ደቡብ አፍሪቃዊዉ የጃዝ አባት ሂዉ ማሴኬላ | ባህል | DW | 01.02.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

ደቡብ አፍሪቃዊዉ የጃዝ አባት ሂዉ ማሴኬላ

ሂዉ ማሴኬላ የደቡብ አፍሪቃ የጃዝ አባት ተብለዉ ነዉ የሚጠሩት። ሂዉ ማሴኬላ መድረክ ላይ ሙዚቃን መጫወት ብቻ ሳይሆን ታሪክንም ነዉ የሚናገሩት። ይህ አቀራረባቸዉ ነዉ ከሌሎች ሙዚቀኞች እና የሙዚቃ መሳርያ ተጫዋቾች ለየት የሚያደርጋቸዉ። ሂዉ ማሴኬላ በደቡብ አፍሪቃ በአፓርታይድ ዘመንም ብዙ የታገሉ ሰዉ ናቸዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 15:45

«ኢትዮጵያ ዉስጥ ሙዚቃን ለማቅረብ አቅደዉ ነበር።»

ታዋቂዉ የጃዝ ሙዚቃ አባትና በተለይ በትራምፔት ድንቅ አጨዋወታቸዉ የሚታወቁት ሄዉ ማሴኬላ የዛሬ ስድስት ወር ግድም በሞሮኮ የአፍሪቃ ሀገራትን የመልካም አስተዳደር ሁኔታን በሚያጠናዉ በሞ ኤብራሂም ዓመታዊ ስብሰባ መድረክ ላይ ያቀረቡትን ሙዚቃ ለደቡብ አፍሪቃዊዉ የጃዝ አባት ሂዉ ማሴኬላ የመጨረሻ መድረክ እንደሆነ ያወቀ አልነበረም። ባለፈዉ ሳምንት ረቡዕ ታዋቂዉ አፍሪቃዊ የጃዝ ሙዚቃ ተጫዋች ሂዉ ማሴኬላ በ78 ዓመታቸዉ በትዉልድ ከተማቸዉ ጆሃንስበርግ ደቡብ አፍሪቃ ዉስጥ ከዚህ ዓለም መለየታቸዉ በተሰማ ጊዜ የዓለም ብዙኃን መገናኛዎች የኃዘን መግለጫቸዉን አስተጋብተዋል፤ ሙዚቃቸዉንም በደማቅ ከፍ አድርገዉ ማሰማታቸዉን እንደቀጠሉ ነዉ። በድንገት ከዚህ ዓለም መሞታቸዉ የተሰማዉ ድንቅ የትራምፔት ተጫዋቹ የአፍሪቃ ጃዝ አባት ሂዉ ማሴኬላ  በትዉልድ ሃገራቸዉ በደቡብ አፍሪቃ አፓርታይድን ለመጣል ከፍተኛ ትግልን በማድረጋቸዉም ይታወቃሉ።

ሂዉ ማሴኬላ በጎርጎረሳዊዉ በ1960ዎቹ ከታዋቂዋ ደቡብ አፍሪቃዊት ከያኒ ከማርያ ማኬቫ ጋርም የትዳር ጓደኛ ነበሩ። ደቡብ አፍሪቃዊዉ የጃዝ ሙዚቃ አቀንቃኝ ሂዉ ማሴኬላ በኢትዮጵያዉያን ዘንድ ምን ያህል ይታወቃሉ? ይህ  ዝግጅታችን የደቡብ አፍሪቃዊዉን የጃዝ አባት የሕይወት ታሪክ እየቃኘን ከኢትዮጵያዉያን ጋር ያላቸዉን ተሞክሮ የሚያጫዉቱንን እንግዶች ጋብዘናል።

የአፍሪቃዉ የጃዝ ሙዚቃ አባት በተለይ ደግሞ በትራምፔት የሙዚቃ መሳርያ ድንቅ አጨዋወታቸዉ በዓለም ታዋቂነትና ተወዳጅነት ያተረፉት ደቡብ አፍሪቃዊዉ ከያኒ ሂዉ ማሴኬላ  ባለፈዉ ረቡዕ ከዚህ ዓለም መለየቱ የተሰማዉ ቤተሰቦቻቸዉ  በትዊተር ባወጡት መግለጫ ነበር። ማሴኬላ በወንዶች የዘር ፍሪ ማመንጫ ማለት በ«ፕሮቴስት» ካንሰር  ሕመም ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት እንደተለዩ ቤተሰቦቻቸዉ ባሰራጩት የትዊተር መልክት ጽፈዋል። በዚሁ  «በትዊተር የማኅበራዊ መገናኛ መድረክ ላይ ባስተላለፉት መልክት ላይ « ማሴኬላ የምንወደዉ አባታችን፤ ወንድማችን፤ አያታችን እንዲሁም ጓደናችን ነበር። ከኛ በመለየቱ ልባችን በኃዘን ተሰብሮአል» ይላል።

 በኢትዮጵያ ለየት ያለ የፈጠራ እዉቀት ያላቸዉን ወጣቶች በማሰልጠንና በመደገፍ እንዲሁም ወጣቶቹ የመነሻ ካፒታል እንዲያገኙ በማስቻል ኃሳባቸዉን ይበልጥ እንዲያፈልቁ የሚረዳ ተቋም በእንጊሊዘኛ መጠርያዉ «Bluemoon Ethiopia»ን  የመሰረተችዉ ከዶክተር ኢሌኒ ገብረመድህን በተለይ በወጣትነት ዘመንዋ የሂዉ ማሴኬላን  ሙዚቃዎች አድማጭ እንደነበረች ነግራናለች ። ዶክተር ኢሌኒ የከፍተኛ ትምህርትዋን በተለይ በሰሜን አሜሪካ ዉስጥ ስትከታተል ሂዉ ማሴኬላ የቀረበቡትን የሙዚቃ መድረክ ዝግጅት ከአንዴም ሁለቴ ሦስቴ ገብታ አይታለች። አሁን በቅርቡ ስድስት ወር ባልሞላ ጊዜ ዉስጥ ሞሮኮ ላይ የመልካም አስተዳደር ሁኔታን በሚያጠናዉ «Mo Ibrahim Foundation» በ«ሞ ኤብራሂም» ዓመታዊ ስብሰባ ዶክተር ኢሌኒ ሜሴኬላን በቅርበት አግንታቸዉ ለኢትዮጵያ ያላቸዉን ፍቅር ደጋግመዉ ነግረዋታል። ፎቶግራፍም አብራቸዉ ለመነሳት እድሉ ገጥሟት ነበር ። 

« ሂዉ ማሴኬላ የዛሬ ሃያ ሠላሳ ዓመት በፊት በደንብ የማዳምጣቸዉ አርቲስት ነበሩ። በአፍሪቃ በጣም አንጋፋ የአፍሪካን ጃዝ መስራች በተለይ ደግሞ በትራምፔት ሙዚቃቸዉ የሚታወቁ ናቸዉ። አሜሪካን ሐገር ተማሪ እያለሁ በተለያየ ጊዜ ምናልባትም ሦስት አራት ጊዜ ወደ ዋሺንግተን እና ኒዮርክ አካባቢ ኮንሰርት ሲሰጡ ሄጄ ታድምያለሁ። ሂዉ ማሴኬላን በአካል አግንቻቸዉ አላዉቅም ነበር። ቅርብ ጊዜ በሞሮኮ ላይ በተካሄደ በ «ሞ ኢብራሂም ፋዉንዴሽን» የዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ እንደ አንድ ተሳታፊ አርቲስትም እንደገናም እንደ እንግዳ ሆነዉ ተጋብዘዉ እንደነበር ሰምቼ ዝግጅቱ ወደሚካሄድበት አዳራሽ እየሄድኩ ሳለሁ በአጠገቤ በቅርብ ርቀት ሲያልፉ አየኳቸዉ።

Hugh Masekela Flash-Galerie

ከዝያም ሮጬ አገኘኋቸዉ። በጣም በጣም ደስ አለኝ። ከስንት ዓመታት በፊት ተማሪ እያለሁ ፤ ስለ አፍሪቃ አንድነት፤ ስለ አፍሪቃ እድገት፤ ስለ አፍሪቃ ነፃ መዉጣት እንቅስቃሴ፤ በተለይ በደቡብ አፍሪቃ የነበረዉን የአፓርታይድ ሥርዓት ተቃዋሚ የነበርኩ አንዷ ነኝ፤ በዝያን ጊዜ የእርሶን ዘፈን እያዳመጥኩ ነበር ፤ በጣም ነዉ የምወዶት አድናቂዎት ነኝ፤ ብዬ ቀረብኩ እሳቸዉ፤ ደስ አላቸዉ፤ እስቲ ኢትዮጵያ ኮንሰርት ባዘጋጅ ደስ ይለኛል። መድረክ አዘጋጂልኝ እመጣለሁ እመጣለሁ፤ እንደዉም ስምዋን ዉሰድ ብለዉ ለረዳታቸዉ ሁሉ ስሜን አድራሼዬን እንዲፅፍ ነገሩት።  ትረዳኛለች ኢትዮጵያ ሄጄ ኮንሰርት እንድሰት ትረዳኛለች እያሉ፤ እየተጨዋወትን ወደ አዳራሽን ገባን። ካቀረቡት ሙዚቃዎቻቸዉ መካከል «Stimela» ስቲሜላ የተባለ፤ በጣም የምወደዉ ዘፈናቸዉን ሲጫወቱ እንባዬ መጣ፤ በጣም የድሮዉን ሁኔታ ሁሉ አሰብኩ። ለካ የዝያን ጊዜ በዚያ መድረክ ላይ ለመጨረሻም ጊዜ ነበር ዘፈናቸዉን ያቀረቡት ነበር ማለት ነዉ። ከአየሁዋቸዉን ከተወሰነ ወር በኋላ ነበር ያረፉት። ከዝያም ስብሰባዉ አልቆ በሁለተኛዉ ቀን አዉሮፕላን ይዤ ወደ አዲስ አበባ ስመለስ ፈረንሳይ ደርሼ ነበር ወደ ኢትዮጵያ የማቀናዉ ወደ ፓሪስ የሚሄደዉ በረራ ላይ አዉሮፕላን ዉስጥ በአጋጣሚ ቅርቤ ተቀምጠዉ አገኘኋቸዉ። እንደገና አናገርኳቸዉ። ዳግም ኢትዮጵያን እንዴት እንደሚወዱ ፤ ወደ ኢትዮጵያም መጥተዉ ሙዚቃን መጫወት እንደሚፈልጉ ነገሩኝ። አዎ መሆን አለበት ብዙ ኢትዮጵያዉያን ይወዶታል፤ መምጣት አለቦት አልኳቸዉ። በቃ ይህ ነበር የመጨረሻዉ ንግግራችን። »   

Hugh Masekela

      

ሂዉ ማሴኬላ በመድረክ ላይ ማዜም ብቻ ሳይሆን አብዛኛዉን ሙዚቃዎቻቸዉ በትረካ የታጀቡ እንደሆኑም በተለይ ሙዚቃዎቻቸዉን የሚያደምጡ አድናቂዎቻቸዉ ይናገራሉ። በጎርጎረሳዊ 1939 ዓ.ም በምስራቃዊ ጆሃንስበርግ በካዋጉክዋ ከተማ የተወለዱት ሂዉ ራሞፖሎ ማሴኬላ በ 14 ዓመታቸዉ ፕያኖ ይጫወቱ እንደነበር፤ ለጥቆም በጣም ይፈልጉት የነበረዉን ትሮምፔት የሙዚቃ መሳርያን መጫወት መቀጠላቸዉ የታሪክ መዝገባት ያሳያሉ። በዚህም ማሳኬላ ከ 50 ዓመታት በላይ በትራምፔት ሙዚቃ አጨዋወታቸዉ በዓለም ተደናቂነትን አትርፈዋል። በኢትዮጵያ የሸገር ሬዲዮ የለዛ መርሐ ግብር አቅራቢው ብርኃኑ ድጋፌ ሂዉ ማሴኬላን የዛሬ 13 ዓመት ግድም ኢትዮጵያ መጥተዉ አነጋግሮአቸዋል።  

« ሂዉ ማሴኬላ ወደ ኢትዮጵያ አንድ ጊዜ እንደመጡ ነዉ የማዉቀዉ። በግሌም አንድ ጊዜ ያነጋገርኳቸዉ። ምናልባት ከ 13  ከ 14 ዓመት በፊት ነዉ፤ ኢትዮጵያ መተዉ የነበሩት። የመጡበትም ምክንያት HIV- AIDS ላይ የሚሰራ አንድ ዝግጅት ለመካፈል ነበር። በሻራተን ሆቴል ዉስጥም ከተለያዩ የአፍሪቃ ሐገሮች የመጡ በርካታ ድምፃዉያን ትርዒታቸዉን ያቀርቡ ነበር። ከነዚህም መካከል ሂዉ ማሴኬላ አንዱ ናቸዉ። ሂዉ ማሴኬላን እንኔ እንዳየኋቸዉ ስብዕናቸዉ በጣም ጥልቅ ነበር። እንደዉ እኛ ጋዜጠኞች ትንሽ ፈዘዝ ብለን ሲያዩን « እንዴት  ነዉ እኛ እዚህ ቁጭ ብለን ብዙ የሚጠየቁ ጥያቄዎች እያሉ፤ ለምንድን ነዉ የማትጠይቁት» ሲሉ ነበር የጠየቁን። እናም በዚህ መድረክ ላይ እኔ የጠየኩት ጥያቄ ነበር ። ለዚህ የሰጠኝ መልስ ሁሌም ይገርመኛል። እናንተ አፍሪቃዉያን ሙዚቀኞች የዓለምን ችግር እንደ አፍሪቃዊነታችሁ የአፍሪቃን ችግር መፍትሔ እንሰጣለን ወይም እንፈታለን ብላችሁ ታስባላችሁ ወይ? ብዬ አልኳቸዉ። ሲመልሱም ፤ የአፍሪቃን ችግር እና አፍሪቃዉያን ሙዚቀኞች ብቻችንን መፍታት ብንችል ኖሮ የዛሬ ስንት እና ስንት ዓመት የደቡብ አፍሪቃን ችግር ማሪያ ማኬቫ በፈታችዉ ኖሮ የሚል መልስን ነዉ የሰጠኝ።»      

ሌላስ ስለ ሂዉ ማሳኬላ ምን የምትነግረን አለህ?

« እንግዲህ ሂዉ ማሴኬላ የደቡብ አፍሪቃ የጃዝ አባት ተብለዉ ነዉ የሚጠሩት። ሂዉ ማሴኬላ መድረክ ላይ ሙዚቃን መጫወት ብቻ ሳይሆን ታሪክንም ነዉ የሚናገሩት። ለምሳሌ «ስቲሚላ » የሚል ዘፈን አላቸዉ ። «Stimela» ስቲሚላ ሲጀምር፤ በባቡር ድምፅ ነዉ።  የከሰል ድንጋይ ማዕድን እና ሰራተኞችን የሚያጓጉዝ ባቡር አለ። ከደቡብ አፍሪቃ ፤ ከናሚቢያ፤ ከዚምባቤ ፤ በአጠቃላይ ከደቡብ አፍሪቃ አካባቢ ሃገራት የሚመጡ በርካሽ ገንዘብ ተቀጥረዉ የሚሰሩ ጉልበታቸዉን የሚበዘበዙ የማዕድን ሰራተኞችን የሚያጓጉዝ ባቡር ነዉ። አሁን ይህን ሙዚቃ ለሚሰማዉ ሰዉ ታሪክ እየተናገረ እንደሆነ ግልፅ ያደርጋል። ሂዉ ማሴኬላ በዘፈኖቻቸዉ በመድረክ ላይ ዝግጅታቸዉን ሲያቀርቡ ይህን መንገድ ነዉ የሚጠቀሙት።  ይህ አቀራረባቸዉ ነዉ ከሌሎች ሙዚቀኞች እና የሙዚቃ መሳርያ ተጫዋቾች ለየት የሚያደርጋቸዉ። ሂዉ ማሴኬላ በደቡብ አፍሪቃ በአፓርታይድ ዘመንም ብዙ የታገሉ ሰዉ ናቸዉ። ብዙ ጊዜያቸዉን  ከደቡብ አፍሪቃ ወጥተዉ በዩኤስ አሜሪካና በብሪታንያ ነበር ኑሮአቸዉን ያደረጉት። ከማርያ ማኬቫ ጋር ለሁለት ዓመት በትዳር ከነበራቸዉ፤ሁለቱ ሙዚቀኞች  በፀረ-አፓርታይድ ትግል ትልቅ ሚና የነበራቸዉ ናቸዉ።»   

ታዋቂዉ የደቡብ አፍሪቃ የጃዝ ሙዚቃ አባት ሂዉ ማሳኬላ በተለይ ፓታ ፓታ በሚባለዉ ሙዚቃ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂነትን ካተረፈችዉ ከደቡብ አፍሪቃዊትዋ ታዋቂ የሙዚቃ አቀንቃኝ ማሪያ ማኬቫ ጋር ከጎርጎረሳዊ 1964 እስከ 1966 ዓ,ም በትዳር ቆይተዋል። ነገርን ነገር ያነሳዋል ነዉና ማርያ ማኬቫ የአገራችን የሙዚቃ ንጉስ የጥላሁን ገሰሰን የጥንቱ ትዝ አለኝ የተባለዉን ዜማ በማቀንቀኗም በሐገራችን ይበልጥ ታዋቂነት ማግኘትዋን ያዉቁ ኖርዋል?

የደቡብ አፍሪቃዉ የጃዝ ሙዚቃ አባት ሂዉ ማሴኬላ ሁለት ግሪሚ አዋርድስ እንዲሁም በዓለም ዙርያ በርካታ ሽልማትን አግኝተዋል። ሂዉ ማሳኬላ የዛሬ ስምንት ዓመት  ለአድማጭ ጆሮ ባደረሱት  «ፎላ» በተሰኘዉ የሙዚቃ አልበማቸዉ አንድ ዜማ እዉነተኛ ባልሆኑ የአፍሪቃ የፖለቲካ መሪዎች መራጮች ከምርጫ በኋላ ባዶ እጃቸዉን እንደሚቀሩ፤ ፖለቲከኞች ከቃላት ድርደራ ባለፈ የሚገቡትን ቃል-ኪዳን ተግባራዊ እንደማያደርጉ አዚመዋል።  የተለያዩ ሙዚቃዎችን በማቀናበር እና በሳክስፎን የሙዚቃ መሳርያ ድንቅ አጨዋወቱ የሚታወቀዉ ኢትዮጵያዊዉ ወጣት ጆርጋ መስፍን ባለፈዉ መስከረም ወር ኒዮርክ ሊንከን ሴንተር ባቀረበዉ ሙዚቃ ላይ የአፍሪቃ የጃዝ አባት ሂዉ ማሳኬላ በመድረኩ በዳኝነት ጠረቤዛ ላይ ታድመዉ አግኝቶአቸዋል።   

«ከደቡብ አፍሪቃዉ የጃዝ ሙዚቃ አባት ከሂዉ ማሳኬላ ጋር ባለፈዉ መስከረም ወር በኒዮርክ በሚገኘዉ ሊንከን ሴንተር፤ የእኔን አንድ የሙዚቃ ቅንብር አቀርብ ነበር እና በዚህ መድረክ ላይ ሂዉ ማሴኬላ እንደታዛቢ ተገኝተዉ ነበር። እንደዉም ይባስ ብሎ አንድ ሆቴል ነበር በአጋጣሚ ያረፍነዉ።

ቀረብ ብዬ ለማነጋገር እድሉን አግንቼ ነበር። ሂዉ ማሴኬላ ኢትዮጵያን ይወዳሉ፤ በአፓርታይድ ጊዜ ኢትዮጵያ ኔልሰን ማንዴላን መርዳትዋን እንዴሁም ማንዴላ ኢትዮጵያ መጥተዉ እንደነበር ስለሚያዉቁ በክብር ነበር ያናገሩን። ለኛ ለኢትዮጵያዉያን እንደ ፈር ቀዳጅ ናቸዉ። የአፍሪቃን ሙዚቃ ለዓለም ያስተዋወቁ በመሆናቸዉም እናከብራቸዋለን። በጣም የሚያበረታቱና ሙዚቀኞችን ለማሳደግ የሚጥሩ ሰዉ ነበሩ።   

በሠዉነታቸዉ ዉስጥ በተሰራጨዉ የነቀርሳ በሽታ ምክንያት በ 78 ዓመታቸዉ በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የአፍሪቃዉ የጃዝ አባት ሂዉ ማሴኬላ በደቡብ አፍሪቃ ስዌቶ ዉስጥ በሕይወት ዘመናቸዉ ለሐገራቸዉ ብሎም ለዓለም ሕዝብ ያበረከቱትን አስተዋፅኦ በማዉሳት በደማቅ የጃዝ ሙዚቃ መድረክ ታዉሰዋል፤ ምስጋናንም  ተቸረዋል። የሂዉ ማሴኬላ የሙዚቃ ሕይወት ዘመንን የሚያሳይ የፎቶግራፍ ዓዉደ ርዕይ ጆሃንስበርግ ደቡብ አፍሪቃ ዉስጥ ተከፍቶአልም። የቀብር ሥነ-ስርዓታቸዉ ዘመዶቻቸዉና ወዳጆቻቸዉ ብቻ በተገኙበት እንደሚፈፀም ቤተሰቦቻቸዉ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ባሰራጩት መረጃ አሳዉቀዋል። ለቃለ ምልልሱ የተባበሩንን ሁሉ በዶይቼ ቬለ ስም እያመሰገንን ፤ ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን። 

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic