ደቡብ አፍሪቃና አፍሪቃዉያን ስደተኞች | ኢትዮጵያ | DW | 16.07.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

ደቡብ አፍሪቃና አፍሪቃዉያን ስደተኞች

ደቡብ አፍሪቃዊዉ ጥቁር በነጮች-የዘር መድሎ ሥርዓት ለዘመነ-ዘመናት ሲገደል-ወገኑ የተገደለ ያሕል-የተጋደለለት፥ ሲረገጥ-የተረገጠ ያሕል የታገለለት፥ ሲጋዝ- የጮኸለት፥ ሲሰደድ ያስተናገደዉ አፍሪቃዊ በተራዉ ተቸግሮ ቢሰደድ ከደቡብ አፍሪቃዉያን የገጠመዉ የጥላቻ መስተንግዶ ሰበብ ምክንያት አነጋግሮ አላበቃም።

default

የ2000ዉ ጥቃት

15 07 10

ደቡብ አፍሪቃ ዉስጥ በሚኖሩ አፍሪቃዉያቃዉን ስደተኞች ላይ የሚደርሰዉ ጥላቻና የሚፈፀመዉ ጥቃት ሰሞኑን እንዳዲስ አገርሽቷል።ጥላቻ፥ ጥቃትና ዘረፋዉን በመፍራት በመቶ የሚቆጠሩ አፍሪቃዉያን ስደተኞች ወደየሐገራቸዉ እየተመለሱ ነዉ።የደቡብ አፍሪቃ መንግሥት ጥቃቱን ለመከላከል በርካታ የጦርና የፖሊስ ሠራዊት በየሥፍራዉ አስፍሯል።የዶቸ ቨለዉ ዘጋቢ ሰብሪ ጎቨንደር እንደሚለዉ የአለም እግር ኳስ ዋንጫ እንደተጠናቀቀ በአፍሪቃዉን ስደተኞች ላይ ያነጣጠረዉ ጥቃትና ዘረፋ እንደሚያገረሽ ወትሮም በሰፊዉ ይታመን ነበር።

ደቡብ አፍሪቃዉያን የዛሬ ሁለት አመት ግድም በአፍሪቃዉያን ወገኖቻቸዉ ላይ ሲዘምቱ የደቡብ አፍሪቃዉያን በተለይም የጥቁሮቹ የትናንት ማንነት ከዓዕምሮዉ ላልጠፋዉ አለም፥አስገራሚ ለአፍሪቃ አስደንጋጭ-አሳዛኝም ነበር።በጥቃቱ ሰባ አፍሪቃዉያን ተገደሉ።በመቶ የሚቆጠሩ ከስደት ጎጆ-መጠለያቸዉ ተፈናቀሉ።አብዛኞቹ የዚምባቡዌ ዜጎች ነበሩ።

ደቡብ አፍሪቃዊዉ ጥቁር በነጮች-የዘር መድሎ ሥርዓት ለዘመነ-ዘመናት ሲገደል-ወገኑ የተገደለ ያሕል-የተጋደለለት፥ ሲረገጥ-የተረገጠ ያሕል የታገለለት፥ ሲጋዝ- የጮኸለት፥ ሲሰደድ ያስተናገደዉ አፍሪቃዊ በተራዉ ተቸግሮ ቢሰደድ ከደቡብ አፍሪቃዉያን የገጠመዉ የጥላቻ መስተንግዶ ሰበብ ምክንያት አነጋግሮ አላበቃም።

ተደገመ።ያሁኑ ጥቃት-ና ዘረፋ ያየለዉ ኬፕ ታዉንና ምዕራባዊ የኬፕ ክፍለ-ግዛት አካባቢ ነዉ።አንድ ጋናዊ በጥይት ተገደለ።የሶሚሊያና የሌሎች ሐገራት ተወላጆች መደብሮችና መጋዘኖች ተዘረፉ።ከሁለት መቶ በላይ ስደተኞች ከየስደት ቤታቸዉ ተፈናቀሉ።

ሌሎች በመቶ የሚቆጠሩ አፍሪቃዉያን ስደተኞች ባብዛኛዉ የዚምባቡዌ ተወላጆች ወደየሐገራቸዉ ለመመለስ ጅሐንስበርግ እየገቡ ነዉ። የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊኩ የኮምፒዉተር ባለሙያ-ደቡብ አፍሪቃ ዉስጥ አምስት አመት ኖሯል-ሠርቷልም።አስራ-አንድ ቤተሰቡን ይረዳል።ነገን ግን አያዉቅም።

«አዎ በጣም ነዉ የምሰጋዉ።ልጆች አሉኝ።የመጨረሻዉ ልጄ ሁለት አመቱ ነዉ።እንዴት ይኖራሉ እያልኩ እያሰብኩ ነዉ።አንድ ነገር ማድረግ አለብን።በቅጡ ማሰብ አለብን።የትም ብንሔድ (ልጆቹ) በነፃነት መንቀሳቀስ አለባቸዉ።ግን ነገ ምን እንደሚሆን አላዉቅም።እንደማንኛዉም ሰዉ ተገቢዉ ነገር ሊደረግላቸዉ ይገባል።»

እሱ ሞይላ ሊዊስ ይባላል።ትክለኛ ስሙ ይሁን አይሁን አይታወቅም።ኢትዮጵያዊ ነዉ።ደርባን ዉስጥ ሁለት አመት ኖሯል።የኢንተርነት ካፌ ባለቤት ነዉ።ለሱ ማምለጥ-ነዉ ብልሐቱ-ይላል።

«እኔ በበኩሌ ለመሸሽ ተዘጋጅቻለሁ።ሊደበድቡን ከቃጡ እኔ መሸሽ ነዉ-የምፈልገዉ።»

ይኸኛዉም የደርባን ነዋሪ ነዉ።የብሩንዲ ዜጋ።እሱና ብጤዎቹ የሚገደሉ፥ የሚደበደቡ፥ የሚዘረፉበት ምክንያት አይገባዉም።ወደ ደቡብ አፍሪቃ የተሰደደዉ ሐገሩ የገጠመዉን ችግር ሽሽት ነበር።አሁን ግን መሔጃም የለዉ።

«እርስ በራሳቸዉ ለምን እንደሚጋጩ አይገባኝም።ሁላችንም አፍሪቃዉያን ነን።ለኔ ይሕ ጥሩ አይደለም።የት እንደምሔድም አላዉቅም።ምክንያቱም ሐገሬ ሩቅ ነዉ።ወደ እዚያ መሔድም አዳጋች ነዉ።»

የደቡብ አፍሪቃ መንግሥት -ገዳይ፥ ደብዳቢ ዘራፊዎቹ ወርሮ በሎች ናቸዉ ባይ ነዉ።የፖሊስ ምክትል ሚንስትር ፊኪሌ ምቡላላ እንደሚሉት ደግሞ ሐገራቸዉ ያስተናገደችዉ የአለም እግር ኳስ ዋንጫ የአፍሪቃን አንድነት አስመስክሯል።

«የአለም እግር ኳስ ግጥሚያ ራሱ በሕዝባችን መካካል ብሔራዊ አንድነት እና የአፍሪቃዉያንን ትብብርን ነዉ-ያጠናከረዉ።ይሁንና ሥራ አጥነትና ድሕነት ይሕ የዉጪ ሰዎች ጥላቻ ተብሎ የሚጠራዉን ችግር አባብሶታል።»

በተለያዩ ዘሮች መካካል ያለዉን ግንኙነት የሚያጣናዉ ተቋም ቃል አቀባይ ካትሪን ሹስለር እንደሚሉት ግን የዛሬ ሁለት አመት የተፈፀመዉን ጥቃት የጫረዉ ሁኔታ አሁንም አልተቀየረም።

«መንግሥትን እንዲያደርገዉ የምንገፋፋዉ የአመራር ሥልጣኑን በመጠቀም ደቡብ አፍሪቃ የሚኖሩ ስደተኞች ያሉበትን ደረጃ እንዲያሻሽል ነዉ።(የመንግሥት ባለሥልጣናት) እነዚሕ ስደተኞች ለሐገሪቱ ምጣኔ ሐብት የሚያበረክቱትን አወንታዊ አስተዋፅ እንዲያጎሉት እንፈልጋለን።»

ስደተኞቹ የሚሹት መንግሥት ጦር ከማስፈር እኩል የዉጪ ሐገር ዜጎች ሥራና ገቢዬን ይሻሙኛል የሚለዉ የደቡብ አፍሪቃዉያን አስተሳሰብ ለመቀየር እንዲጥር ነዉ።

ሰብሪይ ጎቨንደር

ነጋሽ መሐመድ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic