ደቡብ አፍሪቃ የስለላ ቅሌት | አፍሪቃ | DW | 26.02.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ደቡብ አፍሪቃ የስለላ ቅሌት

በአዲስ አበባ የደቡብ አፍሪቃ ኤምባሲ ዲፕሎማቶች፤ ሠላዮች፤ ከኢትዮጵያ የመረጃ ሰዎች ጋር ይራኮቱ-ገቡ።ቢያንስ አራት ጠባቂዎች-እሕል ዉሐ ሳይቀምሱ የአፍሪቃ ሕብረት ፅሕፈት ቤትን ሙጥኝ አንዳሉ አራት ቀን ዉለዉ አደሩ።ሴትዮዋም ከግድያ ሴራዉ አመለጡ።

ከደቡብ አፍሪቃ አፍተልኮ የወጣዉ የስለላ ሠነድ ሐገሪቱ የሰላዮችና የአፀፋ ሠላዮች መናኸሪያ መሆንዋን አጋልጧል።የቀጠሩ አልጀዚራ ቴሌቪዥን ጣቢያና ዘጋርዲያን የተሰኘዉ የብሪታንያዉ ጋዜጣ በተከታታይ ያሰራጩና ያተሙት ሰነድ በደቡብ አፍሪቃ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የስለላ ሚስጥርን ያጋለጠ ነዉ።አፍትልኮ የወጣዉ ሠነድ እንደሚያመለክተዉ ደቡብ አፍሪቃ፤ የዩናይትድ ስቴትሱ የስለላ ድርጅት CIA፤ የብሪታንያዉ M16፤ የእስራኤሉ ሞሳድ እና የሌሎችም የበርካታ ሐገራት የሥለላ ድርጅቶች መጠላለፊያ ነች።ነጋሽ መሐመድ አጭር ዘገባ አለዉ።

ደቡብ አፍሪቃዊቱ ዲፕሎማት ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ የአፍሪቃ ሕብረት ኮሚሽንን የሊቀመንበርነት ሥልጣን ከተረከቡ ሳምታቸዉ ነዉ።ጥቅምት-22 2012 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ።) የደቡብ አፍሪቃዉ የሥለላ ድርጅት (SSA) አዲስ አበባ ለሚገኘዉ የደቡብ አፍሪቃ ኤምባሲ-ያስተላለፈዉ መልዕክት ከወትሮዉ ጠንከር ጠጠር ያለ ነበር።«ሴትዮዋ»ን ለመግደል ያሴሩ አሉ-ይላል-የመልዕክቱ ጥቅል ጭብጥ።

በአዲስ አበባ የደቡብ አፍሪቃ ኤምባሲ ዲፕሎማቶች፤ ሠላዮች፤ ከኢትዮጵያ የመረጃ ሰዎች ጋር ይራኮቱ-ገቡ።ቢያንስ አራት ጠባቂዎች-እሕል ዉሐ ሳይቀምሱ የአፍሪቃ ሕብረት ፅሕፈት ቤትን ሙጥኝ አንዳሉ አራት ቀን ዉለዉ አደሩ።ሴትዮዋም ከግድያ ሴራዉ አመለጡ።ሊገድላቸዉ ያሴሬዉ ወገን ማንነት፤አላማ፤ ፍላጎቱ ግልፅ አይደለም።አልጀዚራ በተከታታይ የዘረገፈዉ የሚስጥር ሰነድ እንደሚያመለክተዉ በዙማ ላይ የተቃጣዉ የግድያ ሴራ አንዷ እና ትንሿ ናት።

ፕሪቶሪያ-ላይ የሚቀለጣጠፈዉ ሥለላ ከአዲስ አበባ፤ ዋሽግተን፤ ለንደን፤ ቴል አቪቭ፤ ካይሮ፤ ቤጂንግ፤ ሞስኮ፤ ሶል እያለ የሰባ ሥምንት ሐገራት ሰላይ ተዘፍቆበታል።ለመረጃ ነፃነት የሚታገለዉና የማወቅ መብት የተሰኘዉ የደቡብ አፍሪቃ ድርጅት ሐላፊ መሬይ ሐንተር የቆሻሹ ሠላዮች ቁሻሻ ምግባር ይሉታል።

«ደቡብ አፍሪቃ እራሳቸዉ የሚያጭበረብሩ የዉጪ ሠላዮች የቆሸሸ ዉልና ስምምነት የሚያደርጉባት ሐገር ሆናለች።እንደሚመስለኝ ከዚሕ ጠቃሚዉ ነገር የዓለምን መጥፎ (ገፅታ) ማየት መቻላችን ነዉ»

አፍትልኮ ከወጣዉ ሰነድ አንዱ የዩናይትድ ስቴትሱ የስላላ ድርጅት CIA የፍልስጤሙን ደፈጣ ተዋጊ ድርጅት ሐማስን ለማግኘት በደቡብ አፍሪቃ በኩል መረማመዱን ይዘከዝካል።የቀድሞዉ የእስራኤል የስለላ ድርጅት ሐላፊ ሚር ዳጋን፤ በጋዛዉ ጦርነት ተፈፅሟል የተባለዉን የጦር ወንጀል ይመረምሩ የነበሩትን የ ደቡብ አፍሪቃዊ ዳኛ የሪቻርድ ጎልድስቶንን ሥራ ለማደናቀፍ-የወጠኑት ሴራም ተጋልጧል።

አንድ እንጨምር የእስራኤል ሸቀጦች ደቡብ አፍሪቃ ገበያ ላይ እንዳይሸጡ ዘመቻ ብጤ ሲጀመር የደቡብ አፍሪቃዉ የገንዘብ ሚንስትር ፕራቪን ጎርድሐም አጭር ማስታወሻ ይደርሳቸዋል።የላኪዉ ሥምና አድራሻ አልተጠቀሰም።መልዕክቱ ግን ዘመቻዉ ካልቆመ የደቡብ አፍሪቃ የገንዘብ ተቋማት የሳይበር መረጃዎች ይደመሰሳሉ የሚል ነበር።

አልጀዚራ ሥም፤ አድራሻ፤ የሥልክ ቁጥራቸዉ ሳይቀር እንዳለዉ ያስታወቃቸዉ ከአንድ መቶ አርባ የሚበልጡ የዉጪ ሠላዮች የደበቡብ አፍሪቃን የመንግሥት መስሪያ ቤቶች፤ ሚንስትሮች፤ ሌላዉ ቀርቶ የፕሬዝዳንቱን ፅሕፈት ቤት ሚስጥር ሳይቀር እንዳሻቸዉ ሲያጮልጉ ነበር።

የደቡብ ኮሪያ የሥለላ ድርጅት፤ ግሪን ፒስ ሥለተባለዉ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በተለይም ሥለ ሐላፊዉ ሥለ ኩሚ ናይዶ አቋምና ማንነት የደቡብ አፍሪቃ የሥለላ ድርጅት መረጃ እንዲሰጠዉ የጠየቀበት ሚስጥርም ተጋልጧል።ደቡብ አፍሪቃዊዉ ኩሚ ናይዱ መንግሥት ሥለ ጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጣቸዉ ጠይቀዋል።

በሚያሳዝን ሁኔታ የደቡብ አፍሪቃ የሥለላ ድርጅት ባለሥልጣናት ሥለአፈተለከዉ ሰነድ ምንም አይነት ማስተባበያ አልሰጡም።ሁለት ነገሮችን አደርጋለሁ።የመጀመሪያዉ መንግሥት ሥለ ጉዳዩ መረጃ እንዲሰጠኝ መጠየቅ ነዉ።(ሥለኔ) ለቀረበላቸዉ ለጥያቄ ምንአይነት መልስ እንደሰጡ እንዲነግሩኝ እፈልጋለሁ።ሁለተኛዉ መወሰድ የሚገባዉን ሕጋዊ እርምጃ መዉስደ ነዉ።»

ዴሞክራቲክ አልያንስ የተኘዉ የሐገሪቱ መንግሥት ተቃዋሚ ፓርቲ መንግሥት ሥለ መረጃዉ እና አፈትልኮ ሥለወጣበት ሁኔታ ለምክር ቤቱ ማብራሪያ እንዲስጥ ግፊት እያደረገ ነዉ።ሚስጥራዊ ሥነድ ከጋዜጠኞች እጅ የገባበት መንግድ ሚስጥር ነዉ።

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለስ 

 

 

 

 

 

Audios and videos on the topic