ድሬዳዋ ተሥፋ የጣለችበት ኢንዱስትሪ ፓርክ | ኤኮኖሚ | DW | 01.11.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

ድሬዳዋ ተሥፋ የጣለችበት ኢንዱስትሪ ፓርክ

የኢትዮ-ጅቡቲ የምድር ባቡር ሲከስም አብራ የተቀዛቀዘችው ድሬዳዋ የኢንዱስትሪ ፓርክ ገንብታ ልታስመርቅ ዝግጅት ላይ ትገኛለች። ለጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት አምራቾች፣ የምግብ አቀነባባሪዎች እና ተሽከርካሪ ገጣጣሚዎች የታቀደው ነው። ከዕለት ወደ ዕለት የሚያሽቆለቁለው ፖለቲካ ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ይገባሉ ተብለው የሚጠበቁ ባለወረቶችን አያሸሽ ይሆን?

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:15
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
11:15 ደቂቃ

ለ15 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል

የኢትዮጵያ መንግሥት በ125 ሚሊዮን ዶላር በድሬደዋ ከተማ ያስገነባው የኢንዱስትሪ ፓርክ በዚህ ወር ሊመረቅ ቀጠሮ ተይዞለታል። ግንባታውን የሚያከናውነው የቻይና ሲቪል ምኅንስድስና ግንባታ ኩባንያ (CCECC) ነው። ወጪውን የሸፈኑት የኢትዮጵያ መንግሥት እና የቻይናው ኤክዚም ባንክ ናቸው። በ150 ሔክታር መሬት ላይ የሚገነባው የመጀመሪያው ምዕራፍ ባለፈው መስከረም ወር ይጠናቀቃል የሚል እቅድ ተይዞለት ነበር። ሙሉ ግንባታው ሲጠናቀቅ ለ68,000 ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ አምራቾች በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ሥራ ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል። የድሬደዋ ከተማ ከንቲባ አቶ ኢብራሒም ኡስማን እንደሚናገሩት ይኸ የመጀመሪያው ምዕራፍ ብቻ ነው። 

"አጠቃላይ የመሬት ስፋቱ 4186 ሔክታር ነው። የመጀመሪያው ምዕራፍ በ150 ሔክታር ላይ በአሁኑ ጊዜ እየተገነባ ያለው በያዝንው ወር መጨረሻ አካባቢ ያልቃል ተብሎ ይጠበቃል። ኢዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በሚባለው የመንግሥት ተቋም የሚገነባ ነው። ሁለተኛው ቻይናውያን ራሳቸው ኢንቨተሮችን በማፈላለግ በጋራ ከፌደራል መንግሥት ጋር የሚገነቡት ወደ 1,000 ሔክታር ቦታ አዘጋጅተን ሰጥተናል። ይኼም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግንባታ የሚጀምሩበት ሁኔታ ይኖራል። እስካሁን ወደ 16 ሔክታር የቢሮ እና ሌሎች ማሳያ ቦታዎችን በራሳቸው 1,000 ሔክታር ላይ ሰርተዋል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ደግሞ ወደ ሙሉ ሥራ ይገባሉ ብለን እናስባለን። ለስደተኞች ታሳቢ የሚደረግ ደግሞ አለ። መንግሥት እየገነባ ካለው የኢንዱስትሪ ፓርክ አጠገብ የሚሰራ ሌላ ፓርክ ይኖራል ተብሎ ይታሰባል።"

የኢትዮጵያ መንግሥት የማምረቻ እና የውጭ ንግዱን ዘርፍ ለማጠናከር እስከ ሚቀጥለው አመት ሰኔ ወር ድረስ የኢንዱስሪ ፓርኮችን ቁጥር ወደ 15 ለማድረስ አቅዷል። የማምረቻው ዘርፍ በጎርጎሮሳዊው 2025 ዓ.ም. ከአጠቃላይ የአገሪቱ የምርት መጠን 20 በመቶ ከውጭ ንግዱ ደግሞ 50 በመቶ ድርሻ እንዲኖረውም አስቧል።

"ድሬዳዋ በምሥራቁ አካባቢ ከዚህ በፊትም በኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ ቀድማ ትልቅ አሻራ የነበራት ከተማ ነች።" የሚሉት አቶ ኢብራሒም ትሩፋቱ ለከተማቸው ይደርሳል የሚል እምነት አላቸው። "በሕገ-ወጥ ንግድ እንቅስቃሴ በመኖሩ፤ የነበሩ ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች እና የባቡር እንቅስቃሴ በመቆሙ አጠቃላይ የነበረው ኤኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ቀዝቅዞ የነበረ እንደሆነ እናውቃለን። ያንን ለመመለስ አሁን እየተገነባ ያለው የኢንዱስትሪ ፓርክ ትልቅ እድገት እና የኤኮኖሚ መነቃቃት ይፈጥራል ብለን ነው የምናስበው።" ሲሉ ያክላሉ። 

የጎርጎሮሳዊው 1960ዎቹ የድሬዳዋ ኤኮኖሚ ያበበባቸው ዓመታት ነበሩ። 784 ኪ.ሜ. ይረዝም የነበረው የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር እና በከተማዋ ብቅ ብቅ ያሉት አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ለከተማዋ የኤኮኖሚ እንቅስቃሴ የላቀ ሚና ነበራቸው።  
"ድሬዳዋ የባቡር መስመሩ ከመከፈቱ ጋር ተያይዞ ነው የተቆረቆረችው። ከዛ በመቀጠል የድሬዳዋ የስሚንቶ ፋብሪካ፣ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ የድሬዳዋ ሌሎች ፋብሪካዎችም ነበሯት።" የሚሉት የምጣኔ ሐብት ባለሙያው አቶ ሲሳይ ጉግሳ ናቸው። 

"በኢንደስትሪ ብዛት አንፃር ኢትዮጵያ ካሏት ከተሞች በርካታዎቹን የያዘች ከተማ ነበረች። ወደ በኋላ ግን ንግዱ ብቻ አይሎ የከተማዋ ነዋሪ ገቢ ከእነዚህ ፋብሪካዎች ከሚያገኘው ደሞዝ በተጨማሪ የባቡር ንግዱ የኮንትሮባንድ ንግዱ የሚያመጣው ገቢ ነው ያኖረው የነበረው። ይኸንንው ንግድ ደግሞ ወደ መሐል ከተሞች ለማመላለስ ከመሐል ከተማ የሚመጣ ነጋዴ አገልግሎት በመስጠት። ይኼ ነው ዋናው የኤኮኖሚ መሰረቷ የነበረው።"

ከ30 አመታት ገደማ በፊት ድሬዳዋ በኮንትሮባንድ ወደ ኢትዮጵያ በሚገቡ ሸቀጦቿ ልቃ ትታይ እንጂ እንቅስቃሴዋ አልዘለቀም። የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ምንዛሪ ፖሊሲ ለውጥ ሲያደርግ ሕገ-ወጡ ንግድ ተቀዛቀዘ። ከተማዋም የነበራትን ሥልታዊ ጥቅም አጣች። ላውራ ልይኮቭስካ ከዓመታት በፊት ይፋ ባደረጉት ጥናት የድሬዳዋ ንግድ እንቅስቃሴ መዳከም ድኅነትን በጎርጎሮሳዊው 1994 ዓ.ም. ከነበረበት  18.2 በመቶ በሦስት አመታት ውስጥ በእጥፍ እንዲያሻቅብ ማድረጉን አትተዋል። 

"መንግሥት ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ የኮንትሮባንድ ንግዱን የማዳከም ሥራ ተሰርቷል። ከዛ በተጨማሪ የባቡር መስመሩም አለመኖር የኮንትሮባንድ ንግዱን አቆመው። ከዚህ ጋር ተያይዞ የሥራ አጥ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። አንዳንድ ቁጥሮች እንደሚያሳዩት 26% የከተማዋ ነዋሪ ሥራ አጥ ነው።" ሲሉ አቶ ሲሳይ ይናገራሉ። ከመሐል አገር ለሚመጡ እንግዶች ቀዝቃዛ ውሐ ከመሸጥ ጀምሮ የከተማዋ ነዋሪዎች ገቢ ከባቡር ትራንስፖርት አገልግሎቱ ጋር የተቆራኘ እንደነበር የሚናገሩት አቶ ሲሳይ "የባቡር መስመሩ መቆም የድሬዳዋ የኤኮኖሚ እንቅስቃሴን በከፍተኛ ሁኔታ አቀዛቅዞታል።" ሲሉ ያክላሉ። 


በቅርቡ በመቀሌ እና በኮምቦልቻ ከተሞች የተመረቁትን ጨምሮ ሰባት የኢንዱስትሪ ፓርኮች በሥራ ላይ ናቸው። 190 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የሆነበት የአዳማ የኢንዱስትሪ ፓርክም ከድሬደዋው ጋር በዚህ ወር ሊጠናቀቅ እቅድ ተይዞለታል። ሁለቱ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በሁለት የሥራ ፈረቃ እስከ 50,000 ሠራተኞች ይቀጥራሉ ተብሎላቸዋል። በድሬደዋው የኢንዱስትሪ ፓርክ የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት፣ የምግብ ማቀነባበሪያዎች እና የተሽከርካሪ መገጣጠሚያዎች ይገቡበታል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከገነባቸው እና በእቅዱ ከያዛቸው መካከል ድሬዳዋ ለጅቡቲ ወደብ ያላት ቅርበት ተመራጭ እንዳደረጋት የምጣኔ ሐብት ባለሙያው ይናገራሉ። "ርቀቷ 380 ኪ.ሜ. አካባቢ ነው ። ሌሎቹ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ራቅ ራቅ ያሉ ቦታዎች ናቸው።" የሚሉት አቶ ሲሳይ ዋናው ትኩረት በጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ምርት ላይ ነው ብለዋል። 

"ከአፋር አካባቢ የሚመረተው ጥጥ ቀደም ሲልም ወደ ድሬ ዳዋ ይመጣ ነበረ። አሁንም ወደ ድሬዳዋ በጥሬ እቃነት መጥቶ «ፕሮሰስ» ተደርጎ የጨርቃ ጨርቅ ማምረቻው የሚያወጣው ውጤት ምቹ በሆነ ቦታ ላይ ተመርቶ ወደ ውጪ ይላካል።"


ድሬዳዋ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዕለታዊ በረራ ከሚያከናውንባቸው ከተሞች አንዷ ናት። በቅርቡ ሥራ ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀው የባቡር ሃዲድም በከተማዋ ከተገነባው የኢንዱስትሪ ፓርክ አቅራቢያ ያልፋል። የመንገድ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል እና የውኃ መሠረተ-ልማቶች ለማቅረብ የፌድራል መንግሥቱ ግንባታ እያከናወነ መሆኑን አቶ ኢብራሒም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ውጥኑ ከሰመረለት በደብረ ብረሃን፣ አራርቲና ባህርዳር ተጨማሪ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለመገንባት አቅዷል። መንግሥት የመረጠው መንገድ ከአፍሪቃ ቀዳሚ አምራቾች ጎራ ያደርሰኛል የሚል እምነትም አለው። በርከት ያሉ አምራቾችን በአንድ የሚያሰባስቡት ማዕከላት በፍጥነት ለሚያድገው የሕዝብ ቁጥር የሥራ ዕድል በመፍጠሩም ረገድ ተስፋ ተጥሎባቸዋል። የምጣኔ ሐብት ባለሙያው አቶ ሲሳይ ጉግሳም የድሬደዋው ከግንባታ ሒደቱ ጀምሮ ለበርካቶች የሥራ እድል መፍጠሩን ታዝበዋል።


"አሁን ባለው ሁኔታ እየተገነባ እያለ እንኳን 3,300 ያህል መካከለኛ ክሕሎት ያላቸው እና የቀን ሠራተኞችን ቀጥሮ እያሰራ ነው። ከወር በኋላ ደግሞ የተባሉት 15 የማምረቻ መጠለያዎች ሥራ ሲጀምሩ 15,000 ሥራ አጦችን ይቀንሳል ተብሎ እየታሰበ ነው። ይህ አንደኛው ምዕራፍ ላይ ብቻ ነው። በምዕራፍ አንድ 150 ሔክታር እየተጠቀመ ነው። በቀጣይ ግን በእቅዱ የተከለለው የመሬት መጠን 1,500 ሔክታር ነው። መንግሥት ግን አሁን ሊያሰፋ ያሰበው እስከ 4,000 ሔክታር ድረስ ነው። በዚያ መጠን ሲሰራ ምን ያክል የሥራ አጥ ቁጥር ሊቀንስ እንደሚችል መገንዘብ ይቻላል።" 


ከዕለት ወደዕለት የሚያሽቆለቁለው የኢትዮጵያ መረጋጋት እና መፍትሔ ያጣው የፖለቲካ ውጥንቅጥ ግን በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ እጣ-ፈንታ ላይ ፈተና የሚሆን ይመስላል። በምሥራቅ ኢትዮጵያ በሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልሎች መካከል የተቀሰቀሰው ፖለቲካዊ ሽኩቻ የማጓጓዣ እና የዕለት ተዕለት የንግድ እንቅስቃሴዎችን አስተጓጉሏል። አሽከርካሪዎች እና ነጋዴዎች ስለ ደኅንነታቸው ሥጋት እንደተጫናቸው ናቸው። እስካሁን ድሬዳዋ ተቃውሞ እና ኹከት ባይገጥማትም ትኩሳቱ ግን አልተለያትም። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ወደ ድሬዳዋ የኢንዱስትሪ ፓርክ የሚመጡ ባለወረቶችን እምነት አያሸሽ ይሆን? "በእኛ አካባቢ ምንም አይነት ችግሮች የሉም" የሚሉት አቶ ኢብራሒም የአካባቢው ሰላም እና መረጋጋት ሊጠበቅ እንደሚገባ ገልጠዋል። 

የምጣኔ ሐብት ባለሙያው አቶ ሲሳይ ጉግሳም ወቅታዊው ፖለቲካ የከፋ ተፅዕኖ ያሳድራል የሚል እምነት የላቸውም። ወደ ኢትዮጵያ የሚያቀኑ ባለወረቶች ዋስትና እንደሚያስፈልጋቸው ግን አቶ ሲሳይ አበክረው ይናገራሉ። 

"አሁን የተፈጠረው ክስተት ያን ያህል ተፅዕኖ ያሳድራል ብዬ በግሌ አላምንም። ከዛ ውጪ ግን ዋስትና ሊኖራቸው ይገባል የሚል እምነት አለኝ። የውጭ መዋዕለ ንዋይ ሲኖር መንግሥት ኪሳራ ቢኖር እንደዚህ አይነት ክስተቶች የሚያመጡትን ኪሳራ አካክሳለሁ ማለት አለበት። ስለዚህ ዋስትናዎች እስካሉ ድረስ ኢንቨስትመንቱ ይኖራል የሚል {እምነት} አለኝ። ግጭቱ ግን ኢንቨስትመንቱ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል የሚል እምነት የለኝም።"

እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች