ዴንግ ሻዎፒንግ፤ የቻይና ዘመናዊ ዕርምጃ ጥርጊያ ከፋች | ኤኮኖሚ | DW | 21.02.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

ዴንግ ሻዎፒንግ፤ የቻይና ዘመናዊ ዕርምጃ ጥርጊያ ከፋች

የቀድሞይቱን ቀይ ቻይና በውል በተሰላ የኤኮኖሚ ለውጥ የካፒታል ማዕከል ለማድረግ በማብቃቱ በኩል የሟቹን ፖለቲከኛ የዴንግ ሻዎፒንግን ያህል ጠቃሚ አስተዋጽኦ ያደረገ የአገሪቱ ባለሥልጣን ተፈልጎ አይገኝም። ቻይናን በዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ መድረክ ላይ ለታላቅነት ያበቁት ዴንግ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ ባለፈው ሰኞ አሥር ዓመት አለፋቸው።

ዴንግ ሻዎፒንግ

ዴንግ ሻዎፒንግ

ዴንግ ሻዎፒንግ ምንም እንኳ አንዴም ከፍተኛ ሥልጣን ባይይዙም ከማኦ ሤዶንግ በኋላ የቻይናን ዕርምጃ ለአሠርተ-ዓመታት በቀደምትነት ያቀናጁና ያቀናብሩ፤ የስኬት አቅጣጫ ያስያዙ ነበሩ። በዚሁም ገና በሕይወት ዘመናቸው እያሉ ባለታሪክ መሆናቸው አልቀረም። ቀደምቱ የአሜሪካ መጽሄት Time ከአንዴም ሁለቴ “የዓመቱ ሰው” ብሎ ሲመርጣቸው ስምንት ጊዜም ዋና ዓምዱ ላይ አስፍሯቸዋል። ዴንግ ሻዎፒንግ ለቻይና ዘመናዊ የዕድገት ዕርምጃ ጥርጊያ የከፈቱ ዓለም ያደነቃቸው የአገሪቱ ፖለቲከኛ ነበሩ።

ቻይና ዛሬ በጥቂት አሠርተ-ዓመታት ውስጥ ለደረሰችበት የተፋጠነ ዕርምጃ የጊዜውን የርዕዮት አጥር ሰብሮ የወጣው የዕድገት ጽንሰ-ሃሣባቸው ዓቢይ አስተዋጽኦ አድርጓል። በጥቂቱ በሕይወት ታሪካቸው እንጀምርና እ.ጎ.አ. ነሐሴ 22, 1904 በሢሹዋን ክፍለ-ሐገር ከአንድ የገበሬ ቤተሰብ የተወለዱት ዴንግ በ 16 ዓመት ዕድሜያቸው ለትምሕርት ወደ ፈረንሣይ ይመጣሉ። ከማርክሲስቱ ርዕዮተ-ዓለም ጋር የመጀመሪያ ንኪኪ ያደረጉትም በዚህ ጊዜ ነበር። ብዙ ሣይቆዩም የቻይናን ኮሙኒስት ፓርቲ ሲቀላቀሉ በ 1926 ወደ አገራቸው ተመልሰው በድርጅቱ ይመራ በነበረው ዓብዮታዊ ትግል መሳተፍ ይጀምራሉ።

ዴንግ ሻዎፒንግ የቻይና ዓብዮት ረጅም-ጉዞ ተሳታፊም ነበሩ። ከዚያም ከጃፓን ጋር በተካሄደው ውጊያና በጸረ-ኩዎሚንታንጉ የእርስበርስ ጦርነት በአደረጃጀትና በወታደራዊ ጥበብ የነበራቸውን ተሰጥኦ ይመሰክራሉ። ከማርሻል ሊዩ ቦቼንግ ጋር በጋራ የመሩት ዲቪዚዮን ገና ቀደም ሲል ከጃፓን ጋር በተካሄደ ጦርነት ዝናን ያተረፈ ነበር። በሚያዚያ ወር 1949 የኩዎሚንታንግ ዋና ከተማ የነበረችውን ናንጂንግን በመያዝ የእርስበርሱ ጦርነት በኮሙኒስቱ ፓርቲ አሸናፊነት ይደመደማል።

ከዚሁ ከሶሥት ዓመታት በኋላ ማኦ ተሰጥኦዋቸውን የሚያደንቁትን ዴንግ ሻዎፒንግን ከደቡብ-ምዕራብ ቻይና ወደ ቤይጂንግ ይጠሯቸዋል። ግን ማኦ ዕውቅና እንጂ አመኔታ ስላልሰጧቸው በተከተሉት ዓመታት ብዙም አያቀርቧቸውም። የሆነው ሆኖ የጊዜውን ዘመቻ እንደምንም በዘዴና በብልሃት ያላንዳች ጉዳት ያልፋሉ። ዴንግ ሻዎፒንግ በ 60ኛዎቹ ዓመታት ባሕላዊ ዓብዮት ወቅት ለዘብተኛ አቋም በማሣየታችው ከጊዜው ጠቅላይ ሚኒስትር ከሊዩ ሻኦኪ ቀጥለው በሁለተኝነት ከላሽ ተብለው መወገዛቸውም አልቀረም።

በዚሁ የተነሣ በጊዜው የነበራቸውን ሥልጣን በሙሉ ሲነጠቁ ግን እንደ ሊዩ ጨርሰው ለመወገድና ወህኒቤት ለመውረድ አይበቁም። የፓርቲ ዓባልነታቸውን እንደያዙ ለመቀጠል ይችላሉ። በዚህ ሁሉ ጠምዛዛ ጉዞ ውስጥ ግን የነበራቸው ራዕይ ጸንቶ ይቆያል። ዴንግ ሻዎፒንግ እንደገና ወደ ቤይጂንግ ሊመለሱ የበቁት ለማኦ ሤዶንግ ቀጥተኛ ደብዳቤ ጽፈው ይቅርታ ከጠየቁ በኋላ ነበር። ይህ ልዝብ ዕርምጃቸውም በጊዜው በጸና ታመው የነበሩትን ጠቅላይ ሚእስትር ሹ ኤንላይን በምክትልነት እንዲያገለግሉ፤ ወደ ከፍተኛው ሥልጣን ማዕከል እንዲመለሱ ዕድል ይሰጣቸዋል።

ከዚህ በኋላ በቻይና የተሃድሶ ጎህ ሊቀድ ብዙም ጊዜ አይፈጅበትም። ዴንግ ሻዎፒንግም እ.ጎ.አ. በ 1976 በማኦ ሤዱንግ ሞት ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ ዕውነተኛ ክብደት ያገኙት። እርግጥ ሥልጣናቸው ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት አላለፈም። ሆኖም የአገሪቱን ኤኮኖሚና የውጭ ፖሊሲ ለማዳበር የነበራችውን ጭብጥ የለውጥ ጽንሰ-ሃሣብ በፖለቲካ ተግባር በሥራ ላይ ለማዋል ይበቃሉ። ራዕያቸው ዛሬ ለሚታየው ታላቅ የቻይና ዕርምጃ መሠረቱ ነበር።

“የወቅቱን የኤኮኖሚ ሥርዓት መሰናክል እስከፈጠረብን ድረስ በዘዴ መለወጡ ግድ ይሆንብናል። ፋብሪካዎች ደረጃ በደረጃ ወደ አዲሱ ቴክኖሎጂ መሸጋገር አለባቸው። የአገሪቱ የሣይንስና የቴክኒክ ይዞታም ተጠናክሮ ወደፊት ማምራት ይኖርበታል። ይህ ብቻ አይደለም፤ ሕዝቡን በተሻለ ሁኔታ በትምሕርት ማነጹም ግድ ነው” ነበር ያሉት።

ዴንግ አንድ ዝናን ያተረፈ ያሉትም ነገር ነበር። አንዲት አይጥ የምትይዝ ድመት፤ የፈለጋትን ትሁን፤ ጥቁር ወይም ነጭ፤ ጥሩ ድመት ናት”- ይህ አንዴ በሢሹዋን ክፍለ-ሐገር የተስፋፋ የሕዝብ አባባል ነበር። የዴንግ ሻዎፒንግ የቻይና ዕድገት ራዕይ በ 1978 የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ጉባዔ ላይ የአገሪቱ ማሕበራዊ ፖሊሲ መለያ አርማ ይሆናል። ጉባዔው የዴንግን አራት የዘመናዊ ተሃድሶ ፖሊሲዎች ማለት የኢንዱስትሪ፣ የእርሻ ልማት፣ የመከላከያና የሣይንስ ዕርምጃ ይፋ መርሁ አድርጎ ያጸደቀው በዚያን ጊዜ ነበር።

የዴንግ ዓላማ ወይም ግብ እስከ ሃያኛው ምዕተ-ዓመት መገባደጃ እያንዳንዱ የቻይና ዜጋ በ 800 ዶላር ዓመታዊ ነፍስ-ወከፍ ገቢ ጥቂትም ቢሆን የብልጽግና ድርሻ እንዲያገኝ ማድረግ ነበር። ዛሬ መረጃ ሰንጠረዦች እንደሚያሣዩት ይህ ግብ ቢያንስ በእጥፍ ሊደረስበት በቅቷል። የዴንግ የዕድገት ሞዴል የቻይናን መለያ ባሕርያት የተከተለ ሶሻሊስታዊ ዘመናዊ ዕድገት የሚል ሲሆን ይሄም የገበያ ኤኮኖሚና የሶሻሊስቱ አመራር ትስስር የሰመረበት መሆኑ ነው። ከዴንግ ጋር በተለያዩ አጋጣሚዎች ተገናኝተው የተነጋገሩት የቀድሞው የጀርመን ቻንስለር ሄልሙት ሽሚት የቻይናውን የለውጥ ሃዋርያ መለስ ብለው የሚያስታውሱት ከከፍተኛ አድናቆት ነው።

“በማኦ መሞት ዴንግ ነጻ ሰው ይሆናሉ። ምንም እንኳ ቀደምት የመንግሥት ሥልጣን ባይይዙም በመንፈስና በፖለቲካ በጊዜይቱ ቻይና ዋናው ሰው ነበሩ። በ 1984 እና በዘጠናኛዎቹ ዓመታት መጨረሻ ባደረግነው ንግግር ለዴንግ ሻዎፒንግ ጥልቅ አድናቆት ነው ያደረብኝ። አስደናቂ የኤኮኖሚ ብቃት ነበራቸው። ቻይና ባለፉት ሃያ ዓመታት ላደረገችው ዕርምጃ ዴንግን ልታመሰግን ይገባታል” የቀድሞው ቻንስለር እንደገለጹት።

ዴንግ ሻዎፒንግ አገሪቱን ለውጭው ዓለም በመክፈት ተማሪዎችን በገፍ ወደ ምዕራቡ ዓለም ይልካሉ። ተማሪዎቹ በዚያው ወጥተው የመቅረታቸው አደጋ ቢኖርም ዴንግ በረጅም ጊዜ ሃሣባቸው ዕውን እንደሚሆን ዕኑ ዕምነት ነበራቸው። ዴንግ በቻይና ነባሩ እንዲጠፋ አላደረጉም። ባለው ላይ ተመሥርተው በአገሪቱ ዘመናዊ ለውጥን ማካሄዱን ነው የመረጡት። በ 80ኛዎቹ ዓመታት የጀመረው ለውጥ ደረጃ በደረጃ በእርሻ ልማቱ መስክ ይካሄዳል። ታዲያ የቻይና ገበሬዎች የኑሮ ደረጃ ለመሻሻል ብዙ ጊዜ አይወስድበትም። ለውጡ ለተከታዩ ሁለንተናዊ የኤኮኖሚ ዕድገት መሠረት ሲሆን እርግጥ በሌላ በኩል በሃብታምና በድሆች መካከል ያለውን ልዩነት በማስፋት ችግር መፍጠሩ አልቀረም። በአጠቃላይ ግን ዴንግ በቁርጠኝነት የጀመሩት የተሃድሶ ለውጥ ቻይናን በዓለም ኤኮኖሚ መድረክ ላይ ከሃያላኑ መንግሥታት አንዷ እንድትሆን አብቅቷል።

ወደ ሌላ ርዕስ እንሻገርና የደቡብ አፍሪቃ ብዙሃን ጥቁሮች ዘረኛው አገዛዝ ከወደቀ ከ 13 ዓመታት በኋላም የሚገባውን ያህል የርስት-ንብረት ባለቤት ለመሆን በቅተው አይገኙም። የአፍሪቃ ብሄራዊ ሸንጎ በ 1994 የአፓርታይዱ አገዛዝ አክትሞ ሥልጣን እንደያዘ ከአገሪቱ የእርሻ መሬት ሲሶውን እስከ 2014 ዓ.ም. ድረስ ለጥቁሮች የማስተላለፍ ግብ ይዞ ነበር የተነሣው። ዓላማውም በዘረኛው አገዛዝ ንብረታቸውን የተጠነጠቁትን ዜጎች መካስ ነበር።

ይሁን አንጂ ዛሬ ይህ ከተባለ ከአሥር ዓመታት በላይ ሲያልፍ በጉዳዩ ብዙም ዕርምጃ አለመደረጉ ነው ችግሩ። መረጃዎች የሚጠቁሙት በነጮች ከተያዘው መሬት አራት በመቶው ብቻ ወደ ጥቁሮች ዕጅ መሸጋሸጉን ነው። የችግሩ መንስዔዎች ብዙዎች ሲሆኑ አንዱም በነጭ ገበሬዎችና በርስት አመልካቾች መካከል የሚካሄደው ድርድር እስከ ስድሥት ዓመት ጊዜ የሚፈጅ አድካሚ ጉዳይ ሆኖ መቆየቱ ነው። ገበሬዎቹ የመሬታቸውን ዋጋ ከፍ ለማድረግ መፈለጋቸው ሽግግሩን ሲያጓትተው ኖሯል። በዚሁ የተነሣም የእርሻና የርስት ጉዳይ ሚኒስትሩ ሉሉ ሺንጉዋና ባለፈው ዓመት የድርድሩን ጊዜ በስድሥት ወር የሚገድብ ሕግ አስፍነው ነበር።

በወቅቱ እሰከሚቀጥለው 2008 ዓ.ም. ድረስ መጠናቀቅ የሚኖርባቸው ስድሥት ሺህ የገጠር መሬት ባለቤትነት ማመልከቻዎች ለክንውን ቀርበው ይገኛሉ። በሌላ በኩል በቀድሞዎቹየጥቁሮች መኖሪያ አካባቢዎች፤ ሆምላንድ ብዙ ያልተነካ መሬት እያለ ለምን ከአምራች ገበሬዎች ርስት ይወሰዳል ሲሉ ቅሬታቸውን የሚገልጹ ነጮች መኖራቸውም አልቀረም። ይሁንና የአፓርታይዱ አገዛዝ በጊዜው በፈጠራቸው ሆምላንዶች መሬት ማልማቱ ቀላል እንዳልሆነ ግልጽ ነው።

ለደቡብ አፍሪቃ 47 ሚሊዮን ሕዝብ የሚቀርበውን ምግብ የሚየርቱት በአብዛኛው ነጮቹ የንግድ ባለዕርሻዎች ናቸው። እነዚሁ መሬት ለጥቁሮች ለማሸጋገር በተያዘው ጥረት አገሪቱ እንደ ዚምባብዌ ቀውስ ላይ ልትወድቅ ትችላለች ሲሉ ያስጠነቅቃሉ። እንደሚታወቀው ዚምባብዌ አንዴ 4,500 የንግድ ባለእርሻዎች ነበሯት። ዛሬ የነጮች መሬት መነጠቅ ከተጀመረ ወዲህ የቀሩት 200 ቢሆኑ ነው። ይህ ደግሞ እርግጥ ጠንካራ የምግብ እጥረት፤ አጠቃላይ ቀውስ እንዲሰፍን አድርጓል። ይሁንና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የደቡብ አፍሪቃ ባለሥልጣናት የአገሪቱን የለውጥ ሂደት ከዚምባዌ ማመሳሰሉን ተገቢ ሆኖ አያገኙትም።

ደቡብ አፍሪቃ ሕጋዊ መዋቅር አላት፤ ለገበሬዎች ካሣም ይከፈላል ባዮች ናቸው። በሌላ በኩል ነጮች መንግሥት የወሰነውን ካሣ ወደዱም ጠሉ መቀበላቸው ግድ እንደሆነ፤ አቤት ማለት እንኳ እንደማይቻል ነው የሚናገሩት። ለምርት መውደቅ ምክንያት እንዳይሆንም ይሰጋሉ። ይሁን እንጂ ብዙሃኑን ጥቁሮች የመሬት ባለቤት የማድረጉ የሽግግር ውጥን የግድ ወደፊት መግፋት ይኖርበታል። አለበለዚያ የብዙሃኑን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የተገባው ቃል ከንቱ ሆኖ መቅረቱ ነው።