ዳርፉርን የተመለከተዉ የተመድ የጄኔቫ ጉባኤ | የጋዜጦች አምድ | DW | 14.12.2006
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

ዳርፉርን የተመለከተዉ የተመድ የጄኔቫ ጉባኤ

የባለሙያዎች ቡድን ወደዳርፉር በመሄድ በስፍራዉ ስላለዉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የራሱን ምርመራ እንዲያካሂድ ጄኔቫ የተሰበሰበዉ የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ልዩ ጉባኤ ወሰነ።

ሆኖም ጉባኤዉ የካርቱም መንግስትን በሚመለከት የሰነዘረዉ ትችት አለመኖሩ ነዉ የተዘገበዉ። የመርማሪዉ ኮሚሽን በዳርፉር የተፈፀመዉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እንጂ የተፈጥሮ አደጋ ያስከተለዉ እንዳልሆነ በግልፅ ቢያቀርብም የካርቱምን መንግስት ሚና አልጠቀሰም። የምክር ቤቱ አባላትም ባሳለፉት ዉሳኔ ስለዳርፉር የሰብዓዊ ቀዉስና የሰብዓዊ መብቶች ይዞታ ያላቸዉን ስጋት ገልፀዋል። የሱዳን መንግስት ከመንግስታቱ ድርጅት ጋር ለችግሩ መፍትሄ ለማፈላለግ በጋራ መስራት እንደሚኖርበትም ተጠቁሟል።
የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በዳርፉር ስለተፈመዉና በመካሄድ ላለዉ የስብዓዊ መብቶች ጥሰት የሱዳንን መንግስት በድጋሚ ለማዉገዝ ብዙም አልሞከረም። ሁለት ቀናት የቆየዉ ጉባኤ ችግሩን አንስቶ ከተነጋገረ በኋላ የተለሳለሰ ዉሳኔ ለማሳለፍ ብዙ ታግሏል። ከአዉሮፓ ህብረት የቀረበዉ የዉሳኔዉ ረቂቅ ጠንከር ያለ ይዘት የነበረዉ ሲሆን ዉሳኔ ሆኖ ሲወጣ ግን ተበርዟል። ምክር ቤቱ በወረቀቱ ላይ በግልፅ ያሰረፈዉ በተፈፀመዉና በሚፈፀመዉ ጥቃት ያደረበትን ስጋትና የሰላማዊ ዜጎች ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል የሚለዉን ነዉ። የሱዳን መንግስትንና ይደግፋቸዋል የሚባሉትን ሚሊሺያዎች ሚና በሚመለከት በዉሳኔዉ ላይ የተጠቀሰ አንዳች ነጥብ የለም። በምክር ቤቱ የሙስሊም ሀገራት፤ እንዲሁም የቻይናና የሩሲያ አማካሪዎች አብላጫዉን ቁጥር በመበርከቱ ተፅዕኗቸዉ ቀላል አይደለም ነዉ የተባለዉ። እናም የካርቱሙን መንግስት ተግባር የማዉገዙ ነገር ሊሳካ ያልቻለዉ በዚሁ ተፅዕኖ ሳቢያ መሆኑ ተጠቅሷል።
ለሁለት ቀናት ለተካሄደዉ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ልዩ ጉባኤ ከመንበራቸዉ ሊሰናበቱ ጥቂት ቀናት የቀሯቸዉ ዋና ፀሃፊ ኮፊ አናን ጠንከር ያለ መልዕክት አስተላልፈዋል። በመልዕክታቸዉም ምክር ቤቱ ልዩ ልዑካንን ያካተተ ገለልተኛ ቡድን ሄዶ ችግሩን በአይኑ እንዲያይና ዘገባ እንዲያቀርብ አሳስበዋል።

«ሁሉንም ለማስጠንቀቅ በመላዉ ዓለም ስም በአሁኑ ሰዓት በዳርፉር ያለዉ ሁኔታ ተቀባይነት እንደሌለዉና መቀጠል እንደማይኖርበት ምክር ቤቱ የራሱን ግልፅና የጋራ መልዕክት መላኩ አስፈላጊ ነዉ። የዳርፉር ህዝቦች ከእንግዲህ ወዲያ ሌላ ተጨማሪ ቀን የሚጠብቁበት አቅሙም የላቸዉም። ጥቃቱ የግድ መቆም አለበት።»
የቪዲዮ መልዕክታቹን ለጉባኤዉ ያደረሱት አናን በዳርፉር የሚገኙት ወገኖች ለሶስት ዓመታት ያሉበትን ስቃይ እንዲታሰብ አድርገዋል። ከዚህም በተጨማሪ አናን በዳርፉር የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ዉስጥ እጃቸዉን የከተቱ የመንግስት አካላትም ሆኑ ሌሎች ወገኖች ለፍርድ የሚቀርቡበት ሁኔታ ባስቸኳ እንዲወሰን አሳስበዋል። ከሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾችና ከከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የቀረቡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በዳርፉር በተፈፀመዉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የካርቱም መንግስት እንጁን ከቷል። የጀርመን አምባሳደር ሚኻኤል ሽታይነር በዚህ ተግባር የሱዳን መንግስት አለመወገዙ አሳዝኗቸዋል። ሆኖም አምባሳደሩ ትንሽ የተደሰቱበት ነገር የዳርፉር ጉዳይ እንደአንድ የመወያያ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ጊዜ ተሰጥቶት መነጋገር የተቻለበትን አጋጣሚ ነዉ። በተጨማሪም ገለልተኛ የባለሙያዎች ቡድን ወደዳርፉር ሄዶ የጥቃቱን መጠን እንዲመረምር መወሰኑንም በድስታ ተቀብለዉታል። Human Rights Watch የተሰኘዉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች በዳርፉር ስላለዉ የመብቶች ጥሰት ምስጢሩን ይፋ ባያደርግ ኖር በስፍራዉ ተራፊ ባልተገኘም ነበር የሚሉም አሉ። ጄኔቫ የሚገኘዉ የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ግን ኒዮርክ እንደሚገኘዉ የፀጥታዉ ምክር ቤት በአንድ አገር ላይ ማዕቀብ የመጣል ስልጣኑ የለዉም። እንደታዛቢ የአፍሪካና አረብ ሀገራትስ ተሳትፎ ምን ሊሆን ይችላል የሚለዉም ተነስቷል። የመንግስታቱ ድርጅት ከፍተኛ ልዑካንም በሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽኑ ፕሬዝደንት መሪነት ወደስፍራዉ እንደሚሄዱ ይጠበቃል።