ዲፕሎማሲ፤ ተቃዉሞና ዉሳኔ በቡድን 8ቱ ጉባኤ | ዓለም | DW | 08.06.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ዲፕሎማሲ፤ ተቃዉሞና ዉሳኔ በቡድን 8ቱ ጉባኤ

የቡድን ስምንቱን ጉባኤ ሂደትና ወጪዉን የሚከታተሉ በርካቶች ትችት እየሰነዘሩ ነዉ። ለጉባኤዉ ለሁለት ቀናት ብቻ የወጣዉ ዉጪ ከጉባኤዉ ከተገኘዉ ጥቂት ዉጤት ጋ ሲነፃፀር አይገናኝም።

ተቃዉሞ በኃይሊገን-ዳም

ተቃዉሞ በኃይሊገን-ዳም

የስምንቱ ባለፀጋ ሀገራት ጉባኤ ምንም እንኳን እንደተጠበቀዉ በአየር ጠባይ ለዉጥ ረገድ ጠንከር ያለ ዉሳኔ ላይ ባይደርስም ለቀጣይ እርምጃዎች ፈር ቀዳጅ ሊባል የሚያስችል ነጥብ ላይ ደርሷል። ይኸዉም ለመጀመሪያ ጊዜ እነዚሁ በኢንዱስትሪ ያደጉት ሀገራት በከባቢ አየር ላይ በአደገኛ ጋዞችና የኢንዱስትሪ ዝቃጭ ሳቢያ ለደረሰዉ ጉዳት ካሳ መክፈል ይገባል በሚለዉ መሰረታዊ ሃሳብ ላይ መስማማታቸዉ ዓብይ እርምጃ ተብሎለታል። በዚሁ መሰረትም በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ዉስጥ በተባበሩት መንግስታት አማካኝነት በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የካርቦን ዳይኦክሳይድን መጠን ለመቀነስ በህግ ለመደንገግ ታስቧል። ከተጨባጩ እዉነታ በመነሳት ከዚህ የበለጠ መጠበቅ አይቻልም፤ ከዚህ ያነሰዉም ደግሞ እዚህ ግባ አይባልም።

የወቅቱ የብድን ስምንት ሊቀ-መንበርነቱን የያዘችዉ የጀርመን መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክልም እንደገመቱት በጉባኤዉ ላይ የተጫወቱት የዲፕሎማሲ ሚና ስኬታማ ሆኗል ተብሎላቸዋል። ሜርክል ጉባኤዉ በአየር ጠባይ ረገድ በተወያየበት ወቅት አንድ ጥሩ ነጥብ አነሱ፤ ከዚያ በኋላ ጃፓንም ሆነች ዩናይትድ ስቴትስ ነገሩን ወደኋላ መድረግ አልቻሉም ተከተሏቸዉ። በኢንዱስቲዉ ዘርፍ ቀና ማለት የጀመሩት እንደ ቻይናና ህንድ ያሉት አዳጊ አገራትን የሚያስገድድ ዉሳኔ አልተላለፈም። እነቻይናና መሰል ሀገራት በፈጣን ሁኔታ በማደግ ላይ የሚገኘዉ የኢንዱስትሪ ዘርፋቸዉ ለአየር ጠባይ መለወጥና ብክለት የበኩሉን አስተዋፅዖ ማድረጉ ባይቀርም በዚህ ጉባኤ እንደታዛቢ ነዉ የተገኙት። ሆኖም እነዚህ የብልፅግናዉን ጎዳና የተያያዙት ወገኖች በቀጣዮቹ ጥቂት ዓመታት ዉስጥ በከባቢ አየር ላይ የከፋ ጉዳት የማድረሱ አቅም አላቸዉና ከወዲሁ በመንግስታቱ ድርጅት የህግ ጥላ ስር እንዲገቡ ድርድሩን ከወዲሁ ማፋጠኑ አማራጭ የለዉም። ለማንኛዉም ለዓለም የአየር ጠባይ ደህንነት ለሚሟገቱ ወገኖች ይህ መልካም መልዕክት ነዉ።

በአንፃሩ በከፍተኛ ደረጃ ጥበቃዉ በተጠናከረበት የቦልቲክ ባህር ዳርቻ በሚካሄደዉ ጉባኤ የሚያዝናና ነገርም አልጠፋም። ከመነሻዉ ዩናይትድ ስቴትስ ሮኬት መከላከያ ለመትከል ማሰቧን የተቃወመችዉ የሩሲያ ፕሬዝደንት ቪላድሚር ፑቲን አቋም ያለፈዉን ቀዝቃዛ ጦርነት ዳግም ይቀሰቅሳል በሚል የስጋት ድባብ ነበር። ከፕሬዝደንት ቡሽ ጋ ፊት ለፊት ከተነጋገሩ በኋላ ፑቲን አገራቸዉ ትተክላለች ያሉትን የሚሳኤል ወር ዳግም ሲያነሱት አልተሰማም። እንደዉም ሩሲያ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋ በሚሳኤል ተከላዉ የምትተባበርበት ሁኔታ ነዉ የሚታሰበዉ። ይህ የሚያመላክተዉም ፊት ለፊት የመነጋገሩን ጠቃሚነት ሲሆን ካለፍ አገደም በጉባኤም ሆነ በተለያዩ መድረኮች ተገናኝቶ ችግር የተባለዉን ሁሉ እያነሱ መነጋገር ዉጤት እንዳለዉ ነዉ። ዩናይትድ ስቴትስ የምትተክለዉን ሚሳኤል በመቃወም ወደማዕከላዊ አዉሮፓ የሚያነጣጥር ሚሳኢል ለመትከል ያሰበችዉ ሩሲያም ከወጪ ሲትድን፤ ሌሎች ሀገራትም በመሰል የመሳሪያ ማምረት ፉክክር ሊያባክኑት የሚችሉት ጊዜና ገንዘብ ተርፏል። ትናንት ራት ላይ ፑቲንና ቡሽ ነፃ ሆነዉ በሰፊዉ የመነጋገር አጋጣሚ ያገኙ ሲሆን ያን የመሰለ ጠንከር ያለ አፀፋ ለዋሽንግተን ፍላጎት ከሞስኮ የተሰማ አይመስልም ነበር። ቡሽ ሚሳኤል ለመትከል ወዳለሙባት ፖላንድ ዛሬ ጉባኤዉ ሲያበቃ ብቅ እንደሚሉ ይጠበቃል። የዛሬዉን ማለዳ ጉባኤ ግን በገጠማቸዉ የሆድ ህመም ሳቢያ አልተካፈሉም።

ከጉባኤዉ በተጓዳኝ የአፅናፋዊ ዓለም ትስስርን የሚቃወሙ፤ የተፈጥሮ አካባቢ ተቆርቋሪዎች እንዲሁም ሌሎች የተቃዉሞ ድምፅ የሚያሰሙ በስፍራዉ ተገኝተዉ ጩኸታቸዉን እያሰሙ ነዉ። ከተቃዋሚዎቹ አንዱ እንዲህ ይላሉ

«ይኽ የወይዘሮ ሜርክል ጉባኤ አልተሳካም። ከባቢ አየርን በመንከባከቡ ጥረት አቶ ቡሽን አካትታለሁ ብለዉ የተጠቀሙበት ስልትም እንዲሁ ከሽፏል።!»

በዛሬዉ ዕለት የባለፀጋዎቹ ሀገራት መሪዎች ትኩረት እንዲሰጧቸዉ በጋዝ ነበልባል በአየር ላይ በሚንሳፈፍ ግዙፍ ፊኛ ለመብረር የሞከሩት Greenpeace የተሰኘዉ የተፈጥሮ ተሟጋች ቡድን ከ15 ደቂቃ በኋላ የፖሊስ ሄሊኮፕተር በፈጠረበት የንፋስ ሞገድ ለመዉረድ ተገዷል። ፊኛዉ አሁኑኑ እርምጃ ዉሰዱ የሚል መፈክር የተፃፈበት ሲሆን በዉስጡ ሁለት የጉዳዩ ተሟጋቾች ነበሩበት። በባህርም ቢሆን በጀልባ በአካባቢዉ በመሽከርከር አቅም ያላቸዉ እነዚህ መሪዎች አንድ ነገር እንዲያደርጉ የጠየቁ ቡድኖች ነበሩ።ተቃዉሞዉ ምናልባት የመገናኛ ብዙሃንን ሽፋን ከማግኘት ባሻገር የትም ላይደርስ ይችላል፤ ብዙዎች ግን የዲሞክራሲያዊ ስርዓት የሚከፍለዉ ዋጋ ይህን ይመስላል ብለዉታል።

በዚህ ጉባኤ ላይ የብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመጨመረሻ የፈንረሳዩ ኒኮላስ ሳርኮዚ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ነዉ የተገኙት።