ድምጻዊት መሰሉ ፋንታሁን፤ የእርጎየዎች ሁለተኛ ትውልድ | ባህል | DW | 19.09.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

ድምጻዊት መሰሉ ፋንታሁን፤ የእርጎየዎች ሁለተኛ ትውልድ

ብርቱካን ፣የሺ እመቤት ፣እናና ፣ንጋቱ እና  እየሩስ ዱባለ አምስቱ እርጎየዎች የ70 ዎቹ መጨረሻና የ80 ዎቹ የሙዚቃ ፈርጦች ነበሩ።የዘጠናዎቹ ፈርጥ ድምጻዊት መሰሉ ፋንታሁን ከዚህ የጥበብ ቤተሰብ የተገኘች ነች።የድምፃዊ ብርቱካን ዱባለ ሶስተኛ  ልጅ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:23

ድምጻዊት መሰሉ ፋንታሁን ፤የእርጎየዎች ሁለተኛ ትውልድ

ድምፃዊት መሰሉ ፋንታሁን በ90ዎቹ  መጀመሪያ  ባህላዊ ለዛ ባላቸው ሙዚቃዎቿ የአድማጭን ቀልብ መግዛት የቻለች የሙዚቃ ሰው ነች።ከዓመት በፊት ደግሞ  «አትሽሽ ጀምበር » በሚል አዲስ የሙዚቃ ስራ ሰርታለች።ድምፃዊት መሰሉ  ፋንታሁን የዛሬው የመዝናኛ ዝግጅት እንግዳችን ነች። 
ብርቱካን ፣የሺ እመቤት ፣እናና ፣ንጋቱ እና  እየሩስ ዱባለ አምስቱ እርጎየዎች የ70 ዎቹ መጨረሻና የ80 ዎቹ የሙዚቃ ፈርጦች ነበሩ።ድምጻዊት መሰሉ ፋንታሁን ከዚህ የጥበብ ቤተሰብ የተገኘች ነች።የድምፃዊ ብርቱካን ዱባለ  ሶስተኛ  ልጅ።የቤተቧን የሙዚቃ ህይወት  እያየች ያደገችው መሰሉ ታዲያ፤ በ10 ዓመቷ ነበር የቤተሰቡን የጥበብ ጉዞ የተቀላቀለችው።ስትቀላቀል ግን እንዲሁ አልነበረም ቤተ ዘመዱ መክሮበት እና ተፈትና ነው።
ቆይታም የብርቱካን ፍሬዎች በሚል መጠሪያ ከወንድሟ  ከጌጥዬ ፋንታሁን እና አሁን በህይወት ከሌለችው ከተወዳጇ ድምፃዊት ማንአልሞሽ ዲቦ ጋር በመሆን አዲስ የሙዚቃ ስራ ለአድማጭ ጀሮ አደረሱ።አለምዬ ናና፣ ባንተ ነዉ ማማሬና ተከለል የተባሉት  ዜማዎቿ በወቅቱ ባጣም ተወዳጅ እና ዝና ያተረፈችባቸው ሙዚቃዎች ነበሩ።

በ2005 ዓ/ም ደግሞ መሰሉ ብዙ አልተደመጠም የምትለውን «ያኔ» የሚል ሌላ የሙዚቃ ስራ የሰራች ሲሆን፤ ከዓመት በፊት ደግሞ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው የኤልያስ መልካ የመጨረሻ ስራ የሆነ «አትሽሽ ጀምበር » የሚል  ሌላ አልበም ለአድማጭ አድርሳለች።ከ15 ዓመት በላይ  የፈጀው እና ከእውቁ የሙዚቃ አቀናባሪ ኤሊያስ መልካ ጋር ተጣምረው የሰሩት ይህ የሙዚቃ አልበም፤ አውታር  በተባለ መተግበሪያ አማክኝነት ለሙዚቃ ታዳሚያን እንዲደርስ ሆኗል።
ስለ ኤሊያስ አውርታ የማትጠግበው መሰሉ ፤ ሙዚቃው የተሰራው ከነበረኝ አቅም ላይ ኤሊያስ አዲስ ማንነት ጨምሮበት በጥንቃቂ የተሰራ ነው ትላለች።ያም ሆኖ ሙዚቃው ሳይወጣ፣ የልፋቱን ፍሬም ሳያይ ኤሊያስን ሞት ቀደመውና  ሙዚቃዉ ለአድማጭ  ሲደርስ ኤሊያስ ባለማየቱ  አሁንም ድረስ ቁጭትና ሀዘኑ አብሯት አለ።

ሆኖም በውጤታማ የሙዚቃ ስራዎቹ  እንድምትፅናና ገልፃለች።በተለይ «ወይ ልምጣ ወይ ምጣ» የሚለው ዘፈን ግጥምና ዜማው የኤልያስ  ሲሆን፤መሰሉ እንደምትለው  የራሱን ህይወት የገለፀበት ነበር።
«በል በርታ በል በርታ ልቤ ጨከን በል ሲመጣ ይመጣል እውነቱን ተቀበል» በሚል  አይቀሬውን ሞቱን የተነበየበት ለሚመስለው ለዚህ ሙዚቃ መሰሉ የተለዬ ስሜት አላት።
እርጎየዎች ከዚያም ሁለተኛ ትውልድ የብርቱካን ፍሬዎች ቀጥሏል። ሶስተኛ ትውልድ በእናንተ ልጆች አይቀጥልም ?ከልጆችሽ ሙዚቃ የሚሞክር የለም።ለመሰሉ ያነሳንላት  ሌላው ጥያቄ ነበር።ሆኖም ከቤተሰቡ የእነሱን ፈለግ የተከተለ እንደሌለ ገልፃ፤ አንድ ወንድ ልጇ ግን ጊታር እንደሚሞክር እና ለሙዚቃ ቅርብ መሆኑን አጫውታናለች።
በቅርቡ አንድ ነጠላ ዜማ  የመልቀቅ እቅድ እንዳላት የምትናገረው ድምጻዊት መሰሉ ፋንታሁን፤ ከሁሉ አስቀድማ ግን ለኢትዮጵያ ሰላም ተመኝታለች። 

ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሀይ ጫኔ
እሸቴ በቀለ

Audios and videos on the topic