ድህነትና የምዕራቡ ዓለም ዕርዳታ ፍቱንነት ማጠያያቅ | ኤኮኖሚ | DW | 04.08.2006
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

ድህነትና የምዕራቡ ዓለም ዕርዳታ ፍቱንነት ማጠያያቅ

ታዳጊው ዓለም፤ በተለይም የአፍሪቃ አገሮች፤ የልማት ዕድላቸውን አንቆ በያዘ ድህነት፣ ረሃብ፣ በሽታ፣ በተወሰነ ደረጃም በእርስበርስ ጦርነትና የስደት መዘዝ ተወጥረው ነው የሚገኙት። ምክንያቶቹ ብዙዎች፤ የውስጥም የውጭም መንስዔዎች ያሏቸው ናቸው።

የአፍሪቃ የድህነት ገጽታ

የአፍሪቃ የድህነት ገጽታ

በአንድ በኩል የበጎ አስተዳደር ጉድለትና የማሕበራዊ ፍትህ እጦት ድህነትን የመቀነሱን ተሥፋ እያቆረቆዘው ይገኛል። በሌላም የምዕራባውያን መንግሥታት የረጅምና የአጭር ጊዜ የልማትና የአስቸኳይ ዕርዳታ አሰጣጥ ፖሊሲዎች ድሃውን ሕዝብ እንዲጠቅሙና ዕድገቱን እንዲያፋጥኑ ሆነው አለመቀናበራቸው የሚገባውን ያህል ፍቱን አያደርጋቸውም። ዓለምአቀፉ የግብረ-ሰናይ ድርጅት ኦክስፋም በቅርቡ በዕርዳታው ፖሊሲ ላይ የተከሰቱትን ጉድለቶች በመጠቆም አማራጭ መንገዶችን ጠቁሞ ነበር። ድህነት፣ የኤኮኖሚ ኋላ ቀርነት የልማት ተሥፋ መቆርቆዝ የሚያሳዝን ሆኖ በተለይ የአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም መለያ ገጽታ ነው። ችግሩና የዕርዳታው ጩኸትም ከዚያው ነው ይበልጥ የሚሰማው።
ግን ተጠያቂው ማንም ይሁን ማ ተገቢው ሁሉ ተደርጓል ለማለት አይቻልም። ቤት ሰራሹና የውጩ እክል ተጣምሮ መከራው እየጨመረ መሄዱ ነው ሃቁ! ለድሆች አገሮች ከድህነት ቀንበር ለመላቀቅ በጎ የአስተዳደር ዘይቤ ዕውን መሆኑና ማሕበራዊ ፍትህ መስፈኑ ቅድመ-ግዴታ ነው። ይህ ለታዳጊዎቹ አገሮች ዕርዳታ የሚለግሱት የበለጸጉት መንግሥታት ራሳቸው ባለፉት ጥቂት ዓመታት ደግመው ደጋግመው ያመለከቱት ጉዳይ ነው። ግን ገቢር እንዲሆን ግፊት በማድረጉ በኩል አንድ ወጥና ቁርጠኛ ፖሊሲ ሲራመድ አይታይም፤ ዕርዳታው ፍቱን አለመሆኑና ድህነቱም እየባስ መሄዱ ለዚህ ነው።

ለነገሩ ሰብዓዊው ወይም አስቸኳዩ ዕርዳታ የችግሩን መባባስ ያህል እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አልመጣም። በድርቅ ወይም በጦርነት ሳቢያ ድንገተኛ ችግሮችን ለማስታገስ የሚቀርበው አስቸኳዩ ዕርዳታ በ 1997 እና በ 2003 መካከል፤ በስድሥት ዓመታት ወስጥ እንኳ ከ 946 ሚሊዮን ወደ 1,7 ሚሊያርድ ዶላር ከፍ ማለቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይሁን እንጂ ያለፉት ወራት የሣሄል አካባቢ፣ የደቡባዊውና የአፍሪቃ ቀንድ አገሮች የምግብ እጥረት ቀውስ እንደሚያሣየው የአፍሪቃ ረሃብ አሁንም ብርቱ ጠንቅ ሆኖ እንደቀጠለ ነው።

በኦክስፋም ገለጻ ለጋሽ አገሮች በተባበሩት መንግሥታት የሚጠየቀው ዕርዳታ በቂ ሆኖና ሳይዘገይ መድረስ ላለመቻሉ አንዱ ምክንያት የድርጅቱ ወኪሎች የአሠራር ብቃት ጉድለት ነው ይላሉ። ያም ሆነ ይህ የግብረ-ሰናይ ቡድኖች የተፋጠነና የበለጠ ዕርዳታ ለመስጠት ለጋሽ አገሮች የአንድ ቢሊዮን ዶላር ግዴታ መግባታችው ቁልፍ መሆኑን ይናገራሉ። ኦክስፋም “የረሃብ መንስዔ” በሚል ርዕስ የአፍሪቃን የምግብ ቀውስ አስመልክቶ በቅርቡ ባወጣው ዘገባ ተገቢው ቀድሞ ማስጠንቀቂያ ዘዴ አለመኖሩም የምግብ ዕርዳታን ከሚያጓትቱት ምክንያቶች አንዱ አንደሆነ አመልክቷል።
የዕርዳታው አቅርቦት ከፍላጎቱ መጠንና አጣዳፊነት ይልቅ በመገናኛ አውታሮች ትኩረት መሳቡም ሌላው ችግር ነው። አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ በድንገተኛ ጊዜ ሕይወትን የማትረፍ ታላቅ ድርሻ ቢኖረውም በተለይ ድህነት ዋና የረሃብ መንስዔ ሆኖ በሚገኝባቸው አካባቢዎች ብቸኛው የምግብ ዋስትና ምላሽ ሆኖ ሊታይ አይገባውም። ከገንዘብ ሽግግር ጀምሮ ገበሬዎችን በምርት ዘር እንዲገዙና ሁኔታውን እንዲያሻሽሉ ሊረዱ የሚችሉ ሌሎች መፍትሄዎችም አሉ።

በሌላ በኩል የባሕር ማዶው የምግብ መዋጮ ከለጋሽ አገሮች ሰብዓዊ ዓላማ ይልቅ የተትረፈረፈ የእርሻ ምርትን የማስወገድ ሚሥጥርም አለው። በመሆኑም ከአሜሪካና ከአውሮፓ የተትረፈረፈውን ምርት በአፍሪቃ ማራገፉ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ትክክለኛው መንገድ ሊሆን አይችልም። በዚያው በአካባቢው ምግብ መግዛቱ ርካሽ ከመሆኑ ሌላ ፈጣንም ነው። አስቸኳይ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጡ በኩል ሌላው ፈተናም አስቸኳዩ ዕርዳታ በሙስና በተጠመዱ ባለሥልጣናት መመዝበሩና ለመንግሥታት የራስ ዓላማ ጥቅም ላይ ሊውል መቻሉ ነው።

ኦክስፋም በዘገባው የረሃብን ችግሮች ለመቋቋም መፍትሄ ያላቸውን ሃሣቦች ዘርዝሯል። አንደኛው ለገጠር አካባቢዎች ልማት የረጅም ጊዜ መዋዕለ ነዋይን ማጠናከር ነው። የአፍሪቃ ሕብረት ዓባል ሃገራቱ ለዚህ ተግባር ከበጀታቸው ቢያንስ አሥር በመቶውን እንዲመድቡ መስፈርት ማስቀመጡ ይታወቃል። እርግጥ ይህ በውጭ ዕርዳታ መጠናከርም ይኖርበታል። በዘገባው መሠረት ከሣሃራ በስተደቡብ ባለው የአፍሪቃ ክፍል በቅርቡ ጥቂት ማገገም ቢታይም የውጩ የእርሻ ልማት ዕርዳታ ከ 1990 እስከ 2002 43 በመቶ ነው ያቆለቆለው። አዝማሚያው አዳጊ ካልሆነ ሃሣቡ እንደገና ከንቱ ሆኖ መቅረቱ ነው።