ዳኛው ከጦማሪዎቹ እና ጋዜጠኞቹ ችሎት ራሳቸውን አገለሉ | ኢትዮጵያ | DW | 05.02.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

ዳኛው ከጦማሪዎቹ እና ጋዜጠኞቹ ችሎት ራሳቸውን አገለሉ

በእስር ላይ የሚገኙት ስድስት ጦማሪያንና ሶስት ጋዜጠኞች የሚዳኙት የመሃል ዳኛ በፈቃዳቸው ራሳቸውን አገለሉ።ተከሳሾቹ ጥር 26 ቀን 2007 ዓ.ም. ያቀረቡትን የዳኛው ይነሱልን ጥያቄ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጎት የነበረ ቢሆንም የመሀል ዳኛው አቶ ሸለመ በቀለ በፈቃደኝነት ራሳቸውን አግልለዋል።

በነሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ በሽብርተኝነት ወንጀል የተከሰሱት እና በእስር ላይ የሚገኙት የዞን ዘጠኝ ስድስት ጦማርያን እና ሶስትጋዜጠኞች ጉዳዩን የሚመለከቱት የመሃል ዳኛ እንዲቀየሩ ያቀረቡት ጥያቄ ፍርድ ቤቱ ዛሬ ሳይቀበለው ቀርቷል።ጥር 26 ቀን 2007 ዓ.ም. የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የ19ኛ ወንጀል ችሎት የእምነት ክህደት ቃል ለመቀበል ተሰይሞ የነበረ ቢሆንም ተከሳሾች በሶስት ምክንያቶች የመሃል ዳኛው አቶ ሸለመ በቀለ እንዲነሱላቸው ጥያቄ ማቅረባቸውን ጠበቃ አምሃ መኮንን ተናግረዋል።

«አቃቤ ህግ በእኛ በኩል ሆን ብሎ በሚባል ምክንያት እየቆነጠረ ክሱን አሻሻልኩ እያለ ሲያቀርብ ፍርድ ቤት ተደጋጋሚ እድል መስጠት አልነበረበትም።» የሚሉት ጠበቃ አምሃ መኮንን ተከሳሾች የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብት ያስከብራል የሚባለው ፍርድ ቤት ለአቃቤ ህግ ተደጋጋሚ እድል መስጠቱ አግባብ አለመሆኑ በዳኛው ላይ ከቀረቡ ቅሬታዎች መካከል ቀዳሚው መሆኑን ተናግረዋል። «ሃሳባችንን በችሎት ለመግለጽ ስንሞክር እገዳ ያደርጉብናል።» የሚለው ቅሬታ ለተከሳሾች ጥያቄ ተጨማሪ ምክንያት መሆኑንም አስረድተዋል። ክሱ እንዲሻሻል ብይን በተሰጠባቸው አራት ነጥቦች ላይ ምንም የማሻሻያ ለውጥ ሳይደረግ ፍርድ ቤቱ «ክሱ ተሻሽሏል።በክርክሩ ቀጥሉ።» የሚል ውሳኔ ማስተላለፉ የራሱን ብይን ራሱ የሻረበት በመሆኑ «በዚህ ብይንም ሰብሳቢው ዳኛ ጉልህ ድርሻ አላቸው ብለን ስለምናምን ሰብሳቢው ዳኛ ይኸን ችሎት እየሰበሰቡ ከዚህ በኃላ በሚኖረው ክርክር ትክክለኛ ፍትህ እናገኛለን ብለን አናምንም።» ሲሉ ጠበቃ አምሃ መኮንን ተናግረዋል።

በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 25/85 አን ቀጽ 27 መሰረት ሶስት ዳኞች በሚያስችሉት ችሎት በመሃል ዳኛው ላይ ቅሬታ በመቅረቡ ቀሪዎቹ ዳኞች ጉዳዩን መርምረው «ውሳኔዎቹ የተሰጡት በሦስቱ ዳኞች መሆኑን በመግለጽና የቀረቡት ቅሬታዎች በማስረጃ ያልተደገፉ ናቸው።»በማለት የመሃል ዳኛው አቶ ሸለመ በቀለ በሌሉበት ውሳኔ አሳልፎ ነበር። ሆኖም የመሃል ዳኛው አቶ ሸለመ በቀለ «በግሌ እንዲህ አይነት ቅሬታ እየቀረበብኝ የምሰጠው ውሳኔ አመኔታን ስለማያገኝ በግሌ ከዚህ ችሎት መነሳት እንደምፈልግ ማመልከቻ አስገብቻለሁ።»በማለት ራሳቸውን ማንሳታቸውን ለችሎቱ አሳውቀዋል።

የዘጠኙ ተከሳሾች ጠበቃ አምሃ መኮንን መሻሻል አለባቸው የተባሉት የክሱ ክፍሎች አለመሻሻላቸውን ይናገራሉ።«ሶስተኛ ተከሳሽ ክሱ ላይ 48,000 ብር ተቀብሏል ተብሎ ነበረ።ከማን ተቀበለ?ለምን አላማ አዋለ? የሚለው ይግለጽ ሲባል ይኸ ትዕዛዝ ግልጽ ነው። ይኸንን ግልጽ አድርጎ ማቅረብ ይቻል ነበረ።ግልጽ አድርጎ ያላቀረበው ብይኑ ስላልገባው ነው ብሎ መውሰድ ያስቸግረናል።ፍርድ ቤቱም አቃቤ ህግ ይኸንን ግልጽ ትዕዛዝ አሻሽሎ ሳይቀርብ ሁለተኛ እድል መስጠት ሳይሆን የነበረበት ፍሬ ነገሩን ከክሱ ውስጥ መሰረዝ ወይም ባጠቃላይ ክሱንም የሚያሰርዘው ከሆነ ክሱን መሰረዝ ነበረበት።» ሲሉ ተናግረዋል።

ስድስቱ ጦማሪያን እና ሶስት ጋዜጠኞች በሽብርተኝነት ወንጀል ተጠርጥረው ከታሰሩ ጠዘኝ ወራት አልፈዋል። ለ19ኛ ጊዜ ችሎት የቆሙት ተከሳሾች መደበኛ ክስ ከቀረበባቸው ስድስት ወራት አልፈዋል። ጠበቃ አምሃ መኮንን «ካጠቃላይ የኢትዮጵያ የፍትህ ስርዓት አኳያ ብዙ ጉዳዮች በዚህ ደረጃም ከዚህ በበለጠ ሁኔታም ሲጓተቱ እናያለን።በዚህ ጉዳይ ግን ከዚህ ባነሰ ማስኬድ ይቻል ነበር።» ሲሉ ይናገራሉ።

ጋዜጠኞቹ ተስፋለም ወልደየስ፣ አስማማው ሃይለ ጊዮርጊስ እና ኤዶም ካሳዬ እና የዞን ዘጠኝ ጦማር ጸሃፊ የነበሩት ዘላለም ክበረት፣ ናትናኤል ፈለቀ፣ አጥናፍ ብርሃነ፤አቤል ዋበላ፤ማህሌት ፋንታሁንና በፍቃዱ ኃይሉ የታሰሩት ሚያዝያ 17 ቀን 2006 ዓ.ም ነበር።

‘ህዝብን ለአመጽ ነማነሳሳት፤ህገ-መንግስቱንና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በአመጽና በሁከት ለመለወጥ፤በህቡዕ ተደራጅቶ የሽብር ወንጀል ለመፈጸም’የሚል ክስ የቀረበባቸው ዘጠኙ ወጣቶች የጥር 28 ቀን 2007 ቀጠሮ 19ኛ ችሎት ነው። ሶልያና ሽመልስን በሌችበት ባካተተው ክስ የኢትዮጵያ መንግስት ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ከፍተኛ ትችት ሲቀርብበት ቆይቷል። የጦማሪዎቹና የጋዜጠኞቹ የክስ ሂደት ለየካቲት 11 ቀን 2007 ዓ.ም. የተቀጠረ ሲሆን በቀጣዩ ቀጠሮ ችሎቱ በአዲስ የመሀል ዳኛ የተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃል እንደሚቀበል ታውቋል።

እሸቴ በቀለ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic