ድህነትን ለመቀነስ የተያዘው የትግል ማራቶን | ኤኮኖሚ | DW | 09.05.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

ድህነትን ለመቀነስ የተያዘው የትግል ማራቶን

የተባበሩት መንግሥታት ዓባል ሃገራት ድህነትን እስከ 2015 ዓ.ም. በግማሽ ለመቀነስ የተስማሙበትን የሚሌኒየም ዕቅድ ገቢር ማድረጉ ያልተቋረጠ ትግልን የሚጠይቅ ተግባር ነው። ማራቶን እንጂ የአጭር ርቀት ሩጫ አይደለም፤ ባለፈው ሣምንት ኡሩጉዋይ ርዕሰ-ከተማ ሞንቴቪዴዎ ላይ ተካሂዶ በነበረ የዓለም ማሕበራዊ እንቅስቃሴዎች ጉባዔ ላይ እንደተነገረው።

የድህነት ገጽታ

የድህነት ገጽታ

በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት የዕዳ ምሕረት ለማድረግና የልማት ዕርዳታችውን ከፍ ለማድረግ የገቡትን ቃል በተወሰነ ደረጃ ገቢር አድርገዋል። ሆኖም የታዳጊው ዓለም ተቆርቋሪ ቡድኖች እስካሁን የተደረገው በመጪዎቹ ቀሪ ሥምንት ዓመታት የሚሌኒየሙን ዕቅድ ከግብ ለማድረስ የሚያበቃ ሊሆን አይችልም ባዮች ናችው። ፍትሃዊ ለሆነ ንግድ፤ ለዴሞክራሲ፣ ለሰብዓዊ መብቶች ከበሬታና ለተጨማሪ ዕዳ ቅነሣ ትግሉ ይቀጥላል ማለት ነው።

በአሕጽሮት GCAP “Global Call to Action against Poverty” ማለት “ጸረ-ድህነት ዓለምአቀፍ የተግባር ጥሪ” የተሰኘው የሲቪክ ማሕበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት ኡሩጉዋይ-ሞንቴቪዴዎ ላይ የሶሥት ቀናት ጉባዔ አካሂዶ ነበር። ይህ ጥምረት የተፈጠረው ብራዚል ውስጥ በ 2005 ዓም. ተካሂዶ በነበረው የዓለም ማሕበራዊ መድረክ ጉባዔ ላይ እንደነበር ይታወሳል። ባለፈው ሣምንት ስብሰባ ላይ 150 ገደማ የሚጠጉ የማሕበራዊ እንቅስቃሴዎችና ከመንግሥት ነጻ የሆኑ ድርጅቶች ልዑካን ሲሳተፉ የውይይቱ ዓላማም ሃብታም መንግሥታት የሚሌኒየሙን ዕቅድ ከግብ ለማድረስ የገቡትን ግዴታ እንዲወጡ በሚደረገው ግፊት ለመቀጠል ስልታዊ ዘዴዎችን መንደፍ ነበር።

የዓለም ማሕበራዊ መድረክ በበለጸጉት መንግሥታት አንጻር የታዳጊ አገሮች ልሣን ሆኖ የተቋቋመ እንቅስቃሴ መሆኑ ይታወቃል። “ጸረ-ድህነት የተግባር ጥሪ” የተሰኘው የመድረኩ ጥምረት የተፈጠረውም ከሁለት ዓመታት በፊት የ G-8 መንግሥታት መሪዎች በስኮትላንድ-ግሌንኢግልስ የዕዳ ስረዛ ባደረጉበት ዓቢይ ጉባዔ ዋዜማ ነበር። የሲቪክ ማሕበራቱ ጥምረት ቃል ገቢር እንዲሆን በጊዜውና ከዚያን ወዲህም የበኩሉን ግፊት ሲያደርግ እርግጥ ጥቂት ዕርምጃ ይታይ እንጂ ድህነትን በመታገሉ ረገድ የሚገባውን ያህል እመርታ ታይቷል ለማለት አይቻልም።

ስለዚህም በሃብታሞቹ መንግሥታት አቅጣጫ የሚሰነዘረው የፍትሃዊ ንግድ፣ የተስፋፋ የዕዳ ስረዛ፣ እንዲሁም የተጨማሪና በይዘቱም የተሻለ የልማት ዕርዳታ ቁልፍ ጥሪ ጸንቶ ይቀጥላል። እርግጥ እነዚህ ነጥቦች ዛሬ በአብዛኞቹ ምዕራባውያን መንግሥታት አጀንዳዎች ላይ ሊሰፍሩ መብቃታቸውን ጥምረቱ በሁለት ዓመታት ሕልውናው እንዳገኛቸው ጠቃሚ የትግል ውጤቶች አድርጎ ነው የሚመለከተው። የደቡብ አፍሪቃው የሲቪል ተሳትፎ ዓለምአቀፍ ሕብረት ዋና ጸሐፊ ኩሚ ናይዱ በስብሰባው ላይ እንደተናገሩት ከሃያ ዓመታት በፊት ዕዳ መቀነሱ ቀርቶ ጉዳዩን አንስቶ ማውራቱ እንኳ የሚታሰብ አልነበረም።
እናም በርሳቸው አባባል ሃያላኑን G-8 መንግሥታት በተፈለገው መጠን ባይሆንም የዕዳ ቅነሣን ዓላማ እንዲቀበሉ ማድረግ መቻሉ ራሱ ጠቃሚ ዕርምጃ ነው። ጥቂት ዘግይቷል፤ ግን አቅጣጫው ትክክል መሆኑ አያጠያይቅም። የማሕበራዊው መድረክ ጥምረት ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በተገኙት ሁለት ዓቢይ ስኬቶች ላይ ጠቃሚ ድርሻ አለው። ከነዚሁ አንዱ G-8 መንግሥታት ለ 14 የአፍሪቃና ለአራት የላቲን አሜሪካ አገሮች የዕዳ ስረዛ ማድረጋቸው ነው። በሌላም ጥምረቱ በዓለም ላይ የተንሰራፋውን ድህነት በሚገባ ለመታገል መሠረቱን ሊያሰፋ ችሏል።

ይህም ሆኖ ግን የወቅቱ የታዳጊ አገሮች አጠቃላይ ሁኔታ ችግሩን በሚገባ ለመቋቋም ብዙ ጥረት እንደሚጠይቅ የሚያመለክት ነው። ጉዞው ማራቶን እንጂ ግቡ የቀረበ የአጭር ርቀት ሩጫ አይደለም። ጸረ-ድህነት የተግባር ጥሪ ጥምረት ሞንቴቪዴዎ ላይ እንዳመለከተው ዛሬም በከፋ ድህነት የተነሣ በያንዳንዷ ቀን 30 ሺህ ወይም በየሤኮንዷ አንድ ሕጻን በአጭሩ ይቀጫል። በተመሣሣይ ምክንያት ዘንድሮ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ ሕጻናት በደቡብ-ምሥራቅ እሢያና በሰላማዊው ውቂያኖስ አካባቢ አገሮች አምሥት ዕድሜ ሳይሞላቸው የሚሞቱ ናቸው። በአጠቃላይ አንድ ሚሊያርድ የዓለም ሕዝብ ከአንዲት ዶላር ባነሰች የዕለት ገቢ ኑሮውን የሚገፋ ሲሆን ንጹሕ የመጠጥ ውሃም አያገኝም።

እርግጥ በሌላ በኩል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለፈው ዓመት ዘገባው እንዳመለከተው በእሢያ በከፋ የድህነት ሁኔታ የሚኖረው የሕብረተሰብ ክፍል ቁጥር በሁለት መቶ ሺህ ገደማ ቀንሷል። ድርጅቱ በአፍሪቃም መጠኑ በግማሽ እንደሚቀንስ ነው የተነበየው። በዘገባው መሠረት በላቲን አሜሪካና በካራይብ አካባቢ ደግሞ የአንደኛ ደረጃ ትምሕርት ድርሻ ከዘጠና በመቶ በልጧል። አብዛኛው የእሢያ ክፍልና የቀድሞይቱ ሶቪየት ሕብረት ሬፑብሊኮች ትምሕርት ለሁሉም እንዲዳረስ የተቀመጠውን የሚሌኒየም ዕቅድ በተጣለለት የጊዜ ገደብ ከግብ ለማድረስ እንደሚቃረቡም ነው የሚታመነው።

በሞንቴቪዴዎ ጉባዔ ላይ እንደተጠቀሰው ከ 1990 ወዲህ ረሃብም በዓለም ዙሪያ እየቀነሰ መጥቷል። ግን ሂደቱ ችግሩን እንደታሰበው በ 2015 በግማሽ ቀንሶ ለመገኝት በቂ አይደለም። በሌላ በኩል በተለይ በጾታ ረገድ የእኩልነት እጦቱ እየጨመረ ነው። አጠቃላዩ ሂደት አቆልቋይ ባይሆንም ችግሩ የሚሌኒየሙን ዕቅድ ገቢር ለማድረግ በ 2000 ዓ.ም. የተቀመጠው የጊዜ ገደብ በግማሽ ተሟጦ እየተቃረበ መሄዱ ነው። ስለዚህም ቀልጣፋና ያልተቋረጠ ግፊት ማድረጉ ግድ ይሆናል።

ጉባዔው ልማትን ለማራመድ ፍትሃዊ ንግድ አስፈላጊ መሆኑንም አስረግጧል። በታዳጊ አገሮች የዓለም ንግድ ድርሻ አንድ ከመቶ መጨመሩ እንኳ 128 ሚሊዮን ሕዝብን ከድህነት ሊያተርፍ እንደሚችል ነው የተነገረው። ታዳጊ አገሮችን የሚጎዱ ወይም በነርሱ ዕድገት ላይ ተጽዕኖ ያላችው የዓለም ንግድ ደምቦች እንዲለወጡም ተጠይቋል። ሁኔታውን ለማስረዳት የአውሮፓ ላሞች ዛሬ በየቀኑ የሚያገኙት መንግሥታዊ ድጎማ ከአፍሪቃ ግማሽ ሕዝብ የበለጠ መሆኑ ነው በምሳሌነት የተጠቀሰው።

ይህም ሆኖ ግን የዕርምጃ ተሥፋ መኖሩን ነው የማሕበራዊው መድረክ ተሳታፊዎች የተናገሩት። ዓለምአቀፉ ሁኔታ በጥቅል ሲታይ በያንዳንዱ የሚሌኒየም ሥምንት ግቦች ለምሳሌ በትምሕርት ረገድ ጠቃሚ ዕርምጃ ተደርጓል። የሚያስደንቅ ሆኖ አንዳንድ ሞዛምቢክን፣ ጋናን፤ ወይም ሩዋንዳንና ባንግላዴሽን የመሳሰሉ አገሮች ብዙዎችን ግቦች ሊያሟሉ በሚችሉበት አቅጣጫ ላይ ይገኛሉ። ይህም እነዚህ ድሃ አገሮች ለዚህ ከበቁ ሌሎች የተሻለ ዕርምጃ ሊያሳዩ የማይችሉበት ምክንያት አይኖርም የሚል ዕምነትን አጠናክሯል።

በሞዛምቢክ የዕዳ ስረዛው አገሪቱ 18,5 ሚሊዮን ዶላር ለጤና ጥበቃ አገልግሎት እንድታውል ረድቷል። ደቡብ-ምሥራቅ አፍሪቃይቱ አገር ነጻ ክትባት በመስጠት ግማሽ ሚሊዮን ሕጻናትን ቴታኑስን፣ ተቅማጥና ሌሎች በሽታዎችን መከላከል እንዲችሉ አብቅታለች። ላቲን አሜሪካ ከአንዳንድ ለምሳሌ ከድህነትና ከረሃብ ከተሳሰሩ ግቦች በስተቀር በአጠቃላይ በሚሌኒየሙ ዕቅድ ጥሩ ዕርምጃ እያሳየች መሆኗ ነው የተነገረው። በሌላ በኩል በዚህ አካባቢ ትልቁ ችግር የጾታ እኩልነት ጉዳይና ማሕበራዊ መገለል ነው። የአካባቢውን ሃብት በተሻለ ሁኔታ ማከፋፈል ካልተቻለ ሁኔታው መለወጡም ሲበዛ ያጠያይቃል።

ጸረ-ድህነቱ የተግባር ጥሪ ጥምረት በዓመቱ ሂደት ብዙ ጥረቶችን ለማንቀሳቀስ ያቅዳል። ከነዚሁም አንዱ በሚቀጥለው ወር በዚህ በጀርመን በሚካሄደው የ G-8 መንግሥታት ጉባዔ ከመሪዎች ግንኙነት ማድረግ፣ ከዚያም ከአንድ ወር በኋላ የሚሌኒየሙን ዕቅድ መለስ ብሎ ማጤኑና በጥቅምት 17 የሚውለውን ድህነትን የማጥፋት ዓለምአቀፍ ቀን ማክበሩ ይገኙበታል። የዘንድሮው የ 2007 ድህነትን የማጥፋት ቀን የሚታሰበው “ተነሣ ተናገር” በሚል መሪ መፈክር ሲሆን ቀደም ባለው ዓመት በዓለም ዙሪያ የሚገኝ 23 ሚሊዮን ሕዝብ “በድህነት’ ላይ ተነሣ” በሚል መርሆ በአስደናቂ ሁኔታ ጸረ-ድህነት የተቃውሞ ዘመቻ ማካሄዱ አይዘነጋም።

በዚህ በጀርመን በፊታችን ወር በሚካሄደው የ G-8 መሪዎች ጉባዔ አስተናጋጇ አገር የአፍሪቃን ልማት ዓቢይ የአጀንዳ ርዕስ ማድረጓ የብዙዎች ማሕበራዊ እንቅስቃሴዎችን ትኩረት ይበልጥ መሳቡ አይቀርም። ጥያቄው የረባ ጭብጥ ውጤት ይገኛል ወይ ነው። ለማንኛውም ጸረ-ድህነቱ ጥምረት ትግሉን አጠናክሮ ይቀጥሏል።