ዶሮን ለወባ ትንኝ ማባረሪያ | ጤና እና አካባቢ | DW | 09.08.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

ዶሮን ለወባ ትንኝ ማባረሪያ

በመላዉ ዓለም ወደ 3,2 ቢሊየን ገደማ ሕዝብ ማለትም ከመላዉ የዓለም ሕዝብ ቁጥር ግማሽ የሚሆነዉ ማለት ነዉ፤ ለወባ በሽታ አደጋ የተጋለጠ መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:29

ዶሮን ለወባ

ወባ ዛሬም ገዳይነቱ እያሰጋ መፍትሄ የሚፈለግለት በሽታ ነዉ። ባለፈዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2015 ብቻ በመላዉ ዓለም 214 ሚሊየን ሰዎች በወባ በሽታ መያዛቸዉን የዓለም የጤና ድርጅት መረጃዎች ያመለክታሉ። በተቃራኒዉ ወባን ለመቆጣጠር ባለፉት 15 ዓመታት የተደረገዉ ጥረት የታማሚዉን ቁጥር በ37 በመቶ መቀነሱ፤ ወባ የምትቀጥፈዉ ሕይወትም በዚሁ ጊዜ በ60 በመቶ ዝቅ ማለቱም ተመዝግቧል። ይህ ለዉጥ የታየዉ በተመድ የአምዓቱ የልማት ግቦች መሠረት ወባ በሰዉ ጤና እና ሕይወት ላይ የምታደርሰዉን የጉዳት መጠን ለመቀነስ በተደረገዉ ጥረት ነዉ። በተለያዩ አካባቢዎች የወባ ትንኝን ንክሻ ለመከላከል የተለያዩ ዘዴዎችን መጠቀም የተለመደ ነዉ። የወይራም ሆነ ሌሎች ጭስ የወባ ትንኝን ሲያባርር ይታወቃል። ከሰሞኑ የተሰማዉ የምርምር ዉጤት ግን እንግዳ እና ብዙዎችን ያስገረመ ነዉ። ዶሮዎች የወባ በሽታን የምታስተላልፈዉን ትንኝ ድራሿን ማጥፋት ይችላሉ። ወይም ዶሮዎች ባሉበት ትንኟ ድርሽ አትልም።

Vogelgrippe Hühnerfarm

በኢትዮጵያዊ ተመራማሪ የተመራ አንድ ነፍሳትን የሚያጠና ቡድን በዚህ ጉዳይ ላይ ምርምሩን የጀመረዉ፣ ትንኞች የትኛዉን እንስሳም ሆነ የሰዉ ልጅ ሲነክሱ ሆኖም ዶሮዎችን ሲሸሹ ካስተዋለ በኋላ መሆኑን ከአዲስ አበባ የወጡ ዘገባዎች ያስረዳሉ። ምናልባት ትንኞቹ ዶሮዎች ለቅመዉ የሚበሏቸዉ መስሏቸዉ ሊሆን ይችላል ይላሉ ተመራማሪዎቹ። ተከታትለዉ በሙከራ አስደግፈዉ ሲያጠኑት ግን ነገሩ ሌላ ሆኖ ነዉ የተገኘዉ። ዶሮዎችን ያካተተዉ የወባ ትንኝ የማባረሪያ ስልት ምርምሩ የተካሄደዉ ምዕራብ ኢትዮጵያ ዉስጥ በተለያዩ ሦስት መንደሮች ነበር ። ዶሮዎችን ከነማደሪያቸዉ በመኝታቸዉ ሥር አድርገዉ በተኙት ቤተሰቦች ቤት የትንኟ ድራሿ አልተገኘም። ዶሮዎችን በመስፈሪያ ቦታቸዉ በማድረግ ከእነሱ ተለይተዉ በቤታቸዉ ያደሩት ቤተሰቦች መኖሪያ ደግሞ የወባ ትንኞቹ በብዛት ተገኙበት። ምርምሩ ቀጥሎ የዶሮ አካላት ክፍሎች በእቃ ተከቶ የተቀመጠበት አካባቢም የወባ ትንኞቹ በተመሳሳይ ድርሽ አላሉም።

የዓለም የጤና ድርጅት ለወባ ትንኝ ማባረሪያ ተብለዉ የሚረጩ መድኃኒቶችን ትንኟ እየተለማመድ መምጣቷ እንዳሰጋዉ ካመለከተ ከራረመ። ይህን ችግር ለመወጣት ደግሞ መከላከያ ክትባት ቢገኝ በሚል ተስፋ ተመራማሪዎችን ሲያበረታታ ይታያል።

በቅርቡ ይፋ የሆነዉ ግኝትም ከዚህ በመነሳት ታዲያ መድኃኒቶችን እየተለማመደች የሰዉን ልጅ የምታጠቃዉ ወባ አስተላላፊ ትንኝን የሚከላከል ስልት ከዶሮዎች ጠረን ሊገኝ እንደሚችል ሃሳብ ማቅረባቸዉ ተሰምቷል። ዶሮ የወባ ትንኝ መከላከያ መሆኗን ለሚሰማ ዝርዝሩን ከመረዳቱ አስቀድሞ ወዲያዉ የሚታሰበዉ ለዶሮዎች ከእንግዲህ ቆጥ አያስፈልጋቸዉም ከምናድርበት ያድራሉ ይሆናል። ይህ ግን ኢትዮጵያ ከምትከተለዉ የጤና ኤክስቴንሽን መመሪያ ጋር ይጣረሳል። የኢትዮጵያ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የወባ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ዘርፍ ባልደረባ ወደ አቶ ደረጀ ድሉም ለዚህ አፅንኦት ይሰጣሉ። የዶሮን የወባ ትንኝ ፀርነት እንደማንኛዉም ሰዉ በዜና ከመስማትና ማንበብ ዉጭ የተመራማሪዎቹንር ዝርዝር ማብራሪያ የማየት ዕድሉ መሥሪያ ቤታቸዉ እንዳልደረሰዉ ከገለጹልን በኋላ የግል አስተያየታቸዉን አካፈሉን።

እርግጥ ነዉ እንዲህ ያለዉ ዜና ሲሰማ ከወባ ትንኝ ንክሻ ለመዳን አጎበር ከልሎ መተኛቱ ቀርቶ በዶሮዎች መከበብ ሊታሰብ ይችላል። ዶሮዎችን እያረቡ እንቁላል እና ሌሎች ጥቅሞቿን በአንድ ወገን እያገኙ መድኃኒት ለመግዛት የሚወጣዉን ወጪ በመቀነስ፤ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ዓይነት ስልት መጠቀም ይቻል ብሎም መገመት አይከብድምም ይሆናል። ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት የወባ በሽታ ኢትዮጵያ ዉስጥ 60 በመቶ የሚሆነዉን ኅብረተሰብ የሚያሳስብ በሽታ ነዉ። የወባ ትንኝን ለመከላከል ጥቅም ላይ ከዋሉት ነገሮች ዋነኛዉ መኝታን የሚከልለዉ አጎበር ነዉ። የወባ መከላከል እና መቆጣጠር ዘርፍ ባልደረባ አቶ ደረጀ ሀገሪቱ ዉስጥ ያለዉ ዋናዉ ችግር ሰዎች የታደላቸዉን የወባ ትንኝ መከላከያ አጎበር በአግባቡ አለመጠቀማቸዉ ነዉ ይላሉ።

ወባ ከሰዎች ወደሰዎች በሴቷ ትንኝ ንክሻ አማካኝነት የሚተላለፍ በሽታ ነዉ። አኖፌሊስ አራቢኒሲስ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሃራ በስተ ደቡብ በሚገኙ ሃገራት ዉስጥ የወባ በሽታን በማስተላለፍ የምትታወቅ የወባ ትንኝ ናት። በቅርቡ ይፋ የሆነዉ የምርምር ግኝት የወባ በሽታን ተሸካሚ የሆነችዉ አኖፌሊስ አራቢኒሲስ ዘር ዶሮዎች ባሉበት አካባቢ ድርሽ እንደማትል ነዉ። ጥናቱ እና ምርምሩ የተካሄደዉ በኢትዮጵያ እና በስዊድን ሳይንቲስቶች ነዉ። ተመራማሪዎች ያስተዋሉትም ይህች የወባ በሽታ አስተላላፊ ትንኝ ዶሮዎችም ሆነ ሌሎች ወፎች በሚገኙበት አካባቢ መቅረብ አለመቻሏን ነዉ። እነሱ እንደሚሉት የምትሸሸዉም የዶሮዎቹን ጠረን ወይም ሽታ ነዉ።

እናም ተመራማሪዎቹ የሚሉት ፤ ቢያንስ የዶሮዋን ጠረን የወሰደ የወባ ትንኝ መከላከያ መድኃኒት ማዘጋጀት ይቻል ይሆናል ነዉ። አሁንም የሰዎች ልጆችን ሕይወት በመቅጠፍ የምታሳቅቀዉ ወባን ለመከላከል የሚያስችል መድኃኒት ለማግኘት የሚደረጉ ምርምሮች ሊበረታቱ ይገባል ይላሉ አቶ ደረጀ።

የዓለም የጤና ድርጅት ሰሞኑን ብዙዎችን ባስገረመዉ በዚህ የምርምር ዉጤት ላይ ያለዉን አስተያየት እንዲያጋራን ጠይቀን ነበር። መረጃዉ እንግዳ የሆነባቸዉ ቢኖሩም በተለይ ወባን የሚመለከተዉ ዘርፍ ጊዜ ወስዶ ጉዳዮን መርምሮ መናገር እንደሚበጀዉ በመግለጽ ለዛሬ አስተያየቱን ከመስጠት መቆጠቡን መምረጡን ገልጾልናል።

በጎርጎሪዮሳዊዉ 2015ዓ,ም ከመላዉ ዓለም 438 ሺዉ በወባ በሽታ አልቋል። በወባ የሚጠቃዉን አካባቢ ስንመለከት ደግሞ በተለይ ከሰሃራ በስተደቡብ የሚገኙት ሃገራት ግንባር ቀደም ስፍራዉን ይይዛሉ። በተጠቀሰዉ ዓመት ብቻም ከተመዘገበዉ የወባ ታማሚዎች ቁጥር 89 በመቶዉ ከሟቾቹም 91 በመቶዉ እዚያዉ የአፍሪቃ ክፍል ዉስጥ የሆነና የደረሰ ነዉ። ወባ አሁን ለሞት የሚያደርስ አደገኛ ከሚባሉት በሽታዎች አንዱ ነዉ። በዚያዉ ልክ ደግሞ ሊከላከሉት ብሎም ተገቢዉ ሕክምናም ከተገኘ ታክመዉ ለመዳን ይቻላል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic