ደብዛዛው «ግንቦት 20» እና የጋዜጠኛ እስር በአዲስ አበባ | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 31.05.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ደብዛዛው «ግንቦት 20» እና የጋዜጠኛ እስር በአዲስ አበባ

​​​​​​​ዘንድሮ የግንቦት 20 መታሰቢያ በዓል ከትግራይ ውጪ በሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች እንዳልተከበረ መገለጡ በርካታ አስተያየቶች አጭሯል። የዓለም የፕሬስ ቀንን አስተናግዳ በተወደሰችው ኢትዮጵያ ጋዜጠኛ ማሰር መፍታት ተጀምሯል። ደብረ ማርቆስና በተለያዩ ቦታዎች ለተከሰቱ ግድያዎች የሚሰጡ አስተያየቶች በብዛት ወገናዊነት ይንጸባረቅባቸዋል ተብሏል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 07:56

ግድያውን ለፖለቲካ ዓላማቸው የተጠቀሙ ታዋቂ ግለሰቦች ነበሩ

ዘንድሮ የግንቦት 20 መታሰቢያ በዓል ከትግራይ ውጪ በሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች እንዳልተከበረ መገለጡ በርካታ አስተያየቶች አጭሯል። «እኛ ኢትዮጵያውያን ሁሉን ነገር ያጣንበት» እና «ወንድም ወንድሙን የገደለበት ቀን» ከሚሉ ጀምሮ «ደርግ የሆነ ኣያከብረውም» እስከሚሉ  ድረስ የተለያዩ አስተያየቶች ተንጸባርቀዋል። ኢትዮጵያ የዓለም የፕሬስ ቀንን አሰናድታ በተወደሰች ማግስት ጋዜጠኛ አዲስ አበባ ውስጥ በኦሮሚያ ክልል ፖሊስ መታሰሩ እጅግ አወዛግቧል።  በደብረ ማርቆስ እና በተለያዩ ቦታዎች ሰሞኑን ለተከሰቱ ግድያዎች የሚሰጡ አስተያየቶች በብዛት ወገናዊነት እንደሚንጸባረቅባቸው የማኅበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች ገልጠዋል። 

ግንቦት ሃያ

ለ17 ዓመታት ኢትዮጵያን የመራው ወታደራዊ መንግሥት ደርግ ከሥልጣን የተወገደበት የግንቦት 20 መታሰቢያ በዓል ዘንድሮ ከትግራይ ውጪ በሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች አለመከበሩ ተገልጧል። በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ የተሰጡ አስተያየቶች በአመዛኙ የግንቦት 20 በዓልን አጥብቀው የሚኮንኑ ናቸው። «ግንቦት 20 ኢትዮጵያ የባሕር በሯን ያጣችበት፣ ዘረኝነት የተዘራበት፣ ሕዝባችን የተሰደደበት፣ መሬታችንን ጨምሮ ንብረታችንን የተዘረፍንበት፣ በአጠቃላይ እንደ አገር የተዋረድንበት ነው» ሲል መረር ያለ ትችቱን በተቀናበረ ምስል ያቀረበው አብርሃም ይስሐቅ የተባለ የፌስቡክ ተጠቃሚ ነው።

«ግንበት 20 ማለት፤ ገና ከጅምሩ ሀገርና ሕዝብ እንዴት እንደሚመራ የሰከነ ሐሳብ የሌላቸው፣ ከጫካ የመጡ ቀማኞች፤ ጠላት በሚሉት ብዙኃን የእትዮጵያ ሕዝብ ላይ ባጋጣሚ ያገኙትን ወታደራዊ ድል በመጠቀም ዘረኛ፣ አምባገነናዊና ፋሽስታዊ የብቀላ ሥርዓት ያቋቋሙበት ቀን ነው» የሚል አስተያየት የሰጠው ደግሞ ዕዮብ ገለታ ነው። ሰፋ ካለው የፌስቡክ ጽሑፉ የተቀነጨበውን ነው ያሰማናችሁ።

መዲድ ሞሐመድ ቀደም ሲል የተሰሙት ሐሳቦችን ይቃወማል።  «ቢያንስ ደስ ብሎናል» ሲልም ጽሑፉን ያንደረደራል። «ሰው በላ ሥርዓት ላንዴና ለመጨረሻ እናም ላይመለስ ከጭቁኖች ጫንቃ ወርዶ የተቀበረበትና ፌዴሬሽን፣ (ከነ ችግሩ) የጀመርንበት። እንኳን አደረሰን» ብሏል።

«የአዲስ ስታንዳርድ» ድረ-ገጽ ጋዜጣ ዋና አርታኢ ፀዳለ ለማ በትዊተር ገጿ በእንግሊዝኛ ግንቦት 20ን ደግፋ ለምን እንደምታከብረው ጽፋለች። ፀዳለ ግንቦት 20ን የምታከብረው እሷ «መኾን ይገባዋል» ባለችው መንገድ «ኢትዮጵያን ዳግም በመቅረጹ» እና «በመተንተኑ» ረገድ «ታሪካዊ መገለል የደረሰባቸው» ስትል የጠቀሰቻቸው ቡድኖች በተሻለ መልኩ «እንዲካተቱ» ቀኑ ፖለቲካዊ እና ባሕላዊ ጥርጊያ በማበጀቱ እንደኾነ ጠቅሳለች። 

ከዚህ ቀደም ሲከበር የነበረውን የግንቦት ሃያ በዓል በተመለከተ፦ «ትዕይንት ነው የነበረው ሲል የተቸው ኢጂ ኃይሌ የተባለ የትዊተር ተጠቃሚ ለፀዳለ መልስ ቀጣዩን በአማርኛ አስፍሯል። «ያው ግንቦት 20 ጨቋኝ የምትሉትን ብሄር ለማንኳሰስ ምታከብሩት በዓል ነው! የሚያሳዝነኝ ግን ጨቋኝ የተባለ ህዝብ የደርግም የጥይት ዕራት የነበረ መሆኑ ነው» ብሏል።

«እንኳን Down Down ወያኔ ወደ ግንቦት 20 ኬኛ በሰላም እና በስልጣን አሸጋገራችሁ የብሩክቲ አጠር ያለ የትዊተር መልእክት ነው።

«ቆይ ግን ለኤርትራውያን [መልካም የነጻነት ቀን ወንድሞቻችን] ብሎ ግንቦት 20 አላከብርም የሚለው ኢትዮጵያዊ ግን እንዴት ነው ትንሽ [አይጋጭም] ሁለቱ ንግግር የሚል መልእክት የጻፈችው ደግሞ ዓና ናት ትዊተር ገጿ ላይ።

ሰሚራ በፌስቡክ ጽሑፏ ግንቦት 20ን እንዲህ ነው የምትገልጠው፦ «ወንድም ድሙን ያሸነፈበት፤ ሀገር ወዳዱ መሪ ከሀገር የለቀቀበት፤ ኢትዮጵያ ብሄር በሚባል አጥር የተከፋፈለችበት፤ ለሀገር ሳይሆን ለውስን ግለሰቦች ጥቅም ሲባል ብዙ ሰው ያለቀበት ቀን ምኑ ነው የሚከበረው? ግንቦት 20 ድል አደረግን ያሉትም የቻሉትን ያኽል በልተዋል የምን በአል ነው? እሰይ ያገሬ ህዝብ ነቃክ» ሲል ይነበባል የሰሚራ ጽሑፍ።

ጌታሁን ካሣዬ፦ «የራሱን ወንድም ገድሎ የድል ቀን የለም ለዛውም የባሰ ገዳይ መንግሥት ላመጣው ትግል» ሲል ጽፏል።

ግድያ በደብረማርቆስ

በደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ አንድ ተማሪ የመገደሉ ዜና ከየአቅጣጫው ቊጣ አስነስቷል። በዚያው መጠን ግድያውን ለፖለቲካ ዓላማቸው የተጠቀሙ ታዋቂ ግለሰቦች ከመሰል ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የሚጠይቊ አስተያየቶችም በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተንጸባርቀዋል።

በደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲተማሪዎች መካከል ባለፈዉ ሳምንት ማብቂያ በተፈጠረ ችግር የተነሳ ቁጥራቸዉ በዉል ያልተገለፀ በአብዛኛው ከትግራይ የሄዱ ተማሪዎች የዩኒቨርስቲዉን ግቢ ለቀዉ መዉጣታቸዉ ተዘገግቧል።

ኢብኑ አል ነጃሺ የተባለ የፌስቡክ ተጠቃሚ፦ «ዩኒቨርሲቲ ማለት የጦር አውድማ ነው የዕውቀት አውድማ ተምታታብኝ ሲል ይጠይቃል። «ለምን ትምህርቱ ቀርቶ ወደየቤታቸው አይመለሱም? ሲረጋጋ ቀስ ብለው ቢጀምሩስ፤ ደግሞ ለዘመኑ ትምህርት እራስን መስዋዕት ማድረግ ትርጉም-አልባ ስለሆነ ተገቢ አይመስለኝም» ብሏል።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች አማካሪ ወይዘሪት ሶልያና ሽመልስ የደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ግድያውን አውግዘው በትዊተር ገጻቸው በእንግሊዝኛ ጽፈዋል። «የጤና አይደለም፤  ጭካኔ ነው። እንደ ማኅበረሰብ እና ሀገር ስለእኛ ብዙ ይናገራል። መራር እና አሳዛኝ ነው» የሚለው የሶልያና መልእክት ለሟች ቤተሰብ መጽናናትን በመመኘት ይጠናቀቃል።

ቢንያም ዲ ጂ«ሻሸመኔ ላይ ህዝብ በተሰበሰበበት በጠራራ ፀሃይ የሰው ልጅ ቁለቁል ተሰቅሎ ማን እንዳደረገው አናውቅም ሲባል ያልሰቀጠጠው ዛሬ ማርቆስ ላይ በግፍ የተገደለውን ምስኪን ምክንያት አድርጎ የአዞ እንባውን ያነባል። አስመሳይ ሁላ» ብሏል። 

«እየመረጡ ቊጣ ሲል አጭር መልእክት ያስተላለፈው ደግሞ «ናርች 1234» የተባለ የማኅበራዊ መገናኛ ተጠቃሚ ነው። «ብሔር እየመረጣችሁ የትርፍ ጊዜ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆናችሁ ሰዎች ግን ምን ይሻላችኋልይኼ ደግሞ የጥላሁን ጽጌ የትዊተር መልእክት ነው።

አዲስ አበባ የጋዜጠኛ እስር

ሌላው በዚህ ሳምንት የማኅበራዊ መገናኛ ዋነኛ ትኩረት ከነበሩ ጉዳዮች መካከል የኦሮሚያ ፖሊስ የአሐዱ ራዲዮ ጣቢያ ድረስ በመምጣት የጣቢያው ጋዜጠኛን አስሮ መፈታቱ ነበር። አንድ የአሐዱ ራዲዮ ጣቢያ ጋዜጠኛና ሌላ ባልደረባዉ «የተዛባ ዘገባ» አሰራጭታችኋል በሚል ነበር ፖሊስ ባለፈዉ አርብ አስሮ ሰኞ የፈታቸዉ።

የቀድሞው «የአርበኞች ግንቦት ሰባት ለአንድነት እና ዴሞክራሲ ንቅናቄ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ» ኤፍሬም ማዴቦ፦ «ኦሮሚያ ፖሊስ ምን አገባዉና አዲስ አበባ መጥቶ ያስራልሲሉ ትዊተር ላይ ጽፈዋል። «የሜዲያ ሰዎች እንደበግ እየተጎተቱ የሚታሰሩ ከሆነ እንዴት ስራቸዉን ይሰራሉ? ሜዲያዉስ ምኑን ነፃ ሆነበማለት የጠየቁት አቶ ኤፍሬም ጽሑፋቸውን የሚያጠናቅቊት፦ «ኧረ በህግ አምላክ» በማለት ነው።

የአሐዱ ሬዲዮ ጋዜጠኛ መታሰርን በተመለከተ ኪያ ኤስ ዓሊ ሰኞ ግንቦት 19 ቀን፣ 2011 ዓም ማኅበራዊ መገናኛ አውታር ላይ ያቀረበው የእንግሊዝኛ ጽሑፉ፦ «ይህ የኾነው ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ እስር ቤት አንድም ጋዜጠኛ  የለም ባሉ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነው» ብሏል።  ፍጹም ሥልጣን አሰፋ ትዊተር ገጹ ላይ፦ «ዘንድሮም እያሰርን ነዉ ሲል በአጭሩ ጠይቋል።  

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች