ደቡብ አፍሪቃ የኤ ኤን ሲ ጉባዔና ዙማ | አፍሪቃ | DW | 16.12.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ደቡብ አፍሪቃ የኤ ኤን ሲ ጉባዔና ዙማ

በደቡብ አፍሪቃ ታህሳስ ሰባት 2005 ዓም 53 ኛውን እና አምስት ቀናት የሚቆይ ሀገር አቀፍ ጉባዔ በማንጋውንግ ከተማ በሚያካሂደው የገዢው ፓርቲ የአፍሪቃውያን ብሔረተኞች ኮንግረስ - ኤ ኤን ሲ አባላት መደዳ በወቅቱ ትልቅ የሀሳብ ልዩነት ይታያል።

አንዳንዶች የታዋቂው ደቡብ አፍሪቃዊ ፀረ አፓርታይድ ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ ፓርቲ አባላት በፓርቲው መሪ እና በሀገሪቱ ፕሬዚደንት ጄኮብ ዙማ አንፃር ተቃውሞአቸውን በይፋ ሲናገሩ ይሰማል። ፕሬዚደንቱ ከጥቂት ወራት በፊት የማዕድን ሰራተኞች ያካሄዱትን ኃይል የታከለበት እና የሰው ሕይወት የጠፋበትን፡ ቆየት ብሎም ወደ ፊናንሱ ዘርፍ እና ወደ የወይን ጠጅ ኢንዱስትሪ የተስፋፋውን የስራ ማቆም አድማ ለማብቃት በተደረገው ጥረት ወቅት የተጫወቱት ሚና ከብዙዎች ነቀፌታ አሰንዝሮባቸዋል። ኤ ኤን ሲ ትኩረቱን በውስጡ በተፈጠረው ንትርክ ላይ ባደረገበት ባለፉት ጊዚያት፡ ደቡብ አፍሪቃ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፎካካሪነትዋን እያጣች በመሄድ ላይ ትገኛለች።

የዶይቸ ቬለው ሉድገር ሻዶምስኪ እንደታዘበው፡ ዘመናይ በምትባለው ደቡብ አፍሪቃም እጅግ ወሳኝ የሆነ ጉዳይ ሲያጋጥም ብዙዎች ወደ ባህላዊው አሰራር በመመለስ የቀድሞዎቹ አባቶች መንፈሥ በረከት እንዲያወርዱላቸው ይማፀናሉ። በዚሁ መሠረትም፡ ፕሬዚደንት ጄኮብ ዙማ በባህላዊው ሥነ ሥርዓት ደንብ የቀድሞዎቹ አባቶች መንፈሥ በነገው ዕለት በሚጀመረው የኤ ኤን ሲ ጉባዔ ላይ የፓርቲው መሪ ሆነው ድጋሚ እንዲመረጡ ይረዱዋቸው ዘንድ ባለፈው ኅዳር ወር አጋማሽ 12 ሰንጋ ጥለዋል። የቀድሞዎቹ አባቶች መንፈሥ ይረዳቸው እንደሆን ነው እንጂ የራሳቸው ፓርቲ እና የደቡብ አፍሪቃ መራጭ ሕዝብ ከዙሉ ጎሣ የሚወለዱትን ፕሬዚደንት ዙማን እንደማይመርጡ ነው ያስታወቁት።

ፕሬዚደንት ዙማን ከፓርቲ መሪነት ለማንሳት የሚፈልጉት ወገኖች « ከዙማ የማይሻል የለም » የሚል መፈክር ይዘው የተነሱት ወገኖች በዙማ አንፃር ጠንካራ ህብረት ፈጥረዋል። ቶክዮ ሼህ ቫለንን የመሰሉ በኤ ኤን ሲ ውስጥ ስም ያተረፉ ግለሰቦች ብቻ ሳይሆኑ ተራው አባልም ሳይቀር ዙማ ከፓርቲው መሪነት እንዲነሱ ጠይቆዋል። የሞራል አባት የሚባሉት የኖቤል ሰላም ተሸላሚ እና የቀድሞው አቡነ ዴመንድ ቱቱ እንኳን ለኤ ኤን ሲ እና ለመንግሥቱ ውድቀት እንደሚፀልዩ ተናግረዋል። ሁሉም ፕሬዚደንት ዙማ በወቅቱ ለሚታዩት፡ ማለትም፡ እየደከመ የሄደውን እና ባለፉት ወራት የስራ ማቆም አድማ በተጨማሪ የተጎዳውን የሀገሪቱን ኤኮኖሚ፡ ሥር የሰደደውን ስራ አጥነት እና ሙስናን ለመሳሰሉት ችግሮች መፍትሔ ለማግኘት በቂ ጥረት አላደረጉም በሚል ይወቅሱዋቸዋል።

ከመጀመሪያዎቹ የፀረ አፓርታድ ታጋዮች አንዷ የነበረችው የሴቶች መብት ተሟጋች ሮዳ ካዳሊ ዛሬ ጠንካራዋ ተቃውሞ የምታሰማ አምደኟ ናት። የፓርቲ አባልነት መታወቂያዋን ከመለሰች ብዙ ጊዜ የሆናት ካዳሊ አሳዛኝ ያለችውን የፓርቲ ጉባዔ በቅርብ ላለመከታተል ስትል በጉባዔው ቀናት ወደ ዩኤስ አሜሪካ እንደምትጓዝ ገልጻለች። የዙማና የተከታዮቻቸው አሰራርን በጥብቅ ትነቅፋለች።

« እርስ በርስ በጀመሩት የስልጣን ሽኩቻ ሀገሪቱ ወደፊት ለመራመድ የምታደርገውን ትረት አሰተጓጉለዋል። እነሱን በይበልጥ ያሳሰባቸው ኤኮኖሚውን መቆጣጠሩ እንጂ የሀገሪቱ አመራር አይደለም። የዘር አድልዎው አመራር ከተገረሰሰ በኋላ የተሰማው ብዙውን የሀገሪቱን ጥቁር ሕዝብ በኤኮኖሚ ለማጠናከር የተሰኘው መፈክርን እኔ በኤኮኖሚው ራስን ማበልፀግ፡ ማለትም፡ እንዴት ነው ፈጥኜ ብዙ ገንዘብ የማካብተው ብዬ ነው የምተረጉመው። ኤ ኤን ሲ ኔልሰን ማንዴላ ለሀገሪቱ የቀየሱትን መንገድ የመከተል አቅም የለውም። እና አሁን ምክትል ኻሌማ ፕሬዚደንት ሞትላንቴ ወይም ጄኮብ ዙማ ለፓርቲው መሪነት ቢመረጡ አንዳቸውም ለፓርቲው መሪነት አይበቁም ባይ ነኝ። »

ኤ ኤን ሲን የገጠመው የፖለቲካ ውዝግብ እና ያለፉት ወራት ኃይል የታከለበት የስራ ማቆም አድማ የባለሀብቶች መስሕብ የነበረችውን ደቡብ አፍሪቃን አብዝቶ እየጎዳ መሆኑን በምሕፃሩ አይ ኤስ ኤስ በመባል የሚታወቀው በፕሪቶርያ የሚገኘው ዓለም አቀፉ የፀጥታ ተቋም ተንታኝ፡ ጋሬት ኒውሀምን የመሳሰሉ ታዛቢዎች በስጋት መከታተል ይዘዋል።

« አስተማማኝ ባልሆነው የፖለቲካ ሁኔታ የተነሳ ሁለት የሀገራት የመበደር አቅምን የሚለኩ ድርጅቶች የደቡብ አፍሪቃን አቅም ዝቅ አድርገውታል። የሀገራችን የዋጋ ግሽበት እጅግ ከፍ ብሎዋል። የማዕድኑ ዘርፋችንም ከተተነበየው ያነሰ የውጭ ምንዛሪ ገቢን ነው ያስገኘልን። ለዚህም ተጠያቂው፡ ሀገሪቱን የሚመሩት ፕሬዚደንት ዙማ እና ሚንስትሮቻቸው ለሀገሪቱ ችግሮች መፍትሔ የሚገኝበትን መንገድ ከመጠቆም ይልቅ በሥልጣኑ ሽኩቻ እና የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቂያ በሥልጣን መቆየት በሚችሉበት ዘዴ ላይ በማትኮራቸው ነው። »

ከትቂት ጊዜ በፊት የተባረሩት የኤ ኤን ሲ የወጣቶች ድርጅት መሪ ጁልየስ ማሌማ ውድቀት ለዙማ እያሉ በአደባባይ መፈክር ማሰማታቸው ሁኔታዎች ምን ያህል አሳሳቢ መሆኑን አመላክቶዋል። ከዚህ የባሰው ግን መሪዎቹ ለምሳሌ የመሬት እና የማዕድናት ባለቤትነት ጥያቄ፡ ተፎካካሪ የኢንዱስትሪ ዘርፍ መፍጠር፡ ምርት ማሳደግ እና የሙያ ስልጠናን ደረጃ ከፍ ማድረግን ለተሰኙት ጉዳዮች ባስቸኳይ መፍትሔ ማግኘት አለመቻላቸው ነው። በድሆቹና በሀብታሞቹ መካከል ልዩነት እየሰፋ በመሄድ፡ ከደቡብ አፍሪቃ ሀምሣ ሚልዮን ነዋሪዎች መካከል ሁለት ሦስተኛው በአማካይ በቀን ከአንድ ዶላር ባነሰ ገቢ ነው የሚኖረው። በዚህም የተነሳ የደቡብ አፍሪቃ መንግሥት ይህን ሁኔታ ለመቀየር በተጨባጭ አንድ ርምጃ እንዲወስድ የጀርመናውያኑ ምጣኔ ሀብት በደቡባዊ አፍሪቃ ያነቃቃው ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንድሬያስ ቬንስል አሳስበዋል።

« ይህ በርእግጥ ያሳስበናል፤ ለኛ የጀርመናውያኑ ኤኮኖሚ የትኛው ግለሰብ የትኟውን ቦታ ያዘ ሳይሆን በደቡብ አፍሪቃ ጠቃሚ ፖሊሲ የሚንቀሳቀስበት ድርጊት ነው ዋነኛው ጉዳይ። ደቡብ አፍሪቃ በኤኮኖሚው ፖሊሲ ላይ የትኛውን መሥመር እንደምትከተል በግልጽ ማወቅ እንፈልጋለን።

በግል ይዞታ ያሉ በተለያዩ ዘርፎች የሚገኙ ተቋማት ወደ መንግሥት እጅ ይገባሉ በሚል በፓርቲው የሚሰማው ውይይት መንግሥት የሚከተለው ፖሊሲ እንደማይሆን ግልጽ ሊሆን ይገባል። እርግጥ፡ የኤ ኤን ሲ የግራ ክንፍ የሆኑት የሙያ ማህበራት እና ኮሚንስቶች፡ የወጣቶች ድርጅት ይህን ዓይነት ጥያቄ ያቀርባሉ፤ ይሁንና፡ ኤ ኤን ሲ ይህ እንደማይሆን ግልጹን መልዕክት የሚያስተላልፍበት ድርጊት የባለሀብቶች መስሕብ እና የኤኮኖሚ አጋር ለሆነችው ደቡብ አፍሪቃ ጠቃሚ ይሆናል። ምክንያቱም፡ ደቡብ አፍሪቃ ከላቲን አሜሪካ እና ከእሥያ ገበያዎች ጋ ነው የምትፎካከረውና። »

ልክ እንደብዙዎቹ ደቡብ አፍሪቃውያን ቬንስልም ከዙማ ጎን የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ሚና ሊይዙ ይችሉ ይሆናል የሚባሉት የተከበሩት ባለተቋም ሲሪል ራማፎዛ በዚሁ ሂደት ላይ ጠንካራ ሚና እንዲጫወቱ ይፈልጋሉ።

አርያም ተክሌ

መስፍን መኮንን

Audios and videos on the topic

 • ቀን 16.12.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/1737R
 • ቀን 16.12.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/1737R