ድርቅ በሳህልና አፍሪቃ ቀንድ | ጤና እና አካባቢ | DW | 17.04.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ጤና እና አካባቢ

ድርቅ በሳህልና አፍሪቃ ቀንድ

የአምናው ድርቅ ገና ሳያገግም ሌላ ድርቅ የምስራቅ አፍሪቃ አካባቢን ስጋት ላይ እንደጣለ ተጠቆመ። በሌላ አንፃር ደግሞ በሳህል አካባቢ የሚኖሩ 15 ሚሊዮን ሰዎች ከፊታቸው የረሀብ አደጋ ተደቅኖባቸዋል።

ዳግም ድርቅ በአፍሪቃ

ዳግም ድርቅ በአፍሪቃ

የአስር ሺህዎችን ህይወት የቀጠፈው የአፍሪቃ ቀንዱ ረሀብ ከተከሰተ ገና አንድ ዓመትም አላስቆጠረ። ረሀቡ በተለይ ጦርነት እና ድርቅ ያዳቀቃት ሶማሊያን ወደ ከፍተኛ ቀውስ እና እልቂት ያመራት ቢሆንም፤ በአለም አቀፉ ማኅበረሰብ ርብርብ ከቁጥጥር ስር መዋሉ ይታወቃል። ታዲያ የአፍሪቃ ቀንዱ ድርቅ እና ረሀብ ገና ጋብ ማለቱ በተነገረ ማግስት አካባቢው ሌላ አሳሳቢ የድርቅ አደጋ እንደተጋረጠበት እየተነገረ ነው። ድርቁ የሚያስከትለውን አደጋ ለመቀነስ የአካባቢ ጥበቃ እና የተሻለ የግብርና ዘዬ ከፍተኛ ትኩረት እንደሚያሻቸው ከስምምነት ላይ ተደርሷል። ሰሞኑን ናይሮቢ ኬንያ ውስጥ በተደረገ ሰፊ ጉባኤ ኢትዮጵያን ጨምሮ አንዳንድ የአፍሪቃ ቀንድ ሐገራት አፋጣኝ ምላሽ የሚያሻው ድርቅ እንደተከሰተባቸው ተጠቅሷል። ሞኒካ ናጋጋ በኬንያ ኦክስፋምን ጨምሮ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ማኅበር አስተባባሪ ናቸው። ስጋት የተደቀነው ይላሉ፥

«አሁን ባለን መረጃ መሰረት ስጋቱ የተደቀነው የምስራቅ አፍሪቃ ማለትም ኬንያ፣ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ላይ ነው። እስካሁን ያነበብኩት መረጃ ይሄን ነው የሚያሳየው።»

የአካባቢው ሀገራትን የሚያስተሳስር የጋራ ዕቅድ ያለመኖሩ ጉዳይ አሁን በአፍሪቃ ቀንድ እየታየ ያለው አይነት ድርቅ በተደጋጋሚ እንዲከሰት ሰበብ ከሆኑ ምክንያቶች አንዱ ነው ብለዋል ሞኒካ ናጋጋ። ባለፈው ዓመት ብቻ ሶማሊያ ውስጥ የተከሰተው ድርቅ በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሀብ አለንጋ ተገርፈው እንዲያልቁ ሰበብ ሆኖ አልፏል። በአፍሪቃ ቀንድ ለተከሰተው ድርቅ ከወዲሁ ፈጣን ምላሽ ካልተሰጠው የከፋ ነገር ሊከሰት ይችላል ሲሉ ሞኒካ ናጋጋ አስጠንቅቀዋል። 

«የባሰ የከፋ ነገር ነው የሚከሰተው። ጭራሽ ማኅበረሰቡን ማዳከሙ አይቀርም። ስለዚህ ማድረግ ያለብን፤ በተቻለ መጠን በፍጥነት  ለኅብረተሰቡ ጥሪ ምላሽ መስጠት ነው። በአንዳንድ አካባቢዎች ድርቁ የከፋ በመሆኑ በዝናብ እጦት ስጋት ውስጥ ለወደቁ ሰዎች ከወዲሁ ርዳታ መሰጠት አለበት።»

የተራቆተ አካባቢ የሚበዛበት እና በረሃማነት የሚያጠቃው ይህ የአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ ለረዥም ጊዜ የዝናብ እጥረት ሲያጋጥመው ችግሩን ያባብሰዋል ሲሉም አክለዋል። ለአብነት ያህል በኢትዮጵያ የበልግ ዝናብ ለረዥም ጊዜ ሳይጥል መቆየቱ ድርቁን አባብሶታል እየተባለ ነው። ሞኒካ ያብራራሉ፥

አፋጣኝ ምላሽ ያስፈልጋል

አፋጣኝ ምላሽ ያስፈልጋል

«በአሁኑ ወቅት ከተጠበቀው በታች የሆነ ዝናብ እንደሚኖር ተገምቷል። እናም ድርቁ ምላሽ ካልተሰጠው ማኅበረሰቡ ያለበት ሁኔታ አስቸጋሪ እንደሆነ ነው የሚቆየው።»

ለዚህ በአዙሪት መልክ የአፍሪቃ ቀንድን ለሚደጋግማት ድርቅ ዘላቂ መፍትሄ ለማፈላለግ በርካታ የአካባቢው ሀገራት የመንግስት ተወካዮችን እና ዓለምአቀፋዊ ተቋማትን ያሳተፈ ጉባኤ በቅርቡ ናይሮቢ ውስጥ ተካሄዶም ነበር። የመንግስት ተወካዮቹ ከለጋሽ ሀገራት እና የልማት ድጋፍ ሰጪ ተቋማት ጋር ባደረጉት ውይይት ስር የሰደደውን የአፍሪቃ ቀንድ ድርቅ ወደፊት በተቀናጀ መንገድ ለመታገል አስፈላጊ ያሉትን ነጥቦች አንስተው ተወያይተውበታል።

«የጉባኤው አንዱ ጠንካራ ጎን የነበረው ከሠብዓዊ ርዳታ እና ከልማት አንፃር በተለያዩ አካላት መካከል ቅንጅት የመፍጠር አስፈላጊነቱ ላይ ትኩረት መስጠት ነው። በተጨማሪም በአፍሪቃ ቀንድ ድንበር ተሻጋሪ የሆነ የጋራ መርሀግብር የመንደፉ አስፈላጊነት አፅንኦት ተሰጥቶበታል።»

ይህ ድንበር ተሻጋሪ የጋራ መርሀ ግብር አስፈላጊ ነው የተባለበት ምክንያት በአፍሪቃ ቀንድ በተለይ ድርቅ የሚያጠቃቸው የኅብረተሰብ አካላት አርብቶ አደሮች በመሆናቸው ነውም ተብሏል። ታዲያ እነዚህ አርብቶ አደሮች ከብቶቻቸውን የሚያጠጡት ውሃ እና የግጦሽ ሳር ሲደርቅባቸው ለጊዜው ድንበር ተሻግረው ከአንዱ ሀገር ወደሌላው ሀገር እንዲንቀሳቀሱ ያስችላቸዋል ተብሏል መርሃግብሩ። ከዚያም በላይ ድርቅ የሚያስከትለውን እልቂት ለመቀነስ ያስችላሉ ተብለው እንደዘላቂ መፍትሄ የተወሰዱትን ነጥቦች ሞኒካ ናጋጋ ሲያብራሩም፥

«ዘላቂ መፍትሄ ሊሆን የሚችለው፤ ድርቁ በተደጋጋሚ የሚያጠቃውን የምስራቅ አፍሪቃ አካባቢ የረዥም ጊዜ የልማት ዕቅድ መደገፍ ነው። በተጨማሪም የመሰረተ-ልማት አውታሮችን ማስፋፋት እንዲሁም የአካባቢው ሰው አማራጭ እንዲኖረው በተለይ በትምህርቱ እና በጤናው ዘርፍ የመዋዕለ-ንዋይ ፍሰት የበለጠ እንዲኖር ማስቻል ያስፈልጋል።  የነዚህ ሁሉ ቁልፉ ሆኖ በጉባኤው አፅንኦት የተሰጠው በአካባቢው ሀገራት መካከል የተቀናጀ እና የተንሰላሰለ ፖሊሲ አስፈላጊ መሆኑ ላይ ነው። እንዲሁም የሲቪሉ ማኅበረሰብ እና የግሉ ዘርፍ ሚና አስፈላጊነትም ትኩረት ተሰጥቶታል።»

ሀገር በቀል ዛፎችን መንከባከብ እና ችግኞችን ተክሎ መንከባከብም ወሳኝ እንደሆነ ተጠቁሟል። በጉባኤው ኢትዮጵያን ጨምሮ የምስራቅ አፍሪቃ የልማት ትብብር ድርጅት በምህፃሩ ኢጋድ አባል ሀገራት ባለስልጣናት ተሳትፈዋል። የለጋሽ ሀገራት ተወካዮች፣ የጀርመን መንግስት፣ የዓለም ባንክ፣ የአፍሪቃ የልማት ባንክ እንዲሁም ለጋሽ ድርጅቶችም  ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ነበሩ። አድማጮች አሁን፥ በተመሳሳይ መልኩ የምዕራብ አፍሪቃ የሳህል አካባቢ ሀገራትን ስጋት ላይ ስለጣለው ሌላኛው የድርቅ ክስተት የምንለው ይኖረናል።

ድርቁን የተመለከተ ጉባኤ በኢጋድ

ድርቁን የተመለከተ ጉባኤ በኢጋድ

ሙዚቃ፥

ኒጀር እና ቻድን ጨምሮ ስምንት ሀገራትን የሚያካልለው የሳህል አካባቢ ረሀብ ከቀን ቀን ከፍተኛ ስጋት አሳድሯል። በአካባቢው 15 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ የምግብ እጥረት እንዳጋጠመው የተባበሩት መንግስታት ይፋ አድርጓል። ሬኔ ዶሎ፥ የተባበሩት መንግስታት የሠብዓዊ ርዳታዎች አስተባባሪ ቢሮ በምህፃሩ ኦቻ፤ የምዕራብ እና መካከለኛው አፍሪቃ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ናቸው። ከድርቁ ባሻገር ማሊ ውስጥ የተከሰተው ግጭት የሳህል አካባቢ ቀውስ እንዲባባስ አድርጓል ባይ ናቸው።

«በሁለት ምክንያቶች ሁኔታው በጣም አሳሳቢ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ድርቁን ተከትሎ እስካሁን የደረሰን የሠብአዊ ርዳታ በቂ አይደለም። ከድርቁ በተጨማሪ የማሊ ቀውስ አለ። ያን ተከትሎም ከማሊ የሚወጡ ስደተኞች እና እዛው ማሊ ውስጥ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚንቀሳቀሱ ተጎጂዎች ሁኔታው እንዲባባስ አድርገዋል። ባሁኑ ወቅት ፈፅሞ እነሱ ጋር መድረስ አልተቻለም። ስለዚህም በሳህል አካባቢ በሚገኙ አንዳንድ ሀገራት ጣምራ የሆነ ቀውስ ነው የተከሰተው።»

በእርግጥ አፍሪቃ ውስጥ ከድርቁ ባሻገር የአየር ንብረት መዛባት፣ የደን መጨፍጨፍ፣ በቂ የግጦሽ መሬት እና ውሃ መታጣት ለረሀቡ መንስኤ ተደርጎ ይወሰዳል። የጎሰኞች ነፍጥ አንስቶ መቆራቆዝ፣ እንዲሁም ዘላቂ መፍትሄን መንደርደሪያው አድርጎ የሚተገበር ዕቅድ በስፋት ያለመኖር ደግሞ ችግሩን ያባብሳሉ ተብለው ከሚጠቀሱ ምክንያቶቹ ጥቂቶቹ ናቸው። ሚሊዮኖችን ለረሀብ በዳረገው የሳህል አካባቢ ድርቅ የተነሳ የሞቱ ሰዎች ካሉ ብለን ሬኔ ዶሎን ጠይቀናቸው ሲያብራሩ፥

«እስካሁን በረሀብ ምክንያት የሞቱ ሰዎች እንዳሉ በእርግጥ የደረሰን መረጃ የለም። በሳህል አካባቢ በየዓመቱ እድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ወደ 600 ሺህ ገደማ የሚጠጉ ህፃናት ይሞታሉ። ከነዚህም መካከል ገሚስ ያህል ህፃናቱ የሚሞቱት ከበቂ ምግብ እጦት ጋር በተያያዘ እንደሆነ እንገምታለን። ያን ስንል ምግብ ከማጣት ብቻ የመጣ  ነው ማለታችን ግን አይደለም። የንፁህ ውሃ አቅርቦት ባለመኖሩ ከሚፈጠር የጤና ቀውስ ጋርም ይያያዛል። ስለዚህ ስለሟቾቹ ህፃናት ቁጥር ስንነጋገር መጠንቀቅ አለብን፤ ምክንያቱም የሞቱ መንስኤ በቀጥታ ድርቅ ሳይሆን፤ በተዘዋዋሪ በቂ ምግብ ባለማግኘት የመጣ ነውና።»

የሳህል አካባቢም አደጋ ላይ ነው

የሳህል አካባቢም አደጋ ላይ ነው

የሳህል አካባቢ ድርቅ እንዲባባስ ያደረገው ልክ እንደ አፍሪ ቀንዱ ሁሉ ወቅቱን ጠብቆ መምጣት የነበረበት ዝናብ በመዘግየቱ እንደሆነ ተገልጿል። የተቀናጀ ዘላቂ የመሬት እና አካባቢ  አያያዝ እጦትም ሌላኛው ሰበብ ተደርጎ ተወስዷል። በዚህም አለ በዚያ በሳህል አካባቢ ለተከሰተው ድርቅ ፈጣን ምላሽ ካልተሰጠው ይላሉ ሬኔ ዶሎ፥

«ይህ ዓለም አቀፋዊ ዕቅድ ዓለም አቀፋዊ የገንዘብ ድጋፍ ያሻዋል። አሁን ችግራችን የሠብአዊ ርዳታ ድርጅቶች ከሚያስፈልጋቸው የገንዘብ ድጋፍ 40 በመቶውን አለማግኘታቸው ነው። ያ ማለት በዚህ መልኩ ከቀጠልን እና ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ካልተደረገ በቀጣይ ሳምንት ሁኔታው የበለጠ ሲባባስ ለችግሩ ምላሽ መስጠት ያዳግተናል ማለት ነው።»

በአፍሪቃ ቀንድ እና በሳህል አካባቢ ሀገራት የተከሰተው አደገኛ ድርቅ ዋነኛ ሰበብ የዝናብ እጥረት ቢሆንም ዝቅተኛ ዝናብ ባለባቸው ሀገራት የሚገኙ ገበሬዎች መሬታቸው እንዲያገግም የሚያስችል የግብርና ዘዬ መከተል ያስፈልጋቸዋል ተብሏል። ከምንም በላይ መንግስታትን፣ ለጋሾችን እና ህብረተሰቡን ያሳተፈ ዘላቂ መፍትሄ አስፈላጊነት ወሳኝነቱ እያነጋገረ ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic