ደቡብ አፍሪቃ የቅይጦች ሐገር፣የተቃርኖ ምድር 25 ዓመት | አፍሪቃ | DW | 29.04.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ደቡብ አፍሪቃ የቅይጦች ሐገር፣የተቃርኖ ምድር 25 ዓመት

በ1788 የያኔዎቹ የዳች (ኔዘርላንድስ) ቅኝ ገዢዎች የጥቁሮችን፣የመንቀሳቀስ፣በፖለቲካ የመሳተፍ፣ በተፈጥሮ ሐብታቸዉ  የማዘዝ መብቱን የሚያግድ፣ የነጭ ሠፋሪዎችን የበላይነት የሚደነግግ ሕግ ካፀደቁበት ጊዜ ጀምሮ የደቡብ አፍሪቃ አንጡራ ሕዝብ ጥቁር በመሆኑ ብቻ ያልተጨቆነ፣ ያልተበደለ፣ያልተሰቃየበት ጊዜ በርግጥ አልነበረም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:50

ደቡብ አፍሪቃ ከአፓርታይድ በኋላ

 

ወጣት ግን እመ ጫት ናት።ሴት ልጅ ከተገላገለች 18 ቀንኗ። ታንዴካ ሲዳያ።የጆሐንስ በርግ ነዋሪ ናት።«የዚያ ቀኑ ሁነት እንዲያልፋት አልፈለገችም።» ናሽናል ጂኦግራፊ እንደፃፈዉ።ሕፃኗን ለአያትዋ ሰጥታ ሔደች።ወደ ምርጫ ጣቢያ።«ያንን ዕድል ማጣት አይፈልጉም ነበር» ትላለች የያኔዋ የ18 ቀን ሕፃን፣ ሲቦኒሲሌ ታሓባላላ «ለአፓርታይድ መወገድ አስተዋፅኦ ማድረግ ይፈልጉ ነበር.» ቀጠለች ታሓባላላ።እናትዬዋ መረጠች።እቤት ስትመለስ ተራዉ የአያትዋ ነበር።እሳቸዉም ድምፅ ሰጡ።ሚያዚያ 27 1994 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ።) ቅዳሜ 25 ዓመቱ።ደቡብ ቀፍሪቃ።ነፃ ሆነች።የደቡብ አፍሪቃ ያለፈና ያሁን እዉነት ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ።

 ታሓባላላ መሐንዲስ ናት።ዘንድሮ-የያኔ እናትዋን አክላለች።25 ዓመቷ።ያ ለእናትና አያትዋ ወይም «ለነሱ» ያለችዉ ልዩ ቀን ለሷም፣ለነሱም፣ ለአብዛኛዉ ደብብ አፍሪቃዊ የድል ቀን ነዉ።የዘር መድሎ ሥርዓት የተገረሰሰበት።የነፃነት ዕለት።

«የነፃነት ቀን ለኔ በደቡብ አፍሪቃ የፖለቲካ ቀን መቁጠሪያ ልዩ ቀን ነዉ።ከኛ በፊት የነበሩት ወገኖቻችን ያስገኙትን ድል የምናከብርበት

Südafrika Land und Leute Kapstadt Hafen Denkmal Desmond Tutu

ዕለት ነዉ።ማክበርም አለብን።»

ይላል እሱ።እሳቸዉ ግን ከሌሎች ጋር ሆነዉ ቅዳሜ ለተቃዉሞ አደባባይ ወጥተዋል።

«የለም የነፃነት ቀን ብሎ ነገር የለም።ነፃነት የሚባል የለም።አሁን በዘር መድሎ ዉስጥ ነን።እነሱ (ፖሊሶቹ) የተሻለ ጥቅም አላቸዉ።ፖሊሶች የተሻለ ነገር አላቸዉ።እኛ ላይ የሚተኩሱበት ጠመንጃ አላቸዉ።»

ደቡብ አፍሪቃ የቅይጦች ሐገር፣ የተቃርኖ እዉነት ምድር።ከዚሕ ለመድረስ ግን ብዙ መጓዝ፤ መሐንዲስ ታሓባላላ «እነሱ» ያለቻቸዉ እናት፣አያት፣ቅድመ አያቶችዋ እንደ እንስሳ በተከለለ ሥፍራ መታገት፣ መረገጥ፣መጋዝ፣መደብደብ፣ መታሰር ሲከፋም መገደል ነበረባቸዉ።«መሪር» ይለዋል-እሱ።

«እናዉቃለን።እንደ ሐገር እዚሕ ለመድረስ በጣም፣በጣም ረጅም መንገድ መጓዝ ነበረብን።በጣም መራር ጊዜ ማሳለፍ ነበረብን።ስለዚሕ ቀለም ዘር ጎሳ፣ መደብ ሳይለየን ሁላችንም ልናከብረዉ ይገባል።»ጉዞዉ ሩቅ፣ ጊዜዉ ረጅም ነበር።ሶስት ምዕተ-ዓመት ግድም። በ1788 የያኔዎቹ የዳች (ኔዘርላንድስ) ቅኝ ገዢዎች የጥቁሮችን፣የመንቀሳቀስ፣በፖለቲካ የመሳተፍ፣ በተፈጥሮ ሐብታቸዉ የማዘዝ መብቱን የሚያግድ፣

የነጭ ሠፋሪዎችን የበላይነት የሚደነግግ ሕግ ካፀደቁበት ጊዜ ጀምሮ የደቡብ አፍሪቃ አንጡራ ሕዝብ ጥቁር በመሆኑ ብቻ ያልተጨቆነ፣ ያልተበደለ፣ያልተሰቃየበት ጊዜ በርግጥ አልነበረም።

በ1948 ሥልጣን የያዘዉ የብሔራዊ ፓርቲ መሪና የደቡብ አፍሪቃ ጠቅላይ ሚንስር ዶክተር ዳንኤል ፍራንሷ ማላን የደችና-ብሪታንያ አያት፣አባቶቻቸዉ የሚያራምዱትን የዘር መድሎ ሥርዓትን የመንግስታቸዉ መርሕ፣ የጥቁር-ነጭ የእስያ-ክልሶች ቅይጥ ሐገር ሕግም አደረጉት።ከደቡብ አፍሪቃ ሕዝብ 4 በመቶ የማይሞሉት ነጮች የሐገሪቱ ሐብት፣ሥልጣንና ኃይል አዛዥ ናዛዥ ሆኑ።

ምዕራባዉያን መንግስታት በገፍ የሚረዷቸዉ ነጭ ዘረኞች በጥቁሮች ላይ የሚያደርሱትን ግፍ ለማስቆም የደቡብ አፍሪቃ ጥቁሮች በፖለቲካ-ዲፕሎማሲዉ መስክ ያልታገሉበት ዘመን የለም።በተለይ በ1912 ጀምሮ የደቡብ አፍሪቃ አፍሪቃዉያን ብሔራዊ ምክር ቤት (ANC) በሚል ምሕፃረ ቃል የተመሠረተዉ የፖለቲካ ፓርቲ ደቡብ አፍሪቃ የሁሉም ደቡብ አፍሪቃዉያን ሐገር እንድትሆን በተደረጀ መልኩ ከታገሉ የፖለቲካ ማሕበራት ግንባር ቀደሙ ነዉ።

የዶክተር ማላን መንግስት በ1948 ዘርመድሎን የመንግስቱ ግልፅ መርሕና ሕግ ማድረጉን ANC አጥብቆ ተቃዉሞም ነበር።የፓርቲዉ ፕሬዝደንት ቺፍ አልበርት ሙምቢ ሉትሊ በ1954 የሰጡት ማስጠንቀቂያ ደግሞ እስከዚያ ጊዜ ድረስ 6 ዓመት የሆነዉ ሰላማዊ፣ፖለቲካዊ ተቃዉሞ ሰሚ ማጣቱን አረጋጋጭ፣ANCም አዲስ የትግል ሥልት ለመቀየስ ዳርዳር ማለቱን ጠቋሚ ነበር።

«የአናሳዎቹ የነጭ አገዛዝ፣ ነጭ ያልሆኑ የሐገሪቱ ተወላጆች በሐገሪቱ አስተዳደር ዉስጥ እንዲሳተፉ (የሚቀርብለትን ማናቸዉንም ጥያቄ) ለመቀበል ዝግጁ አይመስለኝም።ብዙ ነገር እናደርግ ይሆናል፣ ይሁንና አሁን በግሌ የማምነዉ የአፍሪቃ ሕዝብን ለመብቱ እንዲታገል ማደራጀት፣ የፖለቲካ ንቃተ ሕሊናቸዉን ማሳደግና ጤናማ ግፊት እንዲያደርጉ ማነሳሳት ያለብን ይመስለኛል።»

ቺፍ አልበርት ሉቱሊ ያሉትን ባሉ በአራተኛ ዓመቱ የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ሥlልጣን ያዩዙት ሔንድሪክ ፈርቮርድ ግን የዘር መድሎ ሥርዓታቸዉን አዲስ ቀለም ቀብተዉ፣የመንግስታቸዉ የፀጥታ ኃይላት ነጭ ባልሆኑ የሐገሪቱ ዜጎች ላይ የሚፈፅሙትን ግፍ በደል አጠናከሩት።

«ከአፍሪካነር (ቋንቋ) በተወሰደዉ አፓርታይድ በሚለዉ ስም የሚጠራዉ መርሕ የተዛባ ትርጓሜ የተሰጠዉ ይመስለኛል።በቀላሉና በተሻለ መንገድ የሚገልፀዉ በኛ በሰዎች መካከል ያለዉን ልዩነት በመቀበል ጥሩ ጉርብትና መመስረት የሚለዉ ነዉ።ልዩነቱን መቀበል አለብን።ልዩነቱን ከተቀብልን አብሮ መኖርና

መረዳዳት የሚቻለዉ እንደ ጥሩ ጎረቤቶች ስንኖር ነዉ።»

የነፈርቮርድ ግፍ-ጭካኔ ሲበዛ የነ አልበርት ሉቱሊ ትግልም እየተጠነከረ፣ እነ ዋልተር ሲሲሉን፣ ኦሊበር ታንቦን፣ ኔልሰን ማንዴላን ከፊት እያሰለፈ ጥቁር ክልስን ሕዝብ ለመራር-እረጅሙ ትንቅንቅ አነቃነቀ።ብዙዎች ተገድለዋል።ነብስ ያላወቁ ተማሪዎች ተረሽነዋል።ሚሊዮኖች በግፍ ተግዘዋል።ተሰደዋል።እነ ኔልሰን ማንዴላ፣ እነ ሲሲሉ ሳይቀሩ የነፃነት ትግሉ መሪዎች በግፍ ታስረዋል።

የጥቁሮቹ አልገዛም ባይነት ሲበረታ የዘረኛ ነጮችን መንግስት የሚደግፉና የሚያስታጥቁት የምዕራብ አዉሮጳና የዩናይትድ ስቴትስ መንግስታት ለነፃነት የሚፋለሙ የፖለቲካ ማሕበራትንና ማንዴላን የመሳሰሉ ታጋዮችን በአሸባሪነት ፈርጀዉ ይወነጅሉ ገቡ።

ትግሉ ግን አልቆመም።እንዲያዉም ከኢትዮጵያ እስከ ሊቢያ፣ ከጋና እስከ ፍልስጤም የሚገኙ የአፍሪቃና የእስያ  ሐገራትና ድርጅቶች የደብ አፍሪቃ የግፍ ሠለቦችን በግልፅ ሲደግፉ የአዉሮጳና የአሜሪካ ሕዝብም የየመንግስቱን አቋም እንዲያጤን አስገደደዉ።

እራሳቸዉን ከአዉሮጳ ቅኝ ገዢዎች ነፃ ያወጡት የአፍሪቃ ሐገራት በአፊሪቃ አንድነት ድርጅት እየተሰባሰቡ ከኳስ ሜዳ እስከ ዲፕሎማሲዉ አደባባይ፣ ከማዕቀብ እስከ ሙዚቃዉ ድግስ ባንድ ሲያድሙ፣ የትግሉ ዉጤት ነጭ ገዢዎችን እንዳይጠራርግ፣ ምዕራባዉያን መንግስታት ዘዴ ያሉትን ግፊት በፕሪቶሪያ ገዢዎች ላይ ለማድረግ ተገደዱ።ቀዝቃዛዉም ጦርነት ለፍፃሜዉ ያዘግም ያዘ።

 በዚሕ መሐል ከነጮቹ ገዢዎች እስካሁን የመጨረሻዉ የደቡብ አፍሪቃን የፕሬዝደንትነት ሥልጣን ያዙ።1989።ፍሬድሪክ ቪለም ደክላርክ።ባመቱ ዘረኝነት «በቃን» አሉ-እይቀጥልልም።

«በደቡብ አፍሪቃ ብሔራዊ ኮንግረስ፣በመላዉ አፍሪቃዉያን ኮንግረስ፣በደቡብ አፍሪቃ ኮሚንስት ፓርቲና በሌሎች ተባባሪ ድርጅቶች ላይ የተጣለዉ እግድ ተነስቷል።ከእነዚሕ ድርጅቶች የአንዱ አባል በመሆናቸዉ ወይም በየድርጅቶቹ ላይ በተጣለዉ እግድ ምክንያት ሌላ ጥፋት አድርሰዉ የተፈረደባቸዉ ሰዎች ይለቀቃሉ።አመፅ ዑደቱን የምንገታበት፣ ሰላምና እርቅ የምናወርድበት ጊዜ አሁን ነዉ።

ድምፅ አልባዉ አብዛኛ ሕዝብ ይሕን ለማግኘት ዋትቷል።ወጣቱ ሊያገኝ ይገባዋል።»

ማንዴላም ተፈቱ።በሰወስተኛ ዓመቱ የያኔዋ ወጣት እመጫት የሚገባትን አገኘች።ነፃነት።መረጠችም።ማንዴላን።ይሁንና ታንዴካ ሲዳያም ሆነች ሌላዉ ጥቁር ደቡብ አፍሪቃዊ ከፖለቲካ ነፃነት ባለፍ በምጣኔ ሐብቱ የሚፈልጉትን ማግኘታቸዉ ግን ዛሬም አጠያያቂ ነዉ።

                                    

«እንደሚመስለኝ ትልቁ ጥያቄ የድሕነቱ ጉዳይ ነዉ።ባላቸዉና በሌላቸዉ መካከል ያለዉ ክፍተት ሰፊ ነዉ።አብዛኛዉን የደቡብ አፍሪቃን ምጣኔ ሐብት የሚቆጣጠሩት ከሐገሪቱ ሕዝብ ሃያ በመቶ የሚኖኑት ናቸዉ።ከ79ኝ ከመቶ የሚበልጠዉ አብዛኛዉ ሕዝብ የሚኖረዉ ከድሕነት ጠገግ በታች ነዉ።»

ይላሉ የፖለቲካ ተንታኝ ኒክሰን ካቴንምቦ።በነፃነት ማግስት የፖለቲካዉን ሥልጣን ከያዙት የቀድሞ የነፃነት ታጋዮች ገሚሱ ቃል፣ኃላፊነት፣ አደራቸዉን ዘንግተዉ አዳዲስ ቱጃሮች መሆናቸዉ ነዉ-የክፋቱ ምሬት።

ነጋሽ መሐመድ 

እሸቴ በቀለ

Audios and videos on the topic