ድምፅ አልባዉ ሱናሚ | የጋዜጦች አምድ | DW | 23.06.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

ድምፅ አልባዉ ሱናሚ

ኤችአይቪ ኤድስ በዓለም እያደረሰ የሚገኘዉ ጥፋት ከባድ ማዕበል የሚያስከትለዉን መጠን ቢበልጥ እንጂ አያንስም። ከዚሁ ጋር በተያያዘም የወላጅ አልባ ህፃናት ቁጥር እየጨመረ መሄዱ እየተነገረ ነዉ።

በሽታዉ በተለይ በአህጉራችን አፍሪካ ብዙዎች ህፃናትን ያለወላጅ ማስቀረቱ ሳይበቃ በቫይረሱ የተያዙት ቁጥራቸዉ ተበራክቶ የሚያገኙት እንክብካቤ በአቅም ማነስ ለሁሉም አለመዳረሱ ዋና ጉዳይ ሆኗል። ችግሩ ጎልቶ በወጣባቸዉ የደቡብ አፍሪካ አገራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪዎች ከሚችሉት በላይ ለፈተና ተዳርገዋል።
በዚህ ድምፅ አልባ ሱናሚ ከሰሃራ በታች በሚገኙ አገራት ብቻ እንኳን ከወላጆቻቸዉ አንዳቸዉን ወይም ሁለቱንም ያጡ ህፃናት ቁጥር 12ሚሊዮን መድረሱን ከዓለም የቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ፌዴሬሽን የተገኘዉ መረጃ ያሳያል።
እስከ መጪዉ የፈረንጆቹ 2010ዓ.ም. ድረስም በዕጥፍ ይጨምራል የሚል ስጋት አለ ከወዲሁ።
ከነዚህ በኤች አይቪ ኤድስ ወላጆቻቸዉን ካጡ ልጆች መካከልም 4,132,000 የሚሆኑት የሚገኙት በደቡቡ የአፍሪካ ክፍል ነዉ።
የልጄ ልጆች ናቸዉ። እነዚህን ሶስት ልጆች ጥላብኝ እሷ አልፋለች። ጠዋት ስነሳ የሚያሳስበኝ በምኔ ላስተምራቸዉ የሚለዉ ጭንቀት ነዉ ይላሉ ሶስት የልጅ ልጆቻቸዉን በሌለ አቅም ለማሳደግ የተዳረጉት ሴት አያት።
አብዛኛዎቹ የእነዚህ አገራት መንግስታት ህዝቡን ስለበሽታዉ በማሳወቅ፤ የመከላከያ ዘዴ በማስተማርና የእድሜ ማራዘሚያ መድሃኒት በማቅረብ ተግባር ላይ በመጠመዳቸዉ ወላጅ አልባ የሆኑት ልጆች ጉዳይ በቂ ትኩረት እንዳላገኘ ይነገራል።
በዚህ መካከል የተፈጠረዉን ክፍተት ለመሙላት ሃላፊነቱ በአያቶችና በመንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጫንቃ ላይ ወድቋል።
ለምሳሌ በደቡብ አፍሪካ በጎ ፈቃደኞችን በመያዝ ከጆሃንስበርግ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ በዘልማድ የጥቁሮች መንደር በሚባለዉ ሱዌቶ 126 ልጆችን መንከባከብ በሚያስችል መልኩ አደራጅቷል።
ይህን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሚለግሱት መካከል ቪክቶሪያ ሲቢስ እንደሚሉት ከሶስት ዓመታት በፊት ህመምተኞችን መጎብኘት እንደጀመሩ ያስተዋሉት ህፃናት በከፍተኛ ደረጃ ለጉዳት መዳረጋቸዉን ስለነበር እነሱን መንከባከብ ጀመሩ።
ሆኖም ግን ይላሉ ሲቢስ እነዚህ ብቻ አይደሉም እንክብካቤና ድጋፍ የሚፈልጉት ብዙ ናቸዉ አቅማችን አይፈቅድም ከዚህ በላይ እንዳንጨምር።
ወላጆቻቸዉን ከማጣት በተጨማሪ አብዛኛዎቹ ልጆች ከቫይረሱ ጋር በተገናኙ በሽታዎች የሚሰቃዩ በመሆናቸዉ የችግሩ መደራረብ እንደእሳቸዋ ላሉት የበጎ ፈቃድ አገልጋዮች ለጭንቀት ዳርጓል።
አንዳንዴም ይላሉ ሲቢስ ምግብ ከየቤታችን ለልጆቹ ይዘን እንሄዳለን በተለይም መድሃኒቱን ለሚወስዱት ልጆች። ምክንያቱም ከቫይረሱ ጋር በተገናኘ መድሃኒት የሚወስዱ ደህና ምግብ ያስፈልጋቸዋል መድሃኒት ከመዉሰዳቸዉ በፊት።
በጣም ተስፋ የሚያስቆርጠዉ አጋጣሚ ደግሞ ይላሉ ሲቢስ እናትና ልጅ የታመሙበት ቤተሰብ ሲያጋጥም ነዉ።
በዚህ ጊዜ እናት ልጇን መርዳት የማትችልበት አስጨናቂ ሁኔታ ይፈጠራል እኛንም ተስፋ ወደመቁረጥ ይመራናል።
የደቡብ አፍሪካ የቀይ መስቀል የበላይ እንደሚሉት በአካባቢዉ ባሉ አገራት ባጠቃላይ 700,000 ህፃናት ቫይረሱ በደማቸዉ ዉስጥ መኖሩ ተረጋግጧል።
የአገሪቱ ቀይ መስቀል የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪዎችን ተግባር ለማገዝ የሚያስችል በኤችአይቪ ዙሪያ የሚሰሩ ድርጅቶችን አቀናጅቶ መንቀሳቀስ ጀምሯል።
በተጨማሪም ለልጆቹ የትምህርት ቤት ክፍያና አልባሳት ከግል ድርጅቶችም ሆነ ከለጋሾች የሚገኝበትን ሁኔታ በማመቻቸት ላይ መሆኑንም እየገለጸ ነዉ።
በቫይረሱ የተያዙትን ብዛትና መድሃኒቱንም ለእነሱ ለማዳረስ ያለብንን እጥረት ሳየዉ ይላሉ ኃላፊዋ አደጋዉ ከሱናሚ ማዕበል የሚተናነስ አደጋ እንዳልሆነ ተረድቻለሁ።