ድንገተኛው የእስረኞች መፈታት እና ዋሊያዎቹ በአፍሪቃ ዋንጫ | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 14.01.2022
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ድንገተኛው የእስረኞች መፈታት እና ዋሊያዎቹ በአፍሪቃ ዋንጫ

እስክንድር እና ጀዋርን ጨምሮ በእነርሱ መዝገብ የተከሰሱት ከእስር መለቀቅ ለቤተሰቦቻቸው እና ለደጋፊዎቻቸው የፈጠረው ደስታ እና እፎይታ ብዙም ሳይቆይ ትግራይ ውስጥ መንግሥት ሕግ ማስከበር ባለው ጦርነት ተማርከው ለወራት በእስር ቤት የቆዩት 6 ሰዎች መለቀቅ በሕዝብ ዘንድ የፈጠረው ስሜት በማኅበራዊው መገናኛ በተሰራጩ አስተያየቶች ይታያል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:47

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

 

ልክ ባለፈው ሳምንት ዓርብ ዕለት ነበር መንግሥት ብዙም ሳይጠበቅ በተመሳሳይ ወቅት ለእስር የተዳረጉትን የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ  እና የኦሮሞ ፌደራሊስት ምክር ቤት ኦፌኮ አመራሮችን ከዓመት ከስድስት ወር ገደማ እስር በኋላ ድንገት የመፍታቱ ዜና የተሰማው። በቀዳሚነት እስክንድር ነጋ እና በእርሱ መዝገብ የተከሰሱት እንዲሁም ጀዋር መሀመድ እና በእርሱ መዝገብ የተከሰሱት ከእስር መለቀቅ ለቤተሰቦቻቸው እና ለደጋፊዎቻቸው የፈጠረው ደስታ እና እፎይታ ብዙም ሳይቆይ ከትግራ ሕዝብ ነጻ አውጭ ትህነግ መሥራቾች እና ከፍተኛ አመራሮች መካከል ትግራይ ውስጥ መንግሥት ሕግ ማስከበር ባለው ጦርነት ተማርከው ለወራት በእስር ቤት የቆዩት ስብሃት ነጋን ጨምሮ ሌሎች ስድስት ሰዎች መለቀቅ በሕዝብ ዘንድ መደናገር ብሎም ቅሬታን ያስከተለ መሆኑ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚሰነዘሩት አስተያየቶች ያሳያሉ። መንግሥት ከበድ ያለ ክስ መስርቶባቸው የነበሩትን የህወሃትን ነባር ባለሥልጣናት ክስ ያቋረጥኩት በሀገሪቱ የተሻለ የሰላም መንገድ ለመፍጠር ነው የሚል አንድምታ ያለው ማብራሪያውን ሰጥቷል።

Balderas For True Democracy party president Eskindir Nega

ከተሰነዘሩት አብዛኞቹ አስተያየቶች ስሜታዊ እና ለመደበኛ መገናኛ ብዙሃን ደረጃቸው የማይመጥን በመሆኑ የተወሰኑ እና ለዘብ ያሉትን መራርጠናል። የመንግሥትን ርምጃ በአዎንታዊ ጎኑ ከተመለከቱት አንዷ ሜላት ሰሎሞን በትዊተር፤«በስሜት እና በበቀል ሀገር ሊቀጥል አይችልም። የመንግሥት ውሳኔ ፍሬ ለመመልከት ጥቂት ትዕግስት ይኑረን።» ሲሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ የሆኑት ውዱ ማን ግን፤ «ለሀገሪቱ ተስፋን ሳይሆን ጨለማን ነው የደቀነው። ስብሃትን ለመያዝ ስንት ሺህ ሠራዊት ተሰውቶ እሱን ከለቀከው ነገ ሌሎች ተጠያቂዎችን ለመያዝ ስትሞክር ሠራዊትህ ሞራሉ ምን ይሆን?» በማለት ይጠይቃሉ።»

ወዲ ሽባኻ ጨሚቱ ጨዳዳይ የሚል የፌስቡክ ስም የያዙ አስተያየት ሰጪ ደግሞ፤ «አንድ ሐሙስ የቀራቸው በጡረታ የተገለሉ ሽማግሌዎች ተፈቱ ብለው ኮረንቲ ለመጨበጥ እግዚኦ ምቀኝነት! በዚህ አይነት ወጣት ቢፈታ እኮ በታንክ ሰንሰለት ስር ይተኛሉ፤ አሁንስ ለዐቢይ አዘንኩ።» በማለት ቢፈቱ ምንድነው ችግሩ የሚል አንድምታ ያለውን ሃሳባቸውን አጋርተዋል።

ፍቱን ታደሰ በበኩላቸው በፌስቡክ፤ «የውሳኔ ሰጭነት አቅም ያለው ፓርላማ ቢኖረን ኖሮ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በፍርድ ቤቶች ሥልጣን ጣልቃ በመግባት በከባድ ወንጀልና በዘር ማጥፋት የተከሰሱ "ሰዎችን" በፖለቲካ ውሳኔ የፍርድ ሂደታቸው ተቋርጦ በነጻ እንዲሰናበቱ ሲወስን ፓርላማው ጠርቶ ሊጠይቀውና እንዳውም የመተማመኛ ድምፅ (Vote of no confidence) በማሳጣት ከሥልጣን ሊያግደው በቻለ ነበር፡፡» ብለዋል። ኢዮኤል ንጉሤ ደግሞ በዚሁ በፌስቡክ፤ «እንኳን እኛ እሳቸውም ስሰማ ደንግጫለሁ ብለዋል። ፌልትማን ይሆኑ እንዴ ውሳኔውን ያሳለፉትና ትዕዛዙን ለማረሚያ ቤቱ ያደረሱት? ቀልድ አይሉት ምር ሆኖብን በትዕግሥት እየጠበቅን ነው። እስካሁን የሰማናቸው ነገሮች ከእስር መፈታቱ ጋር በተያያዘ ግራ የሚያጋቡና የተምታቱ እንጂ ግልጽ አይደሉም።» ሲሉ፤

ዮናታን አማረ በበኩላቸው በፌስቡክ፤ «በአሁኑ ሰአት ሀገራችን የምትፈልገው በህዝብ ስም የፖለቲካ ጥማቱን የሚወጣባት ተራ የግለሰቦች ስብስብ ሳይሆን፤ አሁን ካለችበት የኢኮኖሚ ድቀት ፣ ከኋላ ቀርነት፣ ከድህነት፣ ከችግር፣ ከረሀብ ወዘተረፈ የሚገላግላት ብቻ ነው። ለወሬውማ እኛው እንበቃለን።» ብለዋል።

ኢሾ ብርሃንም ሌላው ጠያቂ ናቸው፤ «ጦርነቱን ስንደግፍ የነበረው ህወሃት የሰሜን ዕዝን በተኙበት ስለረሸነ ነበር። ጦርነቱ እንዲቀጥል የቀሰቀስነውም ይኼን ውንብድና የፈጸሙ የህወሃት አባላት በሕግ እንዲዳኙ ነበር። ወንጀለኞች ለፍትህ የማይቀርቡ ከሆነ የውጊያው አላማ ምን ነበር?» በማለት ጥያቄያቸውን በትዊተር አቅርበዋል።

ጦርነቱ እኮ ገና አላበቃም የሚሉት ደግሞ ሌላው የትዊተር ተጠቃሚ አበባው ጀምብ ናቸው፤ «ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህወሃት ትጥቅ ባልፈታበት፣ ጦርነት እያካሄደ ባለበት በዚህ ጊዜ ስላሸነፍን ምህረት አወረድን ማለታቸው በራሱ አግባብነት የሌለው ክርክር ነው። ከሰርን እንጂ አላተረፍንም። እንደ ሀገር ተሸነፍን እንጂ አላሸነፍንም።» ነው የሚሉት። አይዛክ አበበ አስተያየትም ከእሳቸው ይመሳሰላል፤ «ጦርነቱ መቼ አለቀ፣ ኦሮሚያ ውስጥ ቀን በቀን ሰው እየተገደለ፣ ህወሃት የጦርነት ነጋሪት በድጋሚ እየጎሰመ ምኑ ነው ሰላም? ሰላምም ቢሰፍን ወንጀለኞችን አለመቅጣት በተበዳይ ላይ እንደመሳለቅ ነው። ፍትህ ከሌለ ሰላም የለም!» ብለዋል።

በድሉ ዋቅጅራም በፌስቡክ ፤ «ይህንን ጽሁፍ የዛሬ ሁለት አመት ገደማ ዴስትኒ ኢትዮጵያ በሚባል ያላፈራ ሀገራዊ ውይይት ላይ ስሳተፍ፣ ካናዳዊው የውይይቱ አስተናባሪ በነገሩን ቁም ነገር ልጀምር፡፡ ሰውየው በሜክሲኮ ባካሄዱት ውይይት ላይ የሀገሪቱ ፕሬዚዳት ተሳታፊ ነበሩ፡፡ ታዲያ የመጀመሪያው ቀን አዳራሽ ሲገቡ የሀገሪቱን ዋና ተቃዋሚ ድርጅት መሪ በመመልከታቸው አዳራሹን ጥለው ይመጣሉ፡፡ ሰውየውም ይከተላቸውና፣

‹‹ምነው? ተመለሱ?›› ይጠይቃቸዋል፡፡

‹‹ያንን ሰውዬ ታውቀዋለህ?›› በቁጣ ፕሬዚዳንቱ፡፡

‹‹አዎ፡፡››

‹‹አምስት ጊዜ የመግደል ሙከራ አድርጎብኛል፡፡ ከዚህ ሰውዬ ጋር ለምንድነው የምነጋገረው?››

‹‹ስድስተኛውን የመግደል ሙከራ ለማስቀረት፡፡›› ብሎ ይመልስላቸዋል፡፡ ከዚያም ወደ አዳራሹ ይመለሳሉ፡፡ በውይይቱ መጨረሻ ፕሬዚዳንቱ አምስት ጊዜ የመግደል ሙከራ ያደረገባቸውን ሰው ምክትላቸው አድርገው ሜክሲኮን መምራት ጀመሩ፡፡ በዚህ እውነት የጀመርኩትበት ምክንያት ግልጽ ይመስለኛል፡፡ ኢትዮጵያ አገር አቀፍ የእርቅና የምክክር ኮሚሽን ስታቋቁም ውጤታማ ይሆን ዘንድ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና የፖለቲካ እስረኞች ከእስር ተለቀው ተሳታፊ እንዲሆኑ፣ ማንኛውም ፖለቲካዊና ሀገራዊ አስተሳሰብ ለምክክር እንደሚቀርብ የሚጠበቅ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር በጁሀር መሀመድና በእስክንድር ነጋ መዝገብ የተከሰሱ ተጠርጣሪዎች መፈታት የሚጠበቅ ነው፡፡ ሀሳባቸውን ወደድነውም ጠላነውም፣ የምክክር ጉባኤው ውጤት አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተሳትፏቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ መከላከያ ሠራዊታችንን በክህደት የጨፈጨፉና በጦር ሜዳ በከባድ መስዋእትነት የተማረኩትን እነ አቦይ ስብሀት ከእስር መፈታት፣ የፍትህ ሚንስትሩ በምክንያትነት ያቀረቡት ‹‹ሰብአዊነት›› እና የጤንነት ሁኔታ ግን፣ በእኔ አመለካከት ትረጉም የለሽና በሰብአዊነት ላይ ማሾፍ ነው። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወንጀል የፈጸሙ ወንጀለኞች ከግማሽ ምእተ አመት በኋላ፣ በ80 እና 90 ዓመታቸው በተሰደዱበት ሀገር፣ ለሞታቸው ከሚያጣጥሩበት አልጋ እየታደኑ ፍትህ ፊት የሚቀርቡት ስለሰብአዊነት ሲባል ነው።፡ የሰብአዊነት ዘበኛ ፍትህ ነው።» በማለት ዘለግ ያለ መሰል ይዘት ያለው አስተያየታቸውን በምሳሌ አጅበው አስነብበዋል። በዚህ መሀልም ጥያቄ የሚያቀርቡ አሉ ለምሳሌ ዶክተር በቃሉ አንማው በትዊተር «ጥያቄ አለኝ ወያኔ ሀገር የማፍረስ እቅዱ ከሽፎበታል፤ ከሞት የተረፈው የህወሃት አመራር መቀሌ ከመሸገ ውሎ አድሯል፤ ከእስር ስለተፈቱት አባሎቹም የተነፈሰው ነገር የለም። ለምን? ወያኔ አሁን ለምን ዝም አለ?» በማለት ፍትህ ይጠይቃሉ።

በዚህ ሳምንት ሌላው የብዙዎች መነጋገሪያ የሆነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከረዥም ዓመታት በኋላ የተሳተፈበት የአፍሪቃ እግር ኳስ ሻምፒዮና ነው። ዋሊያዎቹ ሁለት ግጥሚያ አድርገዋል። ከኬፕቬርዴ አንድ ለባዶ፤ ከካሜሮን አራት ለአንድ ተለያይተዋል። ለዚህ መድረሳቸውን የሚያደንቁና የሚያበረታቱ ብዙዎች ቢሆኑም ውጤት ስላልቀናቸው አዝናኝ አስተያየቶችን የሰነዘሩ ጥቂት አይደሉም። ከካሜሮን ጋር ቡድኑ የሚጫወት ቀን ሴሊና ኤንጅል «አቋማቸው ያስፈራኛል እነዚያ ግብዳ ናቸው» የሚል አስተያየታቸውን በፉስቡክ ሲያጋሩ፤ የቡድኑን ዝናና አቅም በማሰብ አረ ግጥሚያው በድርድር ይታለፍ የሚሉ አስተያየቶችን የሰነዘሩም ነበሩ። እንደተሰጋው ሆኖ ቡድኑ መሸነፉን ተከትሎ ታደለ አሰፋ «ኳስ ግን ዘጠና ደቂቃ መሆን የለበትም ይበዛል።» ሲሉ በቆይታው የነበራቸውን ጭንቀት ያመላከተ አስተያየታቸውን በፌስቡክ አጋርተዋል። ክፍሌ ተስፋዬ ግራ የገባቸው ይመስላል« ዋንጫ ለማግኘት ምን ያህል ጊዜ ሊፈጅብን ይችላል? ሁልጊዜ ምክንያት ስንፈልግ ነው የምንገኘው፤ አንዳንዴ ዝናብ ሌላ ጊዜ ፀሐይ ስለሆነ ነው ይባላል።» ሲሉም ስሜታቸውን ገልጸዋል። ጌጡ ተመስገን ግን በቡድኑ ተስፋ የቆረጡ አይመስልም፤ «ዋልያዎቹን እዚህ በመድረሳቸው ልናበረታታቸው አይገባም? ኢትዮጵያ ከረዥም ጊዜ በኋላ ከአፍሪቃ ሃያላን ተርታ ተሰልፋ ስትጫወት በማየታችን ደስ ሊለን እና ልናበረታታቸው ይገባል።» ሲሉም አስተያየታቸውን በፌስቡክ አካፍለዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች