ዳርፉር እና የለጋሽ ሀገራት ጉባዔ | አፍሪቃ | DW | 06.04.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ዳርፉር እና የለጋሽ ሀገራት ጉባዔ

በምዕራብ ሱዳን የዳርፉር ግዛት ዓማፅያን በማዕከላዩ መንግሥት አንፃር ትግል ከጀመሩ ከአሥር ዓመታትም በኋላ አካባቢው ሰላም እና መረጋጋት እንደጎደለው ይገኛል። እአአ ከ 2003 ዓም ወዲህ በዳርፉር በቀጠለው ውዝግብ ፡ በተመድ ዘገባ መሠረት፡ አሥር ዓመት በሆነው ውዝግብ ከ300,000 የሚበልጥ ሰው ተገድሎ፡

2, 5 ሚልዮን ደግሞ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሎዋል ወይም ተሰዶዋል።ደሚታወቀው፡ የሱዳን ፕሬዚደንት ኦማር ሀሰን ኧል በሺር በዳርፉር በተፈፀመው የጦር ወንጀል የተነሳ ተጠያቂ በሚል ዘ ሄግ ኔዘርላንድስ በሚገኘው ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት ክስ ተመሥርቶባቸዋል።
የዳርፉር ሕዝብ በአሁኑ ጊዜ በጦርነት የተዳቀቀውን ግዛቱን መልሶ ለመገንባት ቆርጦ የተነሳ ሲሆን፡ ለዚሁ ዕቅድ ማሳኪያ አስፈላጊ ነው የሚባለውን በብዙ ሚልዮን የሚገመተውን ገንዘብ ለማሰባሰብ ቓታር ከነገ ጀምራ በመዲናዋ ዶሀ የሁለት ቀናት የለጋሽ ሀገራት እና ድርጅቶች ጉባዔ ታስተናግዳለች።

ይሁንና፡ ውጊያ እና ጦርነት እየተካሄደ በዳርፉር መልሶ ግንባታ ማነቃቃት የማይታሰብ ነው በሚል ብዙዎች ማጠያየቅ ይዘዋል። በዚያም ሆነ በዚህ ግን በዶሀ የሚካሄደው ዓቢይ ጉባዔ በዳርፉር በታየው አስከፊ ሰብዓዊ ቀውስ የተነሳ ከጥቂት ዓመታት በፊት የዓለም አቀፉን መገናኛ ብዙኃንን ትኩረት አግኝቶ የነበረው እና አሁን የመረሳት ዕጣ የገጠመው የዳርፉር ውዝግብ እንደገና የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የመወያያ አጀንዳ ሊሆን የሚችልበትን ዕድል መክፈቱ የማያጠራጥር መሆኑን በተመድ የልማት ትብብር መርሀግብር ባልደረባ የርግ ኩሄኔል ገልጸዋል። የዳርፉርን ውዝግብ በተመለከተ እስከዛሬ የተገኘው ገንዘብ ለሰብዓዊ ርዳታ እና በዚያ እአአ ከ 2007 ዓም ወዲህ ለተሠማሩት20,000 የተመድ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች እና ፖሊሶች ተግባር ማከናወኛ ነው የዋለው። ይህ ሁኔታ ግን አሁን ለዳርፉር በሚወጣ አዲስ የመልሶ መርሀግብር ስልት መቀየር እንደሚኖርበት ኩነል አስታውቀዋል።
« ይህ አዲሱ ስልት ዳርፉርን ከጥገኝነት በማላቀቅ ግዛቱ የራሱን ኤኮኖሚ የሚገነባበት፡ ማህበራዊ ኑሮውን እና ያካባቢ መስተዳድሩን አውታር የሚያስፋፋበትን ዕድል የሚያስገኝ ይሆናል። »


ከዚህ በተጨማሪ ስልቱ በብዙ ሲህ የሚቆጠሩት የዳርፉር ስደተኞች ወደ ትውልድ ቦታቸው መመለስ የሚችሉበትንም ዕድል እንደሚከፍት የርግ ኩነል አስታውቀዋል።
በተመ የልማት መርሀ ግብር መሥሪያ ቤት ዩኤንዲፒ ዘገባ መሠረት ፡ ይህንኑ ግዙፍ ፕሮዤ ተግባራዊ ለማድረግ ስድስት ዓመታት እና ሰባት ቢልዮን ዶላር ያስፈልጋል። ከዚሁ ገንዘብ መካከል አንድ ሦስተኟውን ደቡብ ሱዳን ሐምሌ 2011 ዓም ነፃነቷን ካገኘች ወዲህ ግዙፍ የኤኮኖሚ ችግር ያጋጠመው የሱዳን መንግሥት ለመስጠት ዝግጁነቱን ገልጾዋል። እንግዲህ ለዳርፉር የተነደፈው አዲሱ የመልሶ ግንባታ መርሀግብር ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል ለጋሽ ሀገራትንና ድርጅቶችን ማሳመን የዳርፉር ግዛት ኃላፊነት እንደሚሆን አስተዳዳሪው ቲጃኒ ሴሲይ አስታውቀዋል። እአአ በ 2011 ዓም በዶሀ ቓታር ከሱዳን መንግሥት ጋ የሰላም ውል የተፈራረመው የነፃነት እና የፍትሕ ንቅናቄ የተባለው የአንዱ የዳርፉር ዓማፅያን ቡድን አባል የነበሩት ቲጃኒ ሲሴይ በወቅቱ ዳርፉር ለመልሶ ግንባታው ዝግጁ መሆንዋን እና በቦታውም አስተማማኝ ፀጥታ መኖሩን የተጠራጠሩትን ለጋሽ ሀገራት እና ድርጅቶችን ለማሳመን ቆርጠው መነሳታቸውን ገልጸዋል።
« የፀጥታው ሁኔታ በዶሀ የሰላም ውል ከተፈረመ ወዲህ በጉልህ ተሻሽሎዋል። ይህንን ለውጥ ሁሉም፡ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ጭምር መጥቶ ሊያየው ይችላል። በርግጥ፡ ማሸነፍ ያለብን አንዳንድ ፈተናዎች አሁንም አሉ። ከነዚህም አንዱ በተለይ የሰላም ውል ያልፈረሙትን እና በደቡብ ሱዳን የሚረዱትን ያማፅያን ቡድኖችን ማሸነፍ ነው። »
እንደሚታወቀው፡ ብዙ የዳርፉር ዓማፅያን ቡድኖች አሁንም ከሱዳን ማዕከላይ መንግሥት ጋ የሰላም ውል ለመፈራረም ፈቃደኞች አይደሉም። በዚህም የተነሳ አልፎ አልፎ በመንግሥትና ባማፅያኑ ቡድኖች መካከል፡ እንዲሁም፡ በተለያዩት ጎሣዎች መካከል አሁንም ግጭት ይካሄዳል። የጀርመናውያኑ የፍሪድሪኽ ኤበርት ተቋም ባልደረባ ወይዘሮ ክሪስቲን ሊንከ እንደሚሉት፡ ለዳርፉር መልሶ ግንባታ የሚያስፈልገውን ብዙ ቢልዮን ዶላር ለመስጠቱ ሁኔታ ባካባቢው መረጋጋት የሚረጋገጥበት ድርጊት ዋነኛ ቅድመ ግዴታ ነው። ይህንን መረጋጋት ለማስገኘትም በከፊል ሳይሆን በዳርፉር ከሚንቀሳቀሱ ያማፅያን ቡድኖች ጋ የሚፈረም አጠቃላይ የሰላም ስምምነት አስፈላጊ ይሆናል። እንግዲህ ዓለም አቀፍ ለጋሽ ሀገራት እና ድርጅቶች በዳርፉር የተጀመረው የሰላም ሂደት አስተማማኝ ነው በሚል ለዚሁ ግዛት መልሶ ግንባታ ዝግጁ መሆን አለመሆናቸው ነገን እና ከነገ ወዲያ በዶሀ ቓታር የሚካሄደው ጉባዔ ከተጠናቀቀ በኋላ የሚታይ ይሆናል።

ዩሊያ ሀን/አርያም ተክሌ

መሥፍን መኮንን

Audios and videos on the topic