ድርቅ በአፋር መከሰቱ | ኢትዮጵያ | DW | 06.08.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

ድርቅ በአፋር መከሰቱ

አፋር መስተዳደር በተከሰተው ድርቅ በየቀኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ ከብቶች በማለቅ ላይ መሆናቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ፤ የአካባቢው ባለሥልጣናትም ተገቢና ፈጣን ምላሽ አልሰጡም፤ እንደውም ድርቁን ለመደባበቅ ይሞክራሉ ሲሉ አማረዋል። የፌዴራልና የክልል መንግሥት ግን ችግሩን ለመቋቋም በመስራት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:47
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:47 ደቂቃ

ድርቅ በአፋር፤ «ከብቶች እያለቁ ነው»

አፋር መስተዳደር በተከሰተ ድርቅ በቀን በመቶ የሚቆጠሩ ከብቶች እያለቁ መሆናቸው እየተነገረ ነው። በአካባቢው ካለፈው ዓመት ሰኔ ወር አንስቶ ከ12 ወራት በላይ በቂ ዝናብ አለመጣሉን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጠዋል። በአካባቢው በቂ ዝናብ አለመጣሉ ለድርቁ ምክንያት ከሆኑ ነገሮች ዋነኛው ነው ተብሏል። አንድ የአካባቢው ነዋሪ እንደሆኑ የገለጡልን ግለሰብ ድርቁ አሁን እየተባባሰ ነው ይላሉ።

«እዚህ አዋሽ ፈንታሌ ወረዳ በርድቅ ምክንያት በጣም ከብቶች እያለቁብን ነው። አርብቶ አደር ነን፤ እና ከብቶቻችንን በጣም እያለቁብን ነው። በጣም ድርቅ ገብቷል፤። እና ያለፈው ረመዳን ወር፤ የዛሬ ዓሥራ ሁለት ወር ነው ዝናብ የዘነበው። እስካሁን ድረስ ዝናብ የሚባል ነገር የለም፤ ውኃ የለም፤ ሣር የለም፤ ከብቱ በጣም እያለቀ ነው። እዚህ ጋር ኃይ ባይ ማንም የመንግሥት አካል የለም።እና ይኽንን። ለሚመለከተው ክፍል እንድታስተላልፍልን ነው።»

Dürre in Ostafrika: Äthiopien

ከዓመት በላይ ዝናብ በመጥፋቱ ቢያንስ ከአንድ ወር ከአስራ አምስት ቀን አንስቶ እንስሳቱ በከፍተኛ ሁናቴ እያለቁ መኾናቸውን ደግሞ ሌላ የአካባቢው ነዋሪ ገልጠዋል። መንግሥታዊ ያልሆኑ አንዳንድ ድርጅቶች ርዳታ ቢያደርጉም በቂ አይደለም ብለዋል እኚሁ ነዋሪ።

«የድንገተኛ አደጋ መርሐግብር ላይ አንዳንድ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ርዳታ ያደርጋሉ፤ ግን በቂ አይደለም። እንስሳት እየሞቱ ነው። እንስሳቱ በድርቁ ምንክንያት ስኳር ፕሮጀክት ውስጥ ገብተው የሸንኮራ አገዳ እየተመገቡ ነው።»

መንገድ ላይ ቢኬድ የሞቱት እንስሳት ሽታ አያስጠጋም፤ በየቀበሌው ሆዳቸው አብጦ በየቦታም የወደቁ ከብቶች ተበራክተዋል ሲሉም አክለዋል። ሌላ የአካባቢው ነዋሪ እንደሆኑ የገለጡልን ግለሰብ ደግሞ ባለሥልጣናት ችግሩን ይፋ አድርገው መፍትኄ ከመፈለግ ይልቅ ለማድበስበስ ይሞክራሉ ብለዋል። በአካባቢው ፈጣን ርዳታ እና ርብብርብ ካልተደረገ ችግሩ ከከብቶች እልቂትም ሊሻገር እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጠዋል።

«በአፋር ታሪክ ተከስቶ የማይታወቅ አይነት የከብት ማለቅ ነው በአካባቢው የተከሰተው። ይኼ አርብቶ-አደርማኅበረሰብ ቀጥታ ጥገኛ የኾነው ከብት ላይ ነው። ከብቱ አለቀ ማለት በሚቀጥለው ደግሞ ማኅበረሰቡ ላይ ከፍተኛ የኾነ ረሐብ እንደሚከሰት አመላካች ነው።»

በአካባቢው ተከሰተ ስለተባለው ከፍተኛ ድርቅ የሚመለከታቸው አካላት መልስ እንዲሰጡበት ለማድረግ ሙከራ አድርገን ነበር። በቅድሚያ የደወልነው የአዋሽ 7 ኪሎ ወረዳ የአደጋ ዝግጅቱነት እና መከላከል ክፍል መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙሣ ሐሰን ጋር ነበር። ኃላፊው ዝርዝር ማብራሪያ ሊሰጡን ቃል ገብተው ቀጠሮ ቢያስይዙንም በተደጋጋሚ ስንደውል ስልካቸው አይነሳም።

Dürre in Ostafrika: Äthiopien

የግብርና ሚንስቴር ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ምትኩ ካሣ በእርግጥም በአፋር ብቻ ሳይኾን በሌሎችም አካባቢዎች ድርቅ መከሠቱን ተናግረዋል።

«አኹን በእኛ ደረጃ እያደረግን የምንገኘው አኹን ያለውን ነው። ስለዚህ ድርቅ አለ፤ በትክክል ድርቅ አለ። የዝናብ መዛባት አለ፤ ምክንያቱም የዝናብ መዛባት ሁላችንም እንደምናውቀው ኢሊኖ በሚባለው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መዛባት ክስተት ውስጥ ነው ያለነው። ይኼ እንግዲህ አፋር ውስጥ ብቻ ሳይኾን በሌሎችም አካባቢዎች ደጋ እና ወይናደጋ አካባቢም ላይ የክረምት ዝናብ ላይ ተጽዕኖ እያደረሰ ነው። ስለእዚህ ይኽን በተመለከተ የፌዴራል መንግሥት እና የክልል መንግሥት በጋራ በመኾን ችግሩን ለመቋቋም እየተሠራ ነው የሚገኘው።»

ሚንስቴር ዴኤታው ድርቅ ሲከሰት የሚከናወኑ ድርጊቶችን መሥሪያ ቤታቸው እየፈፀመ መኾኑን ተናግረዋል። ለእንስሳት መኖ እና ድርቆሽ በአፋጣኝ ማቅረብ፣ የተዳከሙ ከብቶችን ለእርድ እንዲሁም የተቀሩትን ለንግድ ማዋሉ በአፋር መስተዳደር ተግባራዊ እየሆነ ነው ብለዋል። በድርቁ በቀን ምን ያኽል ከብቶች እያለቁ መኾናቸውን መናገር የሚቻለው መስክ ላይ እየተከናወነ ያለው ጥናት ሲጠናቀቅ መኾኑንም አክለው አስታውቀዋል።

አርብቶ አደሮቹ ችግራቸው እንዲታወቅላቸው በሚል ከትናንትና ወዲያ አንስቶ የሞቱ ከብቶቻቸውን በየአውራጎዳውን ጥግ እያመጡ በማስቀመጥ ላይ መሆናቸው ተገልጧል። የርዳታ ድርጅቶች፣ የአካባቢው እና መዓከላዊው አስተዳደር ለአፋር የከብቶች እልቂት ፈጣን ምላሽ እንዲሰጥ ነዋሪዎች አሳስበዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic