ድርቅ እና አስቸኳይ እርዳታ በኢትዮጵያ  | ኢትዮጵያ | DW | 29.03.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

ድርቅ እና አስቸኳይ እርዳታ በኢትዮጵያ 

የእርዳታ ጥሪዬ ምላሽ አላገኘም የሚለው መንግሥት በሌላ በኩል የተረጂዎቹ ቁጥር በእጥፍ ቢጨምር እንኳን አስተማማኝ የእህል ክምችት ስላለ ችግሩን መቋቋም እችላለሁ እያለ ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:59

ድርቅ እና አስቸኳይ እርዳታ

በኢትዮጵያ የበልግ ዝናብ ካልጣለ የተረጂዎች ቁጥር ሊጨምር ይችላል የሚል ስጋት አለ። ይሁንና አንዳንድ የበልግ አብቃይ አካባቢዎች የሚጠበቀው ዝናብ ባይጥል ወይንም ሥርጭቱ ተመጣኝ ሆኖ ባይቀጥል ሊያስከትል የሚችለውን ችግር መቋቋም የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን መንግሥት አስታውቋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ለዶቼ ቬለ እንደገለፀው ድርቁ በጸናባቸው አካባቢዎች ከሚሰጠው ድጋፍ በተጨማሪ ለዚህ ስጋት መንግሥት እየተዘጋጀ  ነው።  
ባለፈው ዓመት በዓለማችን የተከሰተው ኤልኒኞ የተባለው የአየር ንብረት ለውጥ በኢትዮጵያ 10.2 ሚሊዮን ሰዎችን የምግብ እርዳታ ጠባቂ አድርጎ ነበር። በዘንድሮው የመኽር ዝናብ እጥረት ምክንያት ደግሞ የአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ያስፈለገው ዜጋ ቁጥር ከ5.6 ሚሊዮን በላይ ሆኗል። ከመጋቢት አጋማሽ ጀምሮ የሚጠበቀው የበልግ ዝናብ በውቅቱ እና በተገቢው መጠን ካልጣለ

በድርቅ ሊጠቁ የሚችሉ ሰዎች ቁጥር ከፍ ሊል እንደሚችል የተመድ ከአንድ ወር በፊት አስጠንቅቆ ነበር። በሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሀን ዘገባ መሠረት የበልግ ዝናብ መጣል ባልጀመረባቸው የደቡብ ኦሞ ዞንን በመሳሰሉ አካባቢዎች የተረጂዎች ቁጥር እየጨመረ ነው። የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኑነት ኃላፊ አቶ ደበበ ዘውዴ  ድርቁ በበረታባቸው አካባቢዎች የተቻለው ሁሉ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል። አቶ ደበበ የሚያሰጋው የበልግ ዝናብ እጥረት ቢከሰት አለያም ሥርጭቱ እንደሚጠበቀው ባይሆን እንኳን መንግሥት እና ህብረተሰቡ ዝግጅት አድርገዋል ይላሉ።የኢትዮጵያ መንግሥት ላለፈው ዓመቱም ሆነ ለዘንድሮው ድርቅ መቋቋሚያ ለለጋሽ ሃገራት ላቀረበው ጥሪ በቂ ምላሽ አላገኘም። በዚህ የተነሳም የአምናውን ድርቅ ለመቋቋም መንግሥት ከራሱ ወጪ ማድረጉን  አስታውቋል። ዘንድሮም ለለጋሽ ሃገራት የ948 ሚሊዮን ዶላር የእርዳታ ጥሪ ቢያደርግም ጥቂት መንግሥታት ከሰጡት ምላሽ በስተቀር የሚፈለገው እርዳታ አለመገኘቱን ነው የገለፀው። የእርዳታ ጥሪዬ ምላሽ አላገኘም የሚለው መንግሥት በሌላ በኩል የተረጂዎቹ ቁጥር በእጥፍ ቢጨምር እንኳን አስተማማኝ የእህል ክምችት ስላለ ችግሩን መቋቋም እችላለሁ እያለ ነው። መንግሥት በድርቅ በተጠቁ አካባቢዎች የሚያስፈልገውን ድጋፍ ከ72 ሰዓታት ባጠረ ጊዜ ውስጥ በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ አቶ ደበበ ቢናገሩም በአንዳንድ አካባቢዎች እርዳታ በወቅቱ እየደረሰ አለመሆኑን የሚገልጹ ቅሬታዎች እየቀረቡ ነው።

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic