ደብብ ሱዳን፣ የተመድ ሰላም አስከባሪዎች እና ተፈናቃዮች | አፍሪቃ | DW | 07.03.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ደብብ ሱዳን፣ የተመድ ሰላም አስከባሪዎች እና ተፈናቃዮች

በደቡብ ሱዳኑ የርስ በርስ ጦርነት ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ደቡብ ሱዳናውያን በተለይም ሴቶች ከስጋት ጋር ነው የሚኖሩት ። በተመድ ሰላም አስከባሪዎች በሚጠበቁ መጠለያዎች ውስጥ የሚገኙት ቢያንስ ለፀጥታቸው ላይሰጉ ይችላሉ ። ይሁንና ከመጠለያው ወጥተው በሰላም ለመመለሳቸው ግን ዋስትና የላቸውም ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:55

የተመድ ሰላም አስከባሪዎች በደቡብ ሱዳን

በደቡብ ሱዳን ሰሜናዊ ክፍል በሚገኘው የማላካል የተፈናቃዮች መጠለያ ውስጥ ያሉት ጎጆዎች ካከርቶን፤  ከብረት እና ከእንጨት የተሰሩ ሲሆን  በፀሐዩ ብዛት ቀለማቸው እየለቀቀ እና እያረጀ ነው ። ከየመፀዳጃው የሚወጣው ፍሳሽ ግቢውን በመጥፎ ሽታ አውዶታል  ።በስፍራው ዶሮዎች ጫጩቶች ሲሯሯጡ ይታያል ።የተመ የህፃናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ በመጠለያው ለሚኖሩ የመጠጥ ወሐ ያከፋፍላል ፤ያስተምራልም ።የሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሠራተኞች ደግሞ ለተፈናቃዮቹ ምግብ እና ሕክምና ይሰጣሉ ። በመጠለያው ያሉት የሺሉክ እና የኑዌር ጎሳ አባላት ናቸው ። አብዛኛዎቹም  ሴቶች እና ህጻናት ናቸው ። ወንዶቹ ሀገሪቱ ውስጥ በተለያዩ ግንባሮች ተሰልፈው ይዋጋሉ ። በዚያ የሚገኙ የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪዎች ተግባር የመጠለያውን ነዋሪዎች መጠበቅ ነው ። ለዚሁ ሥራም በአሸዋ የተሞሉ ከረጢቶችን በመጠለያው ዙሪያ እንደ አጥር ደርድረዋል ።ከርቀት ለማየት የሚያመቹ ረዣዥም ማማዎች መጠለያዎቹ ውስጥ ይገኛሉ ። በመጠለያው በር ላይ የተመድ ወታደሮች አሉ ።  መጠለያው ውስጥ የፀጥታ ስጋት የለም ። ይሁን እና የመጠለያው ነዋሪዎች በተለይም ሴቶች ከግቢው  ከወጡ ግን ለአደጋ ይጋለጣሉ ይላሉ በመጠለያው በሚገኝ የሴቶች ማዕከል ውስጥ የሚሠሩት ዲስዚፓ ጊምስ ።
«ሴቶቹ ማገዶ ፍለጋ ከወጡ ሊደፈሩ ይችላሉ።ከግቢው ከወጡ በኋላ የሚገኘው መንገድ አደገኛ ነው።»

ችግሩ ሰዎቹ መጠለያው ውስጥ የሚያገኙት በህይወት ለመቆየት የሚያስችላቸውን እጅግ አስፈላጊ ምግቦች ብቻ ነው ።የተመጠነ ሩዝ፤ ማሽላ እና አትክልቶች ይሰጧቸዋል  ። ከዚያ በላይ ምግብ ማግኘት የሚፈልግ ከግቢው መውጣት ይኖርበታል ። ብዙ ሴቶች ቀን መጠለያቸውን ለቀው ወደ ጫካ ይሄዳሉ ። የሚሄዱት ማገዶ ፍለጋ ሊሆን ይችላል ። ጫካ ውስጥም አትክልቶችም ይተክላሉ ። በተደጋጋሚ ጊዜያት የዲንቃ ጎሳ አባላት ሴቶቹን እያሳደዱ ይደፍራሉ ። ይህች ስምዋ እንዳይገለጽ የፈለገች ሴት ከዚህ ቀደም በደረሰባት ችግር ምክንያት  የማላካሉን መጠለያ ለቃ ለመውጣት እንደማትደፍር ትናገራለች ። 
«ባለፈው ከግቢው በወጣሁበት ወቅት ወታደሮች ሴቶችን ለማጥቃት ጫካ ውስጥ ተደብቀው ነበር ። እኔና ሌሎች ሴቶች ወታደሮቹን አይተን የተመ ሰላም አስከባሪዎች ወዳሉበት ስንሸሽ ወደ ውስጥ እንዳንገባ ከለከሉን በዚህ ጊዜም ያሳድዱን የነበሩት ከኋላችን ተኩስ ከፈቱብን ። ያኔም የወንድሜን ልጅ አጥቻለሁ ። በተለያየ አቅጣጫ ነበር የሸሸነው ። ወደ መጠለያችን ስንመለስ

መንገድ ላይ የሞቱም አሉ ። »
ደቡብ ሱዳን በሚገኙ መጠለያዎች ውስጥ ጥበቃ የሚያደርጉት የተመድ ወታደሮች ከግቢው ውጭ ያለውን ፀጥታ አልፎ አልፎ ነው የሚቆጣጠሩት  ። አንዳንዴ ወደጎዳናዎች ይወጡ እና ለጥቂት ሰዓታት ተዘዋውረው ይመለሳሉ ። ሌተና ኮሎኔል ራይንሀርድ ሄርማን በደቡብ ሱዳን የተመድ ሰላም አስከባሪ ኃይል ውስጥ ከዘመቱት 16 የጀርመን ወታደሮች አንዱ ናቸው ። ሥራቸውም የተመድ ጦርን እና ሌሎች የሲቪል ተቋማትን ማገናኘት ነው ። የተመድ ሰላም አስከባሪዎች ለምን የመጠለያዎቹን አካባቢዎች እንደማይጠብቁ ተጠይቀው ነበር ።
« ተልዕኮአችን ግልጽ ነው ። ለሰላማዊ ሰዎች ጥበቃ ማድረግ ።እዚህ አስገድዶ መድፈር በየቀኑ ይፈፀማል ። ይህ ጉዳይ ለኔ ከደረሰ አዎ ጣልቃ እገባለሁ ። ሆኖም አስገድዶ መድፈር እንዳልኩት የዕለት ተዕለት ክስተት ነው ።ለእያንዳንዷ ሴት ጥበቃ ወታደር ማሰማራት አይቻልም ። ይህ ሊሆን አይችልም ።»
በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች በሚገኙበት በደቡብ ሱዳን የተሰማራው የተመድ ሠራዊት ቁጥር 13500 ። ይህ ቁጥር ጥበቃ ከሚያስፈልጋቸው ሰላማዊ ሰዎች ቁጥር ጋር ሲነፃጸር ጥቂት ነው፤- እንደ ሌተና ኮሎኔል ሄርማን ።በዚህ የተነሳም በማላካል መጠለያ የሚገኙት ሰዎች ተስፋ ቆርጠዋል ። እንደ አብዛኛዎቹ ደቡብ ሱዳናውያን አንድ ቀን ሀገሪቱን ለቀው የሚወጡበትን መንገድ እያለሙ ነው ። እንደ ሌሎች የአገራቸው ሰዎች መጀመሪያ ሱዳን ከዚያም በሊቢያ አድርገው ወደ አውሮጳ መሻገር ነው ምኞታቸው።

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ 

Audios and videos on the topic