትልቅ አዉደርዕይ ተዘጋጅቷል።»

Peter Limbourg

የዶቼ ቬለ ዋና ሥራ አስኪያጅ ፒተር ሊምቡርግ

በመገናኛ ብዙሃን መድረኩ ከሚሳተፉት በተጨማሪ እንደአዉሮጳዉ ፓርላማ ምክትል ፕሬዝደንት አሌክሳንደር ግራፍ ላምብስዶርፍ፣ እንደፌደራል ጀርመን ምክር ቤት ወይም ቡንደስታኽ ምክትል ፕሬዝደንት ክላዉዲያ ሮዝ፣ አለያም የሥራ ሚኒስትር አንድሪያ ናህልስ ወይም የሙኒሽን የፀጥታ ጉባኤ ኃላፊ ቮልፍጋንግ ኢሺንገር ያሉት ታዋቂ ሰዎች ተወካዮቻቸዉን ሊልኩ ይችላሉ።

በዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃኑ መድረክ የዶቼ ቬለ ሚና እንደአዘጋጅ እና አስተናጋጅ ብቻ ሳይሆን እንደአንድ የዜና አዉታርም እንግዶቹን በቀጥታዉ ስቱዲዮዉ በመጋበዝ ዉይይትም ያካሂዳል። ዶቼ ቬለ ራሱን የሚገልጽበት መሪ ቃል አለዉ፤ «ለአዕምሮ የተሠናዳ» ወይም made for minds የሚል፤ የመገናኛ ብዙኀን መድረኩ አስተባባሪ ፓትሪክ ሉሽ ደግሞ መድረኩን «የአዕምሮ ቦታ» place for minds ብለዉታል።

«ከምር ከተወሰደ ሰዎች ዓለምን ለመለወጥ የሚያስችል የተለየ ነገር የሚያቀርቡበት ለየት ያለ መድረክ ሊቀርብላቸዉ ይገባል። የድረገጽ ጸሐፊዎች ሊሆኑ ይችላሉ፤ ወይም በሚኖሩበት ማኅበረሰብና አካባቢ አንድ ለዉጥ ማስገኘት የሚችሉ መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጅት ወይም በሲቪል ማኅበረሰብ ዉስጥ የሚሳተፉ ሊሆኑ ይችላሉ። የፖለቲካ ዉሳኔ ማሳለፍ የሚችልም ሰዉ ሊሆን ይችላል።»

እሳቸዉ እንደሚሉትም ለሦስት ቀናት ከሚካጌዱት ዝግጅቶቹ መካከል የሽልማት ሥነስርዓቱ እንዲያልፋቸዉ አይፈልጉም። የቱርኩ ጋዜጣ ሁሪየት ዋና አዘጋጅ ሴዳት ኢርጊን የዘንድሮዉ የዶቼ ቬለ የመናገር ነፃነት ተሸላሚ ነዉ። ከዚህ ሽልማት በተጨማሪም በየዓመቱ በኢንተርኔት ስለመብት ለሚሟገቱ ጸሐፍት ዶቼ ቬለ የሚያዘጋጀዉ ዘ ቦብስ የተሰኘዉ ሽልማት ይሰጣል። የዘንድሮዉ ተሸላሚ ባንግላዴሽ ዉስጥ በዚህ ዘርፍ የሚከናወን አንድ ፕሮጀክት ነዉ። ለሦስት ቀናት በሚካሄደዉ የዶቼ ቬለ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን መድረክ እንዲገኙ ከተጋበዙት መካከል የዩጋንዳዋ የሰብዓዊ መብት ተሟጋችና የኖቤል ተሸላሚ ካሻ ጃክሊን ናባጌስራ፤ ግብፃዊዉ የጎዳና ላይ የኪነጥበብ ሰዉ አቡበከር፣ ወይም የፍልስጤም እና ሶርያ ዜጋ የሆነዉ ፒያኖ ተጫዋች አይሃም አህመድ ይጠቀሳሉ። የጉባኤዉን የመዝጊያ ንግግር የሚያደርጉት የተመ የአየር ንብረት ለዉጥ ተከታታይ ዘርፍ ተሰናባች ኃላፊ ክርስቲያና ፊገርስ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።

ማቲያስ ፎን ሃይን/ ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic