1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዶላር ፍለጋ፦ የኢትዮጵያ ባንኮች እና የጥቁር ገበያው ፉክክር እስከ የት ይጓዛል?

ረቡዕ፣ ነሐሴ 1 2016

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጨረታ ዶላር በ107 ብር ከ90 ሣንቲም ተሸጧል። ተመኑ ትላንት በባንኮች ከነበረው አማካኝ ምንዛሪ በ4 ብር ገደማ ጨምሯል። ባንኮች በምንዛሪ ተመን ሲሽቀዳደሙ የጥቁር ገበያ ተዋንያን አድፍጠው ይታዘባሉ። በአዲሱ ሥርዓት የዋጋ ግሽበት በጥር ከ30-35% ሊደርስ እንደሚችል የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ሰነድ ያሳያል።

https://p.dw.com/p/4jD41
ማገናኛዉን ኮፒ አድርግ
ዩሮ፣ ዶላር እና ዩዋን
ሐምሌ 29 ቀን 2016 በኢትዮጵያ ባንኮች 57 ብር ከ48 ሣንቲም ገደማ ይመነዘር የነበረው አንድ የአሜሪካ ዶላር ወደ 107 ብር ከ90 ሣንቲም አሻቅቧል። ምስል Antonio Pisacreta/ROPI/picture-alliance

ዶላር ፍለጋ፦ የኢትዮጵያ ባንኮች እና የጥቁር ገበያው ፉክክር እስከ የት ይጓዛል?

10:10

ኢትዮጵያ በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓት መከተል ከጀመረች ከሣምንት በኋላ የጎንዮሽ ገበያው ተዋንያን ለውጡን በዐይነ ቁራኛ እየተከታተሉ ነው። ባለፉት ቀናት በከፍተኛ ፍጥነት ሲገሰግስ የታየው የባንኮች የዶላር የምንዛሪ ተመን ስንት ሲደርስ ይረጋጋል? መልስ የሚፈልጉለት ጥያቄ ነው።

መንግሥት ከዓለም አቀፍ አበዳሪዎች ያገኘው የውጭ ምንዛሪ በገበያው የሚፈጥረውንም ለውጥ መታዘብ ይሻሉ። በተለምዶ ጥቁር እየተባለ በሚጠራው ትይዩ ገበያ ላይ መንግሥት ሊወስድ የሚችለው እርምጃም በምንዛሪ ሥራ በተሰማሩ ሰዎች ዘንድ በሥጋት ይታያል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “የሕግ አስከባሪ ተቋማት ከድሮው በተለየ መንገድ እያንዳንዱ ሱቅ፤ እያንዳንዱ ሻይ ቤት የሚሠራ አሻጥር ካለ በደንብ ልብስ ብቻ ሳይሆን፤ ከደንብ ልብስ ውጪ ከመንግሥት የሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ቁጥጥር እንድታደርጉ በተሰጠው መመሪያ መሠረት ጥብቅ ሥራ ይጠበቅባችኋል” ሲሉ መደመጣቸው ሥጋታቸውን የሚያጠናክር ነው።

ትይዩው ገበያ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለቤተሰቦቻቸው የሚልኩትን ሐዋላ እየሰበሰቡ ለነጋዴዎች የሚያቀርቡትን ጨምሮ በርካታ ተዋንያን ያሉት ነው። የገበያው ጠባይ ውስጥ አዋቂዎች እንደሚሉት በዋናነት በውጭ ምንዛሪ ፍላጎት እና አቅርቦት ይወሰናል። የኢትዮጵያ መንግሥት ለዓመታት የዘለቀውን የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓት ሲያሻሽል የትይዩው ገበያ ተሳታፊዎች ስብሰባ ሳይቀመጡ ተመሳሳይ አቋም ማንጸባረቅ ይዘዋል።

ከዱባይ እየተመላለሱ የሚነግዱ አንድ ግለሰብ “እስኪለይለት ገለል” ብለዋል። በአዲስ አበባ ብሔራዊ ቴአትር አካባቢ በሚገኝ መደብር የውጭ መገበያያ ገንዘቦች የሚመነዝሩ ነጋዴ እንደሚሉት ሥራው “እንደ ወትሮው አይደለም።” ሌላ በተመሳሳይ የሥራ መስክ የተሰማሩ የዋና ከተማዋ ነዋሪ መቀዛቀዙን አረጋግጠው “ዶላር ያላቸው ምንዛሪው የበለጠ ይጨምራል” በሚል እምነት “ያዝ” ማድረጋቸውን አስረድተዋል።

አዲስ አበባ ብሔራዊ ቴአትር
በአዲስ አበባ ከተማ ብሔራዊ ቴአትር አካባቢ በሚገኝ መደብር የውጭ መገበያያ ገንዘቦች የሚመነዝሩ ነጋዴ ሥራው “እንደ ወትሮው አይደለም” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።ምስል Eshete Bekele/DW

ዶይቼ ቬለ በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች ያነጋገራቸው ሰዎች እንደሚሉት አንድ ዶላር ከ120 እስከ 140 ብር እየተመነዘረ ይገኛል። ከአውሮፓ ኅብረት 27 አባል ሃገራት መካከል የ20ዎቹ መገበያያ ገንዘብ የሆነው ዩሮ ከ125 እስከ 130 ብር ድረስ የሚመነዝሩ የትይዩ ገበያው ተዋንያን አሉ። የዩናይትድ ኪንግደም ፓውንድ 150 ብር ገደማ ይመነዘራል።

የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ በገበያው የተፈጠረው “ግራ መጋባት” የጎንዮሽ ምንዛሪው “ፈራ ተባ” እንዲል ሳያስገድደው እንዳልቀረ ይናገራሉ። በገበያው ከውጭ የሚገባ ዕቃ የሚሸጥበት ዋጋ የመረጋጋት ሁኔታ እንዲሁም “ባንኮቹ ለነጋዴው በቂ የውጭ ምንዛሪ ያቀርባሉ አያቀርቡም?” የሚሉ ጉዳዮች “ማንም ሰው ፈራ ተባ” እንዲል የሚያደርጉ ናቸው።

የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ነጋዴው “በአንድ ጊዜ ዘሎ [አንድ ዶላር] 180 ብር ሊገዛ አይችልም። ባንኮች ያቀረቡ እንደሆነ ሊወርድ ይችላል ብሎ ይፈራል” ሲሉ አስረድተዋል።

“በጥቁር ገበያ የማይሠራ ምን ነገር አለ?”

ትይዩው ገበያ “ሕገ-ወጥ” እየተባለ በባለሥልጣናቱ ሲሳደድ ይቆይ እንጂ ኢትዮጵያ ከዓለም ገበያ ለምትሸምታቸው ሸቀጦች ክፍያ ለመፈጸም ዋነኛ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ሆኖ ቆይቷል። የምጣኔ ሐብት ባለሙያው አቶ ጌታቸው ተክለማርያም የኢትዮጵያ ነጋዴዎች ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው ሸቀጦች ወደ ኢትዮጵያ ሲያስገቡ ትይዩውን ምንዛሪ ለመጠቀም ተገደው መቆየታቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ነጋዴዎች በሚያቀርቧቸው ሰነዶች የሸመቷቸው ዕቃዎች ትክክለኛ ዋጋ እንደማይጠቀስ የገለጹት አቶ ጌታቸው ክፍያው የተወሰነው በባንኮች “ብዙው ደግሞ ከባንክ ሥርዓት ውጪ ሐዋላን በመሳሰሉ መንገዶች እንደሚከፈል” አስረድተዋል።   

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “የሕግ አስከባሪ ተቋማት በእያንዳንዱ ሱቅ፤ እያንዳንዱ ሻይ ቤት የሚሠራ አሻጥር ካለ በደንብ ልብስ ብቻ ሳይሆን፤ ከደንብ ልብስ ውጪ ከመንግሥት የሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ቁጥጥር” እንዲያደርጉ ትዕዛዝ መሰጠቱን ተናግረዋል። ምስል Fana Broadcasting Corporate S.C.

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው ሣምንት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት ስለ መንግሥታቸው የኤኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር ማብራሪያ ሲሰጡ “ኢትዮጵያ ውስጥ ከነዳጅ እና ከማዳበሪያ ውጪ በጥቁር ገበያ የማይሠራ ምን ነገር አለ?” ሲሉ ተደምጠዋል። ዐቢይ በጽህፈት ቤታቸው ማብራሪያ ሲሰጡ የግል ባንኮች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጭምር ተገኝተው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ለመሆኑ ባንኮች ብር በጥቁር ገበያ አይዘረዝሩም?” እያሉ ከሰዋቸዋል። ዐቢይ በጥያቄ መልክ በሰነዘሩት ሐሳብ “ኮሚሽን” እንደሚቀበሉ፤ “በትውውቅ“ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ለመንገድ ግንባታ ከመንግሥት ጋር ውል የሚገቡ “ኮንትራክተሮች በጥቁር ገበያ ሒሳብ ነው ዋጋ የሚያስገቡት” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የውጭ ምንዛሪ ግብይት በአቅርቦት እና ፍላጎት እንዲከወን ከመደረጉ በፊት በነበረው የምንዛሪ ተመን “የሚሰራ ምንም ሥራ የለም” ሲሉ ተደምጠዋል። “መንግሥት ነዳጅ ይገዛል፤ ማዳበሪያ ይገዛል። ከዚህ ውጪ ሁሉ ነገር ጥቁር ገበያ ነው” ያሉት ዐቢይ “አሁን ምን ተዓምር ተፈጥሮ ነው ከ50 ወደ 70 ብር ገባ ተብሎ ዋጋ የሚጨመረው?” ሲሉ ጠይቀዋል።

መንግሥት በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓት ተግባራዊ ቢያደርግም ዐቢይ በባንኮች ተመን እና በትይዩው ገበያ መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ መሔድ እንዳላስደሰታቸው የዕለቱ ንግግራቸው ምስክር ነበር። መንግሥት ለባንኮች የውጭ ምንዛሪ ገዝተው የሚሸጡበትን ዋጋ እንደማይተምን ዐቢይ ተናግረዋል። ይሁንና በመጀመሪያዎቹ ቀናት ባንኮች ሁለቱን ገበያዎች ለማቀራረብ የተከተሉት መንገድ ዐቢይ “ትክክለኛ እርምጃ አይመስለኝም” የሚል አቋም አላቸው።

የባንኮቹ አካሔድ ይፋዊውን ምንዛሪ ከትይዩው ገበያ እንደማያዋህድ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥታቸው በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት ሰፊ ሊሆን አይገባም የሚል አቋም እንዳለው አስረድተዋል። “እናንተ 70 ስትገቡ እነሱ 130 ከገቡማ ምን ለውጥ አለው? ይሔ ንግግር ይፈልጋል። በቂ አይደለም የተሠራው ሥራ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ጥቁር ገበያን የሚቀንስ አካሔድ መከተል አለብን” የሚል ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ለዶላር ከፍ ያለ የምንዛሪ ተመን በመስጠት ቀዳሚ የነበረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አካሔዱን ቀዝቀዝ የማድረግ አዝማሚያ ሲያሳይ የግል ባንኮች ቀደም ቀደም እያሉ ይታያሉ። ምስል Eshete Bekele/DW

የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የውጭ ምንዛሪ ግብይቱ አሁን ካለው የትይዩ ገበያ ተመን አካባቢ ወይም ከዚያ አነስተኛ ቅናሽ አሳይቶ ሁለቱ ገበያዎች ይዋሃዳሉ ብለው ይጠብቃሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በጉዳዩ ላይ ከሰጡት አስተያየት በኋላ የባንኮች የዶላር መግዣ እና መሸጫ ተመን በከፍተኛ መጠን አሻቅቧል።

በብሔራዊ ባንክ መረጃ መሠረት ሐምሌ 30 ቀን 2016 አንድ የአሜሪካ ዶላር በባንኮች የተመነዘረበት አማካኝ 104 ብር ገደማ ነበር። በማግሥቱ ማለትም ዛሬ ነሐሴ 1 ቀን 2016 ብሔራዊው ባንክ ዶላር ለባንኮች ለማቅረብ ባካሔደው ጨረታ የምንዛሪው ተመን ወደ 107.9 ብር አሻቅቧል።

በዛሬው ዕለት ከፍተኛ የዶላር መግዣ እና መሸጫ ተመን ያቀረበው ገዳ ባንክ ነው። ባንኩ አንድ ዶላር በ107 ብር ገዝቶ በ112 ብር ይሸጣል። በሁለተኛ ደረጃ የሚገኘው ጸደይ ባንክ አንድ ዶላር በ102 ብር ገደማ ገዝቶ በ112 ብር የሚሸጥበት ተመን አቅርቧል።

ከባንኮቹ ዝቅተኛ ተመን ያቀረቡት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ እና ብርሐን ባንክ እንደ ቅደም ተከተላቸው ናቸው። ሦስቱ ባንኮች ዶላር የሚገዙበት ተመን በዛሬው ዕለት ከ100 ብር በታች ነው። ተመኑን ከፍ በማድረግ ቀዳሚ የነበረው መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አንድ ዶላር በ95 ብር ከ69 ሣንቲም ገደማ ገዝቶ 101 ብር ከ40 ሣንቲም ገደማ እየሸጠ ነው።

የኢትዮጵያ ባንኮች አንዱ ከሌላው “የተሻለ [የምንዛሪ ተመን] እየሰጠ ገበያ ለመሳብ እየተሯሯጠ ነው” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን “ሁሉም ቶሎ ዶላር ለማግኘት” እየተጣደፉ መሆኑን ታዝበዋል። ባንኮቹ ሊኖርባቸው የሚችለውን ዕዳ ለመክፈል ያላቸው ፍላጎት ለፉክክሩ አስተዋጽዖ ሊያበረክት እንደሚችልም ያምናሉ። ይሁንና የፉክክሩ “መድረሻ የት እንደሆነ አናውቅም” ሲሉ ተናግረዋል።

 ብሔራዊ ባንክ
ኢትዮጵያ በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓት መከተል ከጀመረች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ብሔራዊ ባንክ ባካሔደው ጨረታ አንድ ዶላር በ107 ብር ከ90 ሣንቲም ተሸጧል። ምስል Eshete Bekele/DW

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዛሬ በጨረታ ለባንኮች የውጭ ምንዛሪ ሸጧል። ከጠዋቱ 4 ሰዓት እስከ 6 ሰዓት በተካሔደው ጨረታ 27 ባንኮች መሳተፋቸውን የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ገልጸዋል። ማንኛውም ባንክ ለጨረታ ከቀረበው አጠቃላይ ዶላር ከ20 በመቶ በላይ መውሰድ አይችልም። ይሁንና ምን ያክል ዶላር ለጨረታ እንደቀረበ ይፋ አልተደረገም።

ብሔራዊው ባንክ በጨረታ የሚያቀርበው የውጭ ምንዛሪ አዎንታዊ የሆነ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ዶክተር አብዱልመናን ይስማማሉ። ባንኮቹ ዕዳቸውን ለመክፈል ወይም የነጋዴዎችን የዶላር ፍላጎት ለማሟላት እንደሚሹ ያስታወሱት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው መንግሥት ይኸን ፍላጎት የሚያሟላ የውጭ ምንዛሪ ማቅረብ ከቻለ ነጋዴዎች ወደ ትይዩ ገበያ የሚያቀኑበት ምክንያት እንደሚቀንስ አስረድተዋል። ይሁንና “የኢትዮጵያ መንግሥት ለዚያ የሚሆን [የውጭ ምንዛሪ] አይኖረውም” የሚል ሥጋት አላቸው።

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና ዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ መንግሥት የሰጡት 2.5 ቢሊዮን ዶላር ብድር እና እርዳታ ከብሔራዊ ባንክ ቋት መግባቱን ገዥው አቶ ማሞ ምሕረቱ ተናግረዋል። ይኸ የውጪ ምንዛሪ ግን ሙሉ በሙሉ በጨረታ ወደ ባንኮች የሚዘዋወር አይሆንም። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ለሠራተኞች ሊያደርግ ያቀደውን የደመወዝ ጭማሪ የሚያካትት 551 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት እያዘጋጀ ይገኛል።

መንግሥት ለአፈር ማዳበሪያለነዳጅ እና ለመድሐኒት ሊያደርገው ያቀደው ድጎማም ጠቀም ያለ የውጭ ምንዛሪ ያስፈልገዋል። የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች ኢትዮጵያ በብድር እና እርዳታ ያገኘችው የውጭ ምንዛሪ ገበያውን ለማረጋጋት ምን ያክል በቂ ነው? የሚል ጥያቄ አላቸው።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ኢዮብ ተካልኝ
የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የተሰጠውን ብድር እና እርዳታ ጨምሮ በመጪዎቹ ዓመታት በአጠቃላይ 27 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያገኝ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ኢዮብ ተካልኝ ተናግረዋል። ምስል Eshete Bekele/DW

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ኢዮብ ተካልኝ ግን በዕዳ እፎይታ፣ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት፣ ከዓለም ባንክ በተሰጡ ብድር እና እርዳታዎች፣ ወዳጅ ያሏቸው ሀገራት በብሔራዊ ባንክ ካደረጉት ተቀማጭ እንዲሁም ከየተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ጋር በተደረገ የመገበያያ ገንዘብ ልውውጥ ጨምሮ መንግሥታቸው በመጪዎቹ ዓመታት እስከ 27 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያገኝ አስረድተዋል። ኢዮብ የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ንብረት ከሆነው ፋና ብሮድካስቲንግ ጋር ባደረጉት ቃለ-መጠይቅ “ከሚያስፈልገን በላይ በጣም በቂ የሆነ ገንዘብ ነው እየመጣ ያለው” ሲሉ ተደምጠዋል።

በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ተግባራዊ በመሆኑ በኢትዮጵያ በጥር 2017 ገደማ የዋጋ ግሽበት ከ30 እስከ 35 በመቶ ሊደርስ እንደሚችል ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ይፋ ያደረገው ሰነድ ያሳያል። በሰነዱ የተጠቀሰው አሀዝ የዋጋ ግሽበት በሚያዝያ 2015 ከነበረበት 33.5 በመቶ የተቀራረበ ነው።

የምንዛሪ ተመን ለውጡን ጨምሮ የኢትዮጵያ መንግሥት ተግባራዊ የሚያደርገው ማሻሻያ ከማኅበራዊ ቅሬታ፣ ግጭት እና ዓለም አቀፍ የዋጋ አለመረጋጋት የሚመነጩ ሥጋቶች ሊኖሩበት እንደሚችሉ ይኸው ሰነድ ይጠቁማል። በሰነዱ መሠረት ቁልፍ የፊስካል እና የምንዛሪ ተመን ማሻሻያዎች ወጥነት የሌለው ትግበራ ወይም መቀልበስ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ከፍተኛ የፋይናንስ ክፍተት ሊፈጥር ወይም ከአበዳሪዎች ቃል የተገባለትን ድጋፍ ሊያጣ ይችላል።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ