ዴቪድ ኬመረን አይ ኤስን ለመዋጋት ዛቱ | ይዘት | DW | 14.09.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ይዘት

ዴቪድ ኬመረን አይ ኤስን ለመዋጋት ዛቱ

«አይ ኤስ» የተባለው አክራሪ ታጣቂ ቡድን ዳግም አንድ ምዕራባዊ ምርኮኛን ገድሎ ጭካኔ የተሞላበት ድርጊቱን በኢንተርኔት ይፋ ማድረጉ ተገለፀ።

ሟቹ ምርኮኛ የእርስ በእርስ ጦርነት በሚካሄድባት ሶርያ የሰብዓዊ ርዳታ ለመለገስ ባለፈው ዓመት የተጓዙት ብሪታኒያዊው ዴቪድ ሄንስ እንደሆኑ ተረጋግጧል። የብሪታንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ኬመረን፣ የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ እና የፈረንሳይ አቻቸው ፍራንስዋ ኦሎንድ ድርጊቱን አፀያፊ ግድያ ብለውታል። የአይ ኤስ ቡድን ይህንን የበቀል ግድያ የፈፀመው ብሪታንያ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር የፀረ ሽብር ህብረት በመፍጠሯ እንደሆነ ገልጿል። ይህ ቪዲዮ ይፋ ከመሆኑ አስቀድሞ ሁለት የዩናይትድ ስቴትስ ጋዜጠኞች ታግተው እንደተገደሉም ይታወሳል። በአጠቃላይ እስካሁን ከ30-40 የሚደርሱ አውሮፓውያንና አሜሪካውያን በአማፂው ቡድን ቁጥጥር ስር እንደሚገኙ ይገመታል። በሌላ ዜና እራሱን «እስላማዊ መንግሥት» ብሎ የሚጠራዉን አማፂ ቡድን ለመዋጋት አውስትራሊያ ትብብሯን እንደምትለግስ አስታወቀች። በዚህም መሰረት አውስትራሊያ ወታደሮች እና የጦር አይሮፕላኖችን በመላክ ትተባበራለች ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ አቦት ። 600 የሚጠጉ ወታደሮች ኢራቅ ውስጥ የሚገኙ ጄሐዲስቶችን በመዋጋቱ ሂደት ድጋፍ ለመስጠት ወደ የተባበሩት የአረብ ኢሚራቶች እንደተላኩ ተጠቅሷል። ከዚህም ሌላ በርካታ የጦር ጄቶች ወደ አካባቢው አምርተዋል ተብሏል። ይሁንና ግን አቦት አያይዘው አውስትራሊያ በቀጥታ ወደ ኢራቅ የእግረኛ ጦር በመላኩም ሆነ ሶርያ ውስጥ በአይ ኤስ ቡድን ላይ ለመጣል በታቀደው የአየር ጥቃት እንደማትሰለፍ አሳስበዋል። የዩናይትድ ስቴትሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ በፀረ ሽብር ህብረቱ የሚሳተፉ ሃገራትን ለማግባባት በተለያዩ የአረብ ሃገራት በመጓዝ ላይ ይገኛሉ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ልደት አበበ