ድጋፍና ተቃውሞ በግብፅ | አፍሪቃ | DW | 06.12.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ድጋፍና ተቃውሞ በግብፅ

በግብፅ ፕሬዝዳንታዊ ቤተመንግስት ፊት ለፊት የተጋጩት የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት መሐመድ ሙርሲ ተቃዋሚዎችና ደጋፊዎች አካባቢውን ለቀው እንዲሄዱ የግብፅ የክብር ዘብ ዛሬ ትዕዛዝ ካስተላለፈ በኋላ የሙርሲ ደጋፊዎች ከስፍራው እንደለቀቁ ተዘገበ ። ይሁንና ሙርሲ ያወጡትን ድንጋጌ በመቃወም የተሰበሰቡት ሰዎች ተቃውሞው እንደሚቀጥሉ ዝተዋል ።

በግብፅ ፕሬዝዳንታዊ ቤተመንግስት ፊት ለፊት የተጋጩት የግብፁ ፕሬዝዳንት መሐመድ ሙርሲ ተቃዋሚዎችና ደጋፊዎች አካባቢውን ለቀው እንዲሄዱ የግብፅ የክብር ዘብ ዛሬ ትዕዛዝ ካስተላለፈ በኋላ የሙርሲ ደጋፊዎች ከስፍራው እንደለቀቁ ተዘገበ ። ይሁንና ሙርሲ ከ 2 ሳምንት በፊት ያወጡትን ድንጋጌ በመቃወም ቤተ መንግሥቱ አካባቢየተሰበሰቡት ሰዎች በተቃውሞው እንደሚቀጥሉ ዝተዋል ። ሙርሲ ማምሻውን ለህዝቡ ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል ።

የግብፅ ፕሬዝዳንት መሐመድ ሙርሲ ብዙ ሥልጣን የሚያሰጣቸውን ተቃውሞ ያስነሳ ድንጋጌ ካወጡ 2 ሳምንት ሞላው ። ያኔ ድንጋጌውን በመቃወም ታህሪር አደባባይ የተጀመረው አመፅ ወደ ፕሬዝዳንታዊው

ቤተ መንግሥት ተሸጋግሮ ግጭቱ በፖሊስና በሰልፈኞች መካከል መሆኑ ቀርቶ በተቃዋሚዎችና በደጋፊዎች መካከል ከሆነ 2 ቀናት ተቆጥረዋል ። ሆኖም ዛሬ የግብፅ የክብር ዘብ በፕሬዝዳንታዊው ቤተ መንግሥት አካባቢ የተቃውሞ ሰልፍ ማካሄድን በማገድ ሰልፈኞቹም አካባቢውን ለቀው እንዲሄዱ ባዘዘው መሠረት የሙርሲ ደጋፊዎች የተቀመጠው የጊዜ ገደብ ከመድረሱ በፊት ጓዛቸውን ጠቅለው ሲነሱ ተቃዋሚዎች ግን እዚያው ቀርተዋል ። በቤተ መንግሥቱ ፊት ለፊት ሲጋጩ ውለው ያደሩትን የሞርሲ ተቃዋሚ ደጋፊዎች ለመለየትም የክብር ዘቡ ታንኮች መሃላቸው እንዲቆም ማደረጉን ሃላፊው ጀነራል ሞሐመድ ዛኪ አስታውቀዋል ። ተቃዋሚዎች ግን ቤተ መንግሥቱ ፊት ለፊት ሌሎች የተቃውሞ ሰልፎችን ማካሄዳቸው እንደማይቀርም እየዛቱ ነበር ቀን ። ተቃዋሚዎች ሙርሲ ከሥልጣን ይውረዱ ፤ ረቂቅ ህገ መንግሥቱም ይቀየር ነው የሚሉት ።

«ሙርሲ በእውነት አያስፈልጉንም።እርሳቸው እንዲመሩን አንፈልግም። የሙስሊም ወንድማማቾች ማህበርንም አንፈልግም፤ ረቂቅ ህገ መንግሥቱ እንዲቀየር ነው የምንፈልገው »

ከ 9 ቀን በኋላ ለህዝበ ውሳኔ ይቀርባል የተባለውን ረቂቅ ህገ መንግሥት  ለዘብተኞችና ክርስቲያኖች አልተቀበሉትም ። ለፕሬዝዳንት ሞርሲ ፍርድ ቤት ሳይቃወማቸው እርምጃ መውሰድ የሚያስችላቸው ሥልጣን የሚሰጠውን ድንጋጌ ከወጣ በኋላ በተከሰተው ብጥብጥ መንስኤ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 7 ደርሷል ። ከመካከላቸው 5 ቱ ትናንትናና ከትናnte በስተያ ተጠናክሮ በቀጠለው በተቃዋሚዎችና ደጋፊዎች ግጭት ነው የተገደሉት ። በግጭቱ ሰበብ 4 የሙርሲ አማካሪዎች እንዲሁም የግብፅ መንግሥታዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ሃላፊ በፈቃዳቸው ሥራቸውን መልቀቃቸው ተዘግቧል ። ትናንት በ 10 ሺህዎች የሚቆጠሩ በቤተ መንግሥቱ ፊት ለፊት ተቀምጠው የነበሩ ተቃዋሚዎችና የሙርሲ ደጋፊዎች ተቀጣይ ፈንጂና ድንጋይ ሲወራወሩ መኪናዎችም ሲያቃጥሉ ነው ያመሹት ። የካይሮው ብጥብጥ ለሊቱን ወደ ወደብ ከተማዋ ኢስማይሊያ ና ስዌዝ ተዛምቶ ተቃዋሚዎች የሙስሊም ወንድማማቾች ማህበርን ቢሮዎች አቃጥለዋል ።

ምዕራባውያን መንግሥታት የግብፁ ግጭት በውይይት እንዲፈታ እየጠየቁ ነው ። የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂለሪ ክሊንተን ችግሩን ለመፍታት ግልፅና ዲሞክራሲያዎ ውይይት እንዲካሄድ ጠይቀዋል ።  የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊዶ ቬስተር ቬለም ሁሉም ወገኖች ለችግሩ ሠላማዊ መፍትሄ እንዲሹ ጥሪ አስተላልፈዋል ።

« ከካይሮ በሰማሁት ዜና እጅግ ተደናግጫለሁ። አመፅ ለሃገር ውስጥ የፖለቲካ አለመግባባቶች የኃይል እርምጃ መፍትሄ አይደለም ። ሁሉም ወገኖች በሰከነ መንፈስ በማስተዋል ለችግሩ መላ እንዲፈልጉለት እማፀናለሁ »

ምንም እንኳን ተቃውሞው ቢቀጥልም የግብፅ ምክትል ፕሬዝዳንት መሐመድ ሜኪ ሂሻም በረቂቅ ህገ መንግሥቱ ላይ የሚካሄደው ህዝበ ውሳኔ በተያዘለት ጊዜ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል ። ሂሻም ተቃዋሚዎች ቅሬታቸውን በፅሁፍ ማቅረብ ይችላሉም ብለዋል ። ብጥብጡ ከተባባሰበት ጊዜ አንስቶ ከመገናኛ ብዙሃን የራቁት ሞርሲ ዛሬ ማምሻውን በቴሌቪዥን ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል ።

ሂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ