ደቡብ አፍሪካና የኤችአይቪ ኤድስ ስርጭት | የጋዜጦች አምድ | DW | 15.03.2006
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

ደቡብ አፍሪካና የኤችአይቪ ኤድስ ስርጭት

ደቡብ አፍሪካ በአህጉሪቱ ከሚገኙ ሀገራት መካከልም ሆነ ከሌሎች ጋር ስትነፃፀር በርካታ ዜጎቿ በHIV/ AIDS እንደተጠቁባት ነዉ መረጃዎች የሚጠቁሙት።

በቁጥር ሲሰላም ከ47 ሚሊዮን ህዝቦቿ መካከል አምስት ሚሊዮኑ ከቫይረሱ ጋር የሚኖር ነዉ። በአሁኑ ጊዜም የእድሜ ማራዘሚያዉን መድሃኒት በበሽታዉ ለተያዙትና እጅግ ለሚያስፈልጋቸዉ የማዳረሱ ነገር ፈታኝ ሆኗል። ሁኔታዉን በቅርበት የሚያዉቁት ወገኖች የችግሩ መንስኤ የገንዘብ እጥረትም ሆነ የመድሃኒት አቅርቦት ጉድለት አይደለም ይላሉ።
በጆሃንስበርግ ዊትዋተርስራንድ ዩኒቨርሲቲ የኤድስ ፕርጀክት ተጠሪ የሆኑት ፋጡማ ሃሰን እንደሚሉት ይህ መድሃኒት የሚያስፈልጋቸዉ ዜጎች ከ500,000 በላይ ናቸዉ።
በአሁኑ ጊዜ ግን ከተጠቀሰዉ ቁጥር ግማሹን ያህል የሚሆኑት ብቻ ናቸዉ ከአቅምም ሆነ ከአቅርቦት ችግር ጋር በተገናኘ መድሃኒቱን ማግኘት የቻሉት።
ባለፈዉ ህዳር ወይ መንግስት ያወጣዉ መረጃ እንደሚያሳየዉ በሽታዉ የሚያስከትለዉን ጉዳት ለመከላከል በተደረገዉ ጥረት 85,000 ሰዎች ባለፈዉ መስከረም ወር ብቻ የተባለዉን መድሃኒት ለማግኘት በመንግስት የጤና ተቋማት ተገኝተዋል።
ፋጡማ ሀሰንም ባለፈዉ ነሐሴ ወር በግል ደረጃ ይህን መድሃኒት ያገኙት ከ70,000 እስከ 80,000 ይደርሳሉ ባይ ናቸዉ።
ይህ ደግሞ በአገሪቱ መንግስት ለፈረንጆቹ 2005ና 2006ዓ.ም የመድሃኒቱን አቅርቦት ለመደጎምና ለማዳረስ ታቅዶ ከነበረዉ መጠን ጋር ፈፅሞ አይደራረስም።
መድሃኒቱ ለህፃናት ምን ያህል ሊዳረስ ይችላል የሚልም ስጋት አላቸዉን። ይህንንም ሲገልፁ
«አብዛኛዉቹ ህመምተኞች ሴቶች ሲሆኑ በዚያ ላይ 10 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ህፃናት ናቸዉ። የህፃናት ሀኪሞችና የህፃናት መብቶች ተሟጋቾችም በጣም ጥቂት ህፃናት ብቻ ህክምና ማግኘታቸዉን ስለሚያዉቁ ሁኔታዉ አሳስቧቸዋል። መረጃዉንም ብናየዉ ቢያንስ 50,000 የሚሆኑ ህፃናት ይህ መድሃኒት ያስፈልጋቸዋል። ሆኖም 10,000 የሚሆኑት ብቻ ናቸዉ ህክምና ማግኘት የቻሉት።»
ኬፕ ታዉን ዉስጥ በተመሳሳይ ዘመቻ የተጠመደ Treatment Action የተሰኘዉ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት እንደሚለዉ ከሆነ ደግሞ መድሃኒቱን ለማቅረብ እንደሚወራዉ ችግሩ ገንዘብ አይደለም።
ባለፈዉ ዓመት ሰኔ ወር የዓለም የጤና ድርጅት ሶስት በአምስት በተሰኘዉ መርሃ ግብር መሰረት ደቡብ አፍሪካን እስከ መጪዉ የፈረንጆቹ 2006ዓ.ም. ድረስ ለዚሁ መድሃኒት የሚዉል አንድ ቢሊዮን ዶላር በጀት እንድትመድብ አዟት ነበር።
ሶስት በአምስት የተሰኘዉ መርሃ ግብር የተጀመረዉ በ2003ዓ.ም በዓለም የጤና ድርጅትና በተባበሩት መንግስታት የኤች አይቪ ኤድስ መርሃ ግብር ጥምረት ነዉ።
ዓላማዉም 3 ሚሊዮን የሚደርሱ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸዉ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ወገኖች እስካለፈዉ የፈረንጆቹ ዓመት ድረስ መድሃኒቱን ማግኘት እንዲችሉ ማድረግ ነበር።
የTreatment Action ኑ ዛኪር አችማት ችግሩ ያለዉ በሁሉ ቦታ መሆኑን ነዉ ያዩት
«በደቡብ አፍሪካ ያለብን ዋነኛዉ ችግር HIV ቫይረስ AIDS እንደሚያስከትል የማያምን ፕሬዝደንት ነዉ ያለን። በዚያም ላይ ከአቅም በላይ እንዲሰሩ እያደግን ለነርሶችና ለዶክተሮቻችን የሚከፈላቸዉ ደሞዝ አነስተኛ ነዉ። እና የዑጋንዳንና የዛምቢያን ነርሶች እንወስዳለን የእኛን ደግሞ ብሪታንያ ትወስዳለች።»
በማለትም የችግሩን ዉስብስብነትና ዘርፈ ብዙነት ለማሳየት ይሞክራሉ።
ፕሬዝደንት ታቦ ምቤኪን ኤች አይቪ ቫይረስ ኤድስን ማስከተሉን በመጠራጠራቸዉ ለመድሃኒቱ በነፃም ሆነ እንደልብ መገኘት በሚለፉትና በሽታዉን በቁጥጥር ስር ለማድረግ በሚጥሩ ወገኖች ዘንድ የለኮሱት እሳት ቀላል አይደለም።
የኤች አይቪ ቫይረስ ምርመራ በሚደረግበት ኩባንያ ዉስጥ የሚሰሩት ኪም ቴቨርሻምም ተመሳሳይ ነዉ ሃሳባቸዉ
«ገንዘብም ሆነ መድሃኒቱ አለ። ለህዝቡ የሚደረዉ አገልግሎትም ቢሆን ከማዝገሙ በቀር ጥሩ ነዉ። ችግሩ እርዳታ አድራጊዎቹና ድጋፍ መስጠት የሚገባቸዉ በአካል ተገኝተዉ ተገቢዉን ለማድረግ አለመቻላቸዉ ነዉ።»
የመንግስት ድጋፍ በተለየዉ የህክምና እርዳታ ሳቢያም በርካታ የበሽታዉ ሰለባ የሆኑ ደቡብ አፍሪካዉያን ተገቢ ህክምና አያገኙም።
በስፋት የታወቀዉ d4t የተሰኘዉ መድሃኒት ለአንድ ወር 65ዶላር ይጠይቃል። ይህ ደግሞ ግማሽ የሚሆነዉ ህዝብ ከድህነት ወለል በታች ለሚገኝባት ደቡብ አፍሪካ ዜጎች የሚሞከር አይደለም።
በሽታዉ መድሃኒቱን የመቋቋም ባህሪ ሲያሳይ ደግሞ የሚወሰደዉ መድሃኒት ዓይነቱ ስለሚለወጥ ዋጋዉም አብሮ ይለወጣል ይጨምራል።
ይህ ደግሞ በአብዛኛዉ አቅም የሌላቸዉ ለከፋ የጤና ቀዉስ ብሎም ለህፈተ ህይወት የሚዳረጉበት አጋጣሚ ይሆናል።