ድምጻዊ እና ማሲንቆ ተጫዋቹ ብርሀን ሞላ | ባህል | DW | 27.05.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

ድምጻዊ እና ማሲንቆ ተጫዋቹ ብርሀን ሞላ

በመዲና ዘለሰኛ የካሴት ሥራውን አንድ ያለው ብርሀን ፣ «ጀምበሬ» ፣ «አማን አደረ ወይ»፣ «ስንዴ ድብልቁ» የተሰኙትን አልበሞች አሳትሟል። ከመካከላቸው ስንዴ ድብልቁ ይበልጥ ተዋጥቶልኛል ህዝብም ወዶልኛል ይላል።ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ብርሀን ለሌሎች ድምጻውያን ዜማ እና ግጥም መስጠት ጀምሯል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:46

ድምጻዊ እና ማሲንቆ ተጫዋቹ ብርሀን ሞላ

የ37 ዓመት ጎልማሳ ነው። ሙዚቃን ሙያው ካደረገ ከ20 ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል። ከልጅነቱ አንስቶ እስካሁን ያልተለየው ማሲንቆ መታወቂያው ነው። እናትም አባትም ሆኖ ያሳደገኝ ለሚለው ለዚህ የባህል ሙዚቃ መሣሪያ ትልቅ ቦታ ነው የሚሰጠው። ብርሃን ሞላ ይባላል።

ብርሀንን ከህዝብ ጋር ይበልጥ መታወቅ የጀመረው «መዲና ዘለሰኛ» የተሰኘውን መንፈሳዊ ዜማዎችን ያካተተውን የመጀመሪያ ካሴቱን ካሳተመ በኋላ ነው። ከ«መዲና ዘለሰኛ» በኋላ ሌሎች ሦስት የባህል ሙዚቃ አልበሞች አውጥቷል።

ብርሀን አዲስ አበባ ሲመጣ 17 ዓመቱ ነበር። መጀመሪያ ኮተቤ የሚገኝ ቡና ቤት ውስጥ ነበር የሚዘፍነው። ከዚያም በሀገር ፍቅር ቲያትር በነጻ በማገልገል ላይ ሳለ ክስታኔ በሚባል ባንድ ውስጥ ተቀጥሮ መሥራት ጀመረ። እንዲህ እንዲህ እያለ ነው ካሴት ወደማሳተም የተሻገረው። በመዲና ዘለሰኛ የካሴት ሥራውን አንድ ያለው ብርሀን ፣ «ጀምበሬ» ፣ «አማን አደረ ወይ»፣ «ስንዴ ድብልቁ» የተሰኙትን አልበሞች አሳትሟል። ከመካከላቸው «ስንዴ ድብልቁ» ይበልጥ ተዋጥቶልኛል፤ ህዝብም ወዶልኛል ይላል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ብርሀን ለሌሎች ድምጻውያን ዜማ እና ግጥም መስጠት ጀምሯል።  በአፍላ የወጣትነት እድሜው ወደ ሙዚቃው ዓለም የገባው ብርሀን በማሲንቆ ተጫዋችነት ብዙ ዓመት ቢሰራም ይበልጥ የታወቀው እና የተሻለ ገቢም ማግኘት የጀመረው መዝፈን ከጀመረ በኋላ መሆኑን ይናገራል። ይሁን እና የሁሉም መሠረት የሁሉም መነሻ ለሆነው ማሲንቆ ግን ዛሬም ወደፊትም የሚሰጠው ቦታ ላቅ ያለ ነው።

የተለየ ድምጽ ለሚያወጣው ለማሲንቆ ትኩረት ሊሰጥ ተተኪ ባለሞያም ማፍራቱ ሊታሰብበት እንደሚገባ ብርሀን ያሳስባል። ከወደፊት እቅዶቹ መካከል አንዱ፣የማሲንቆ ማስተማሪያ ትምህርት ቤት መክፈት ነው። ወደፊት ሌሎች ሙዚቃዎችንም የማሳተም እቅድ አለው። ብርሀን ባለትዳር እና የአንድ ልጅ አባት ሲሆን ባለቤቱም ድምጻዊት ጥሩወርቅ አየለ ናት።

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic