ድርድር -ጦርነት፤ ጦርነት-ድርድር፤- ሶሪያ | ዓለም | DW | 03.04.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

ድርድር -ጦርነት፤ ጦርነት-ድርድር፤- ሶሪያ

ኪስንጀር ለሳዑዲ አረቢያዉ ንጉስ ፈይሰል አጭር መልዕክት አስተላለፉ።መልዕክቷ «አዉሮፕላኔ ነዳጅ አጥታ በመቆምዋ ወደ ሐገሬ መመለስ አልቻልኩምና እባክዎ ነዳጅ ይላኩልኝ» የምትል ነበረበች።ንጉሱ መለሱ «እኔ ሽማግሌ ነኝ።እየሩሳሌም ሔጄ አል አቅሳ  መስጊድ ለፈጣሪ መስገድ እችል ዘንድ ይረዱኝ ይሆን?»

አውዲዮውን ያዳምጡ። 13:42

ድርድር -ጦርነት፤ ጦርነት-ድርድር፤- ሶሪያ

አረብ  የቋንቋ ባሕል እምነቱን አንድነት ደፍልቆ መጠፋፊያዉ ካደረገዉ ዘመናት አስቆጥሯል።የአረቦች ታሪክ፤ ባሕል፤ እምነት፤ ሥልጣኔ፤ ቀንዲል የምትባለዋ የሶሪያ ፖለቲከኞችም አንድ ከመሆን ይልቅ ጠላትነትን መርጠዉ መተላለቅ ከጀመሩ ስድስተኛ ዓመታቸዉ።የሞስኮ፤ የዋሽግተን፤ የብራስልስ፤ የቤጂንግ ፖለቲከኞች በብዙ ነገር ይለያዩ ይሆናል።በሶሪያ ጦርነት ግን ፍፁም ይቃረናሉ።አንካራዎች ከዋሽግተን፤ብራስልሶች ጋር በጦር ሐይል ትብብር የተሳሰሩ፤ ከሞስኮ-ቴሕራን፤ ሪያዶች ጋር ከንግድ-እስከ ጉርብትና ከባሕል-እስከ ታሪክ-ሐይማኖት በሚደርስ ጥቅም የተቆራኙ ናቸዉ።በሶሪያ ጦርነት ግን ተቃራኒዉ ነዉ ሐቁ።አሜሪካኖችም-ካሜሪካኖች አይስማሙም።ጦርነቱም አሸናፊም-ተሸናፊም አልተለየበትም።አንድ መስለዉ ግን አንድ ነገር ይላሉ «ድርድር»።ለምን? 

                            

ታሕሳስ 1973 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር) ኩዌት ዉስጥ የተሰበሰቡት የአረብ ሐገራት የነዳጅ ሚኒስትሮች ያሳለፉት ዉሳኔ እስራኤልን ያስፈራ፤ የአሜሪካ መሪዎችን ያስቆጣ ነበር።የሚንስትሮቹ   ዉሳኔ፤ እስራኤል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዉሳኔ ቁጥር 242ን አክብራ በሐይል የያዘችዉን የአረቦች ግዛት ለቅቃ ካልወጣች አረቦች የጣሉትን የነዳጅ ዘይት ሽያጭ ማዕቀብን አያነሱም የሚል ነዉ።

ዉሳኔዉ ከቴል አቪቮች ይበልጥ ዋሽግተኖችን ያናደደ በተለይ ፕሬዝደንት ሪቻርድ ኒክሰንን ለጦር ኃይል ወረራ የገፋፋ ነበር።ዉጪ ጉዳይ

ሚንስትር ሔንሪ ኪሲንጀር ግን የፕሬዝደንት ኒክሰን ቁጣ፤ ምናልባትም የጦር ሐይል እርምጃ ከቬትናሙ ጦርነት ጋር ተዳምሮ የሚያደርሰዉን ኪሳራ አሰላስለዉ ጉዳዩን ለማርገብ አንድ ሁለት ይሉ ገቡ።ቁም ነገርን ከፌዝ፤ ፖለቲካን ከሽሙጥ ቀይጠዉ በመናገር ዲፕሎማሲያዊ ችሎታቸዉ የሚደነቁት ኪስንጀር ለሳዑዲ አረቢያዉ ንጉስ ፈይሰል አጭር መልዕክት አስተላለፉ።መልዕክቷ «አዉሮፕላኔ ነዳጅ አጥታ በመቆምዋ ወደ ሐገሬ መመለስ አልቻልኩምና እባክዎ ነዳጅ ይላኩልኝ» የምትል ነበረበች።ንጉሱ መለሱ «እኔ ሽማግሌ ነኝ።እየሩሳሌም ሔጄ አል አቅሳ  መስጊድ ለፈጣሪ መስገድ እችል ዘንድ ይረዱኝ ይሆን?» ብለዉ።

ኪሲንጀር ተበለጡ።ግን ዝም አላሉም።«ማዕቀቡን ካላቆማችሁ አሜሪካ ጠንካራ እርምጃ ልትወስድባችሁ ትችላለች» የሚል ይዘት ያለዉ ማስፈራሪያ ላኩ።ጠንካራዉ እርምጃ ወረራ እንደሚሆን ንጉስ ፈይሰል አላጡትም።ወረራዉን መቋቋም እንደማይችሉም ያዉቁታል።ግን መለሱ።«የኔ ሕዝብ የግመል ወተት እየጠጣ፤ ቴሚር እየበላ በረሐ ይኖር የነበረ ነዉ።ቢወረር ወደዚያ በረሐ መመለስ አያቅተዉም።»እያሉ።

ብዙ አልቆዩም።የወንድማቸዉ ልጅ በጥይት ደብድቦ ገደላቸዉ።ገዳያቸዉ እንጂ አስገዳያቸዉ «በሆድ ይፍጀዉ ብሒል እንደተጀቦነ አርባ ሁለተኛ ዓመቱ አለፈ።ኪሲንጀር አሸነፉ።የንጉሱ ልጅ ልዑል ቱርኪ ኢብን ፈይሰል በቅርቡ ያቀርቶ ሌላ ታሪክ መጥቶ አሉ።

                        

«እንደሚመስለኝ ከአርባ ዓመት በፊት እነዚያ ቃላት በተነገሩበት ወቅት የነበረዉ እዉነት ብዙ ተለዉጧል።ንጉሳዊ አስተዳደሩ ወደ በረሐ መመለስን እንደ አማራጭ የሚያይበት ጊዜ አልፏል።የመሠረተ ልማት አዉታሮቹ የተገነቡበት፤በተማሪዎች እና በወደፊቱ ትዉልድ ላይ የሚወጣዉ መዋዕለ ንዋይ፤ ሥራ ላይ የዋሉት ፕሬጀክቶች ሌሎችም የከተማ አኗኗርን ለማስፈን የተደረጉ ናቸዉ።»

የከተሜዉ አረብ ዉዝግብ፤ግጭት፤ጦርነትም ከእስራኤል ጋር አይደለም።ከአሜሪካ ጋርም አይደለም።አንድም እርስ በርስ ሁለትም ከኢራን ጋር እንጂ።ሶሪያ የዘመናችን አብነት ናት።

አረብ ሐብታም ነዉ።ሳዑዲ አረቢያ

ደግሞ በጣም ሐብታም ናት።በ20011 እስከ 2013 በነበሩት ሁለት ዓመታት ብቻ የሶሪያ አማፂያንን ለማስታጠቅ አንዲት ሳዑዲ አረቢያ ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ ከስክሳለች።ትንሺቱ ቀጠር ከ3 ቢሊዮን ዶላር አፍስሳለች።ጦርነቱ ዘንድሮ ስድስተኛ ዓመቱ ነዉ።ሁለቱ ሐገራት ብቻ በሁለት ዓመት ዉስጥ ሰባት ቢሊዮን ዶላር ካወጡ በስድስት ዓመት 21 ቢሊዮን ዶላር ረጭተዋል።

ፋርስም ሐብታም ነዉ።የፕሬዝደንት በሽር አል-አሰድን መንግሥት ለመደገፍ አንዲት ኢራን ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር ክስክሳለች።ግን አረብ ደሐ ነዉ።ከ14 ሚሊዮን የሚበልጥ ሶሪያዊ እዉል ዉሐ የሚያገኘዉ እየለመነ ነዉ።ግማሽ ሚሊዮን የሚገመተዉ ደሐ አረብ አልቋል።

ወርልድ ቪዥን የተሰኘዉ ግብረ-ሰናይ ድርጅት እንደሚለዉ ወትሮም ከድሕነት ብዙም ያልራቀችዉ ሶሪያ ባለፉት ስድስት ዓመታት ወደ 280 ቢሊዮን ዶላር ከስራለች።የዓለም ባንክ እንደገመተዉ ደግሞ የሶሪያን ስደተኞች የሚያስተናግዱት ዮርዳኖስ፤ቱርክ፤ኢራቅ እና ግብፅ 35 ቢሊዮን ዶላር ከስረዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ «አሸባሪ» የምትላቸዉን የሶሪያ ሸማቂዎች መደብደብ ከጀመረች  ከነሐሴ 2014 ጀምሮ በቀን የ12 ሚሊዮን ዶላር ቦምብ እና ሚሳዬል  ሶሪያ ላያ ታዘንባለች።አሜሪካን ተከትለዉ ሶሪያን የሚደበድቡት ብሪታንያ፤ ካናዳ፤ አዉስትሬሊያ፤ የአዉሮጳ ሕብረት አባል ሐገራት እና የአረብ ሐገራት የሚያወጡት የገንዘብ መጠን አሜሪካኖች ከሚያወጡት ቢበልጥ እንጂ አያንስም።

 

ሩሲያ «አሸባሪ» የምትላቸዉን ቡድናት መደብደብ ከጀመረች ከመስከረም 2015 ጀምሮ በየቀኑ ከ3

ሚሊዮን ዶላር በላይ ትከሰክሳለች።ዓለም ሐብታም ነዉ።ግን ከ60 ሚሊዮን ለሚበልጥ ስደተኛ ምግብ እና  መጠለያ  መስጠት አይፈልግም።ከ30 ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ አድም በምግብ እጥረት አለያም በለየለት ረሐብ ይጠበሳል።አዉሮጳ እና የአሜሪካ መንግሥታት ሥደተኛ እንዳይገባባቸዉ ድንበራቸዉን ያሳጥራሉ።የገባዉ እንዲወጣ አንዴ በኃይማኖቱ ሌላ ጊዜ በቆዳ ቀለሙ ያበሻቅጡታል።

ሶሪያ ላይ ያ ሁሉ ሕዝብ አልቆi፤ ያ ሁሉ ንብረት ወድሞ፤ ቢሊዮነ-ቢሊዮናት ዶላር ፈስሶም ዓለም  ጦርነቱን ለማቆም ፍላጎት ያለዉ አይመስልም።እርግጥ ነዉ በጦርነቱ አሸናፊ-እና ተሸናፊዉን መለየት እንደማይቻል የዓለም ፖለቲከኞች አይደሉም ተራዉ ሰዉም ጠንቅቆ ያዉቀዋል።የሚታወቀዉ ፈጥቶ ሲመጣ የሚመዘዝ አንድ ማደናገሪያ አለች።ድርድር የሚሏት።የቪየና ድርድር ሒደት፤የዤኔቭ የድርድር ሂደት ፤የአስታና ድርድር----ስድስተኛ ዓመቱ።ስድተኛዉ የዤኔቭ ድርድርም ባለፈዉ ሳምንት አበቃ።

                              

«ከዚሕኛዉ ዙር (ድርድር) በኋላ ከጥንቃቄ ጋር፤ ሁሉም ተጋባዦች የያዝነዉን አጀንዳ፤ በአቀርብነዉ ስልት መሠረት በጥልቅ መርምረዉታል ማለት እችላለሁ።እርግጥ ነዉ ይሕን ማድረጋቸዉን ይክዱ ይሆናል።ምክንያቱም መካድ የተለመደ ነዉና።»

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የአረብ ሊግ ዋና አደራዳሪ ስታፋን ደሚስቱራ።የሚካካድ ዓለም።መካካድ ፈሊጥ የሆነበት ዲፕሎማሲ።ከደሚስቱራ በፊት ላሕዳር ብራሒሚ ነበሩ።አንጋፋዉ አልጄሪያዊዉ  ዲፕሎማት የሶሪያ አረቦችን ለማስታረቅ አረቦችን በአረብኛ ማናገሩ ብቻ እንደማይበቃ ሲያዉቁት በበቃኝ አቆሙ።ከብራሒሚ በፊት ኮፊ አናን ነበሩ።የዓለም ትልቅ የዲፕሎማሲ ማሕበርን ነብስ ካወቁበት ጊዜ ጀምሮ አልተለዩትም።

ግዙፉን ድርጅት አስር ዓመት መርተዉታል።በአስር ዓመት የዋና ፀሐፊነት ዘመናቸዉ ለዓለም ሠላም ላበረከቱት ታላቅ አስተዋፅኦ የዓለምን ታላቅ የሠላም ሽልማት ኖቤልን ተሸልመዋል።የሶሪያ ጦርነት አቀጣጣዮችን ለማግባባት ግን ስድስት ወሩ ሞከሩ። አቃታቸዉ።ተሸነፉ።አቆሙ።

ደ ሚስቱራ ዘመነ ሥልጣናቸዉ ለተጨማሪ ስድት ወር ተራዝሞላቸዋል።በምዕራብ-ምሥራቆች፤በአረብ-ፋርሶች፤ በቱርክ-ኩርዶች ግራ ቀኝ የሚጎተቱን የሶሪያ ተፋላሚዎች የማደራደሩ ሒደት ለዉጤት መብቃቱን እራሳቸዉም እርግጠኛ አይደሉም።

                            

«ከባድ ፈተና እንዳለ ማንም

አይክደዉም።እኔም አልክደዉም።እስካሁን የተደረገዉ ድርድር በቅርቡ ወደ ሰላማዊ ሥምምነት ይደርሳል የሚል ግምትም የለኝም።ምንም ጥርጥር የለዉም።የምናገረዉ በሁሉም ተሳታፊዎች ሥም ነዉ ብዬ አምናለሁ።በፖለቲካዊ ሒደት የታየዉን ይሕንን ለጋ ጅምር ማጠናከር አለብን።»

ኮፊ አናን የአደራዳሪነት ሐላፊነታቸዉን በ«በቃኝ» ያቆሙት የዓለም ኃያላን የጋራ አቋም ካልያዙ ሶሪያዎችን እየሰበሰቡ ተደራደሩ ማለቱ ትርጉም የለዉም ብለዉ ነበር።የጦርነቱን ተሳታፊዎች ማንነት፤ የየተሳታፊዎችን ዓላማና ፍላጎት የሚያዉቁ የፖለቲካ ተንታኞች ደግሞ ከኮፊ አናንም ጠንከር ብለዉ ጦርነቱ የሚቆመዉ ዋሽግተኖች-ከሞስኮ፤ ሪያዶች-ከቴሕራን ሲስማሙ ብቻ ነዉ ይላሉ።

የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ እና ሹማምንቶቻቸዉ ግን የሶሪያዉ ፕሬዝደንት በሽር አል-አሰድ ከሥልጣና ካልተወደገዱ ጦርነቱ አይቆምም ባዮች ነበሩ።

                               

«የአሰድ የሥልጣን ቀናት በጣት የሚቆጠሩ ናቸዉ።አሳድ መወገድ እንዳለባቸዉ እንስማማለን።አሰድ መወገድ አለባቸዉ ስል፤ አሰድ እንደሚወገዱ እተማመናለሁ።ጥያቄዉ ይሆን-ይሆን ወይ አይደለም መቼ እንጂ።»ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮቹም ደገሙ-አሰለሱትም።ሒላሪ ክሊንተን

                         

«ለሶሪያ ሕዝብ ሲባል፤ እሳቸዉ ከስልጣን የሚሰናበቱበት ጊዜ ደርሷል።»ሌላዉ የቀድሞ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጆን ኬሪ አሰለሱ።«እሳቸዉ በማያሻማ መንገድ እንደገለፁት አሰድ ሕጋዊነታቸዉን አጥተዋል።መምራት አይችሉም።»

የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት ጦርነቱ በጋመ፤ ድርድሩ በተጀመረ፤ ዲፕሎማሲዉ በተካረረ ቁጥር ያሉትን ሲሉ ሩሲያዎች ካንጀትም ሆነ ካንገት የአሰድን ሥልጣን የሚወስነዉ የሶሪያ ሕዝብ ነዉ ሲሉ ነበር።ሁለቱ አልተደማመጡም።መደማመጥ አልፈለጉም። ያደናቆሩት ዓለምም ሁለቱንም አልሰማቸዉም።

እዉነቱም አሰድ እንደነበሩ አሉ።ኦባማ ግን በርግጥ ሔዱ።ጆን ኬሪም።ክሊንተን ተሸነፉ።ዶናልድ ትራምፕ አሸነፉ።የትራምፕ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሬክስ ቲለርሰን ባለፈዉ ሳምንት አንካራ ላይ አዲስ ነገር አሉ።«የፕሬዝደንት አሰድ የረጅም ጊዜ ሕልዉና በሶሪያ ሕዝብ ይወሰናል።»ሞስኮዎች እስከ ዛሬም ሌላ አላሉም።የአዲሶቹ የአሜሪካ መሪዎች አዲስ አቋም የሞስኮ-ዋሽግተኖችን ፍትጊያ አስወግዶ ለሶሪያ የሰላም ጭላንጭል ይበርቅ ይሆን? 

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ

 

 

 

 

 

 

Audios and videos on the topic