ድርቅና የሶማሌ ክልል የአርብቶ አደሮች | ኢትዮጵያ | DW | 12.04.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

ድርቅና የሶማሌ ክልል የአርብቶ አደሮች

ኢትዮጵያ ዉስጥ ኤሊንኞ የተባለው የአየር ጸባይ ክስተት ባስከተለው ድርቅ ከተጎዱ አካባቢዎች አንዱ አርብቶ አደሮች የሚገኙበት የሶማሌ ክልል ነው። በክልሉ በተከሰተው ድርቅ በርካታ ከብቶች መሞታቸው የህዝቡን ኑሮ አዛብቷል። ከረዥም ዓመታት ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ የተባለው ይኽው ድርቅ ልዩ ስም ተሰጥቶታል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:38
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:38 ደቂቃ

ድርቅና የሶማሌ ክልል የአርብቶ አደሮች

ወደ አካባቢው የተጓዘው የዶቼ ቬለው ጀምስ ጀፍሪ እንደዘገበው በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የሚኖሩት አርብቶ አደሮቹ የዳህቦ ቤተሰብ ከነበራቸው ከብቶች አሁን የተረፉት ሦስት ፍየሎች ብቻ ናቸው። በፊት 10 ግመሎች፤ 200 ፍየሎችና በጎች ነበሯቸው። የከብቶቹ ቁጥር ሲመናመን ቤተሰቡ እንደ ቀድሞው የአርብቶ አደር ሕይወት መምራት አቁሟል። ወደ ቀድሞው አኗኗሩ መመለሱም ያጠራጥራል። ይህን ያስከተለው አካባቢውን ደጋግሞ የመታው ድርቅ ሲሆን ከጎርጎሮሳዊው 2014 አጋማሽ አንስቶ በአካባቢው በሦስት የዝናብ ወቅቶች ዝናብ አልጣለም። በአሁኑ ጊዜ የ 37 ዓመትዋ ዳህቦ ባለቤትዋና 8 ልጆችዋ ከድሬዳዋ በስተሰሜን ወደ 75 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ድርቅ ላፈናቀላቸው በተዘጋጀ መጠለያ ውስጥ ነው የሚገኙት። ፈዴቶ ወደ ተባለው ወደዚሁ መንደር ከመጡ 8 ወር ሆኗቸዋል። ከጭቃ የተሠራ አነስተኛ ጎጆ ውስጥ ነው የሚኖሩት። የ45 ዓመቱ ባለቤትዋ ጊርቡህ የሌላ ተፈናቃይ ቤተሰብ ጎጆ ሥራ ሲያግዝ ቆይቶ እጁ በጭቃ እንደተለወሰ ወደ ቤቱ መጣ።
«በጣም የሚያስጨንቀኝ ነገር እዚህ መታሠሬ ነው። ለዚህ የተዳረግኩት ከብቶቼን በማጣቴ ነው። ድርቁ በዚህ ብቻ አያበቃም። እኛም ከዚህ የምንሄድ አይመስለኝም።»ይላል ጊርቡ


የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልልን የመታው ድርቅ ከእስከ ዛሬዎቹ የከፋው መሆኑን ከዚህ በፊት በአካባቢው ያጋጠመውን ድርቅ ያዩ አዛውንቶች ይናገራሉ። እነርሱ እንደሚሉት ድርቁ የክልሉ ነዋሪ ሕይወት የሆኑትን ከብቶች ፈጅቷል። በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በስተሰሜን በሚገኘው በሲቲ ዞን ብቻ ከ600 ሺህ በላይ ከብቶች እንዳለቁ ይገመታል። ፈዴቶ የሚገኙት የ65 ዓመቱ አዛውንት ኤልትሴ ሙሰ ባህ ድርቁ አስከፊ ከመሆኑ የተነሳ ልዩ ስም ሰጥተነዋል ይላሉ።
«ይህን የመሰለ ድርቅ አጋጥሞኝ አያውቅም። በሌሎቹ ድርቆች ለኛ በቂ የሆኑ ከብቶች ይተርፉ ነበር። በአሁኑ ግን ይህ አልሆነም። ድርቁን ሙልያ ብለነዋል። በምድር ያለ ነገርን በሙሉ የሚያጠፋ ማለት ነው ።»
በመላው ኢትዮጵያ 10 ሚሊዮን ሰዎች በድርቅ ተጎድተዋል። በአሁኑ ጊዜ መንግሥት በሚያካሂደው የምግብ ዋስትና የሴፍቲ ኔት መርሃ ግብር 7.9 ሚሊዮን ሰዎች እየተረዱ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ዓመት በጥቅምት ወር የእርዳታ ጥሪ ካቀረበ

ወዲህ ዓለም አቀፍ አጋሮችና የእርዳታ ድርጅቶች የማስጠንቀቂያ ደውል በማሰማት ላይ ናቸው ፈዴቶን በመሳሰሉ አካባቢዎች ሰብዓዊ ቀውሱን ለማቋቋም እየተንቀሳቀሱ ነው። ሴቭ ዘ ችልድረን የተባለው ግብረ ሰናይ ድርጅት ሃላፊ ጆን ግራሃም የእርዳታ ጥገኝነትን ለማስቀረት በመጣር ላይ ባለችው በኢትዮጵያ ወደፊት ሁኔታዎች ይሻሻላሉ የሚል ተስፋ አላቸው።
« በርግጥ ኢትዮጵያ ባለፉት 10 ዓመታት ጥገኝነትን ለመቀነስ ብዙ ለውጥ አስመዝግባለች። ይህ ደግሞ ሂደቱን አደናቅፎታል። ነገር ግን ይህ የአየር ፀባይ ለውጥ ባለፉት 50 ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ ነው። እንዲህ ዓይነት ነገሮች ያጋጥማሉ። መጪው ድርቅ ያን ያህል የከፋ እንደማይሆን ህዝቡም የጀመረውን ልማት ሊቀጥል እንደሚችል ተስፋ እናደርጋለን ። »
ይሁንና አሁን ከሶማሌ ክልል ነዋሪዎች ብዙዎች የእርዳታ ጥገኛ ሆነዋል፤ ንጹሕ የመጠጥ ውኃ ለማግኘት ብዙ የእግር መንገድ መሄድ ይኖርባቸዋል። በክልሉ ባለፈው ሳምንት ዝናብ መጣሉ በጎ ተስፋ ቢሰጥም ያስከተለው ጎርፍ የሰው ሕይወት አጥፍቷል። ይህን መሰሉ ዝናብ ድርቁ ያዳከማቸውን ከብቶች ለበሽታ ማጋለጡ ደግሞ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው ሆኗል።

ጀምስ ጀፍሪ/ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic