ደቡብ ሱዳን፤ ከጦርነት ወደ ጦርነት | አፍሪቃ | DW | 23.12.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ደቡብ ሱዳን፤ ከጦርነት ወደ ጦርነት

ከፖለቲካ ዲፕሎማሲዉ ይልቅ፥ ጠመንጃ ጦርነትን ያደጉ የኖሩበት ሳልቫ ኪር የዲንካን፥ እንደ ፖለቲከኛ-ሻጥርን፥ እንደ ዲፕሎማት ግድምድሞሽ ዘይቤን፥ እንደ ታጋይ የጫካ ዉጊያ አጣምረዉ የያዙት ዶክተር ሪክ ማቼር የኑዌር ጎሳን፥ ከየጎናቸዉ አሰልፈዉ ተፋጠዋል።

default

ኪርና ማቼር ክጎረቤት ሐገራት መሪዎች ጋር-አምና ሐምሌ

የዛሬ-ስምት ዓመት በዚሕ ወቅት ግድም የረጅም ጊዜዉ ጦርነት፥ የሚሊዮኖች እልቂት ፍጅት ስደት አበቃለት ተባለ።የዛሬ-ሰወስት ዓመት በዚሕ ወቅት ግድም ሕዝቧ በነፃ ዉሳኔዉ ነፃነትዋን ማስፀደቁ ተነገረ። የዓለም ፖለቲከኞች መሠከሩለትም።ደቡብ ሱዳን።ሐምሌ-ሁለት ሺሕ አስራ-አንድ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ነፃነቷ ታወጀ።ፌስታ።

ወዲያዉ ግን ግጭት። ደግሞ ጦርነት።ዛሬም ጦርነት ላይ ናት።አዲስ ሐገር፥ ግራ አጋቢ ምድር።እንዴት ለምን? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።

አምና ነዉ።መስከረም።አዲሲቱን አፍሪቃዊት ሐገር ካሮጌ እልቂት ፎጅቷ ለመድፈቅ፧ አዳዲስ ጄኔራሎቿ የጀመሩት አመፅ፣ የአሮጌ ፖለቲከኞችዋን ነባር ሸኩቻ፤ የነባር ጎሶችዋን አሮጌ ግጭት ባዲስ መልክ አንሮታል።እንደ የበላይ የበታቾቻዉ ሁሉ በዉጊያ፣ አመፅ፣ ሽኩቻ፣ የኖሩት የያኔዉ የሐገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቼር ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ኒዮርክ የገቡት አዲሱ አመፅ፣ ሽኩቻ ግጭት ከኖሩበትና ከዘወሩት ብዙ ብጤዉ እንደማይከፋ እያሰላሰሉ ነበር።

ማቼር ከጉባኤዉ አዳራሽ ሲደርሱ ካገጠሟቸዉ ጋዜጠኞች ቢያንስ አንዱ የአዲሲቱ ሐገራቸዉን አዲስ ቀዉስ ምናልባትም የራሳቸዉንም ቅሬታ በቅጡ የሚያዉቅ ሳይሆን አይቅርም። «መንግሥትዎን መፈንቅለ መንግሥት ያሰጋዋል ይባላል» ብሎ ጠየቃቸዉ።ጥያቄዉ ያሰቡትን-ወይም ያለሰቡትን የሚያሳስብ ሊሆን፥ ላይሆንም ይችላል።መልሳቸዉ ግን «በፍፁም» የሚል ነበር።

እንዲሕ አይነት እርምጃ «ጅልነት» አሉ-አሉ አንጋፋዉ የነፃነት ታጋይ፥ «አዲሱን መንግሥት በአመፅ መጀመር አንፈልግም።» አከሉ፥-የአዲሲቱ ሐገር የያኔ ትልቅ ሹም።አሁንም አምና ነዉ።ግን ሐምሌ። ኪር እና ማቸር በየልባቸዉ የሚያስቡ፥ የሚያሰላስሉትን ከነሱ በስተቀር በግልፅ የሚያዉቅ-ከነበረ ቢያንስ አስካሁን በግልፅ አይታወቅም።ሁለቱም ሁለት ዓመት እንደኖሩበት የመጀመሪያዉ እንደ ፕሬዝዳት፥ ሁለተኛዉ እንደ ምክትል ፕሬዝዳት በዓሉን አከበሩ።የነፃነት በዓል-ሁለተኛ ዓመት። ወዲያዉ ግን የመጀመሪያዉ ከሥልጣን አባራሪ፥ ሁለተኛዉ ተባባራሪ ሆኑ።

«አሁን የአንድ ሰዉ አገዛዝ ነዉ ያለን።ያንድ አገዛዝ ምን ማለት ነዉ።አምገነንነት።»

የቀድሞዉ ምክትል ፕሬዝዳት ሪክ ማቸር።ከሥልጣን በተባረሩ ማግሥት።ሐምሌ።ደቡብ ሱዳን፥ የሚነገር አይሆንባትም፥ የታቀደ አይፈፀምባትም፥የተነገረ-አይታመንባትም።ወይም የሚነገር፥ የሚባል፥ የሚታቀደዉ ከነባር እዉነቷ፥ከአቅም ማንነቷ ጋር ይጣረሱባታል።ማቼርም አምና መስከረም እንደ ምክትል ፕሬዝዳት ኒዮርክ ላይ የተቃወሙትን፥ባለፈዉ ሳምንት ለዕሁድ አጥቢያ ጁባ ላይ አደረጉት።መፈንቅለ መንግሥት።ከሸፈ።መዘዙ ግን ዛሬም አላባራም።

ፕሬዝዳት ሳልቫ ኪር የመላዉ ሱዳንን የምክትል ፕሬዝዳትነት ሥልጣን ከጆን ጋራግ ከወረሱበት ጊዜ ጀምሮ አደባባይ ሲወጡ አሜሪካኖች «የእረኛ» የሚሉት ሠፊ-ክብ ባርኔጣ ካናታቸዉ ተለይቶ አያዉቅም።ይወዱታል።ባርኔጣዉ በሚዘወተርበት ቴክስሳ ግዛት ያደጉ-የሚኖሩት የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ ለሳልቫ ኪር የሸለሟቸዉም ይሕኑ ባርኔጣ ነበር።

ዕሁድ ግን ባርኔጣቸዉን አዉልቀዉ፥ ሱፍ ከረባትታቸዉን በጄኔራል ማዕረግ በተንቆጠቆጠ የዉጊያ ልብስ ቀይረዉ ከጦር ሜዳ እንደተመለሰ ጄኔራል እያጉረጠረጡ ከቴሌቪዥን ካሜራ ፊት ብቅ አሉ።

«ከቀድሞዉ ምክትል ፕሬዝዳት ከዶክተር ሪክ ማቼር እና ከቡድናቸዉ ጋር የሚተባበሩ ወታደሮች ጁባ ዩኒቨርስቲ አጠገብ በሚገኘዉ በSPLA ዋና ፅሕፈት ቤት ላይ ጥቃት ፈፅመዋል።ጥቃቱ እስከ ዛሬ ጠዋት ድረስ ቀጥሎ ነበር።ይሁንና ለዜጎቼ በሙሉ፥ መንግሥታችሁ ጁባ ያለዉን የፀጥታ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩን ማሳወቅ እፈልጋለሁ።»

እርግጥ ነዉ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዉ ከሽፏል።የአዲሲቱ ሐገር እዉነታ ግን ፕሬዝዳንቷ ካሉት ተቃራኒዉ ነዉ።ራሷ ጁባ፥ ቦር፥ ጃንጌሌይ፥ ዩኒቱ ከተሞች እና ግዛቶች ዛሬም በሳምንቱ በዉጊያ ይርዳሉ።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ፓን ጊሙን ይሕን መሠከሩ።

«እያሽቆለቆለ የመጣዉ የደቡብ ሱዳን የፀጥታ ሁኔታ በጣም አሳስቦኛል።ሁሉም የፖለቲካ፥ የጦር እና የሚሊሺያ ሐይላት መሪዎች ሰላማዊ ሰዎችን የሚጎዳዉን ጠብ፥ ግጭታቸዉን እንዲያቆሙ እጠይቃለሁ።»

የሰማቸዉ እንጂ ቢያንስ እስካሁን የተቀበላቸዉ የለም።ጥንት በዚያ ግዛት እንዲያ ነበር።ድሮም።የዛሬ ስምንት ዓመትም እንዲሁ።ጥር ዘጠኝ።ሁለት ሺሕ አምስት።ናይሮቢ።

«ወገኖቼ፥ የሐገሬ ወንዶችና ሴቶች ሆይ! እንኳን ደስ አላችሁ።ደስታም በናንተ ላይ ይሁን። ንቅናቄያችሁ SPLM/SPLA እና የብሔራዊ ምክር ቤት መንግሥት አጠቃላይ የሠላም ስምምነት ተፈራርመዉላችኋል።ዛሬ የፈረምነዉና እናንተ ያችሁትን ፍትሐዊ እና የተከበረ የሠላም ዉል አቅርበንላችኋል።በዚሕ የሠላም ዉል መሠረት ከአፍሪቃ ረጅሙን ጦርነት አቁመናል።»

የቀድሞዉ የደቡብ ሱዳን ነፃ አዉጪ ጦርና ንቅናቄ መሪ ዶክተር ጆን ጋራንግ።ጋራንግ እንዳሉት ትልቂቱ አፍሪቃዊት ሐገር በ1956 ነፃ ከወጣችበት ጊዜ ጀምሮ ከጥቂት ዓመታት ፋታ በስተቀር ጦርነት ተለይቷት አያዉቅም።ስምንቱ ሚሊዮኖችን የፈጀዉ፥ ከአራት ሚሊዮን በላይ ያሰደደዉን፥ ሰላሳ-ዘጠኝ ዓመታት ያስቆጠረዉን ጦርነት ማስቆሙ እርግጥ ነዉ።

ከወጣትነት ዘመናቸዉ ጀምሮ ለአርባ ዓመታት ያኽል ያን ጦርነት ባንድ ወይም በሌላ መልኩ ሲዘዉሩ የነበሩት ጆንጋራንግ ያን ስምምነት ሲያበስሩ ዘግናኙ ጦርነት መቆሙን ብቻ ሳይሆን ሌላ ብጤዉ እንደማይከሰትም እርግጠኛ ነበሩ።ወይም ላዳመጣቸዉ መስለዉ ነበር።

«በዚሕ ሥምምነት መሠረት ከእንግዲሕ በየዋሕ ሕፃናትና እናቶች ላይ ከሠማይ የሚወርድ ቦምብ አይኖርም።ከእንግዲሕ ሕፃናት በደስታ የሚቦርቁበት፥ ባንድ ወይም በሌላ መልኩ ደስታቸዉን የተቀሙ እናቶች በእልልታ የሚደሰቱበት ሠላም ይሠፍናል።»

ተናገሩ።አልበሽር (የሰሜን ሱዳን ፕሬዝዳንት) ቦምብ የሚባለዉን ቃል ሲሰሙ ፈገግ አሉ። ጆንግ ጋራንግ የሠላም ስምምነቱን ዉጤት ለማየት፥ የሐራቸዉን ነፃነት ለመመልከት አልታደሉም።ከአርባ ዘመን ጦርነት አምልጠዉ በቅፅበት የሔሊኮብተር አደጋ-ሞቱ።ጋራንግ እንዳሉት እኒያ የሰሜን ሱዳን አዉሮፕላኖች የሚያወርዱት ቦምብ ከሁለት ሺሕ አምስት በኋላ ቆሟል።ደቡብ ሱዳን ግን ሠላም ሆና አለማወቋ እንጂ ቁጭቱ።

Südsudan Juba Ausschreitungen Flüchtlinge UN

የጁባ ነዋሪዎችበነፃነትዋ ዋዜማ ኮርዶፋን ግዛት ለተደረገዉ ጦርነት ሰሜን ሱዳኖችን መዉቀስ፥ መወነጅሉ፥ ለዛሬዎቹ የጁባ ገዚዎችም፥ ለምዕራባዉያን ደጋፊዎቻቸዉም ቀላል ነበር።አምና መጋቢት ሒጂሊጅ እና አካባቢዉን ያጋየዉን ዉጊያ የቆሰቆሱት ሳል ቫኪር መሆናቸዉ አለጠያየቅም፥ ጦርነቱ የቆመዉ ግን ሐያሉ ዓለም አልበሽርን አዉግዞ አስጠንቅቆ፥ ኪርን ካባበለ በኋላ ነበር።

ደቡብ ሱዳን እስከ ዛሬም ከአስሩ ግዛቶችዋ ዘጠኙ በእርስ በርስ ጦርነት፥በጎሳ ግጭትና ቁርቁስ እንደተመሠቃቀሉ ነዉ።እና ሰሜን ሱዳኖች የሚያወርዱት ቦምብ በርግጥ የለም።የደቡብ ሱዳን ሕዝብ ግን ዛሬም እንደተገደለ፥ እንደ ቆሰለ፥ እንደተሰደደ፥ እንደተራበ ነዉ።የሳልቫ ኪርን አገዛዝ እና የሳልቫ ኪር ጎሳ የዲንካን የበላይነት በመቃወም በየሥፍራዉ ያመፁት ሰባት የተለያዩ ቡድናት ከመንግሥት ጦር እና እርስር በርስ በሚያደርጉት ዉጊያ በብዙ ሺሕ የሚቆጠር ሕዝብ ተገድሏል።በብዙ ሺሕ የሚቆጠር ተፈናቅሏል።ወይም ተሰዷል።

አሁን ደግሞ መፈንቅለ መንግሥትና መዘዙ ያንመከረኛ ሕዝብ ከዳግም እልቂት፥ ስደት፥ ዶሎታል። አምና መስከረም ጋዜጠኛዉ ማቸርን ሥለመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የጠየቀዉ፥ የሐገሪቱን የፖለቲካ ዉጥንቅጥ፥ የጎሳ ጠብ፥ ቁርቁስን ሥላወቀ፥ ወይም ሥለገመተ እንጂ-ነብይነት ቃጥቶት አልነበረም።
በጁባ የዩናይትድ ስቴትስዋ አምባሳደር ሱዛን ፔጅ በቀደም እንዳሉት ግን የሆነዉ እንደሚሆን ማወቅ አይደለም የጋዜጠኛዉን ያሕል እንኳን አልገመቱም ነበር።ማንም አልጠበቀም ይላሉ በጁባ የልዕለ ሐያሊቱ ሐገር ዲፕሎማት።

«የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በርግጥ ከአቅሙ በላይ ተወጥሯል።እዚሕ ያለ ማንም ቢሆን የተለመደዉን ሠብአዊ ርዳታ ለማቀበል ነበር የተዘጋጀዉ።ጁባ ዉስጥም ሆነ በክፍለ ግዛቶች አሁን የተፈጠረዉ ቀዉስ ይፈጠራል ብሎ ማንም ሰዉ አልጠበቀም።»

ከኑዌር የሚወለዱት ሪክ ማቼር እንደመሩት በሚታመነዉ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራና ሙከራዉን ባከሸፈዉ በፕሬዝዳት ሲልቫ ኪር ታማኞች መካካል ጁባ ዉስጥ ብቻ በተደረገዉ ዉጊያ ስድስት መቶ ሰዎች ተገድለዋል።በሌሎች ከተሞችና ክፍለ ግዛቶች በተደረገና በሚደረገዉ ዉጊያ የሞተ-የተሰደደ፥ የተፈናቀለዉን በትክክል የቆጠረዉ የለም።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳስታወቀዉ ጁባ እና ቦር በሚገኙ ሰወስት ቅጥር ግቢዎቹ ብቻ ከሠላሳ-አምስት ሺሕ በላይ ሕዝብ ተጠልሏል።ምዕራባዉያን ሐገራት ዜጎቻቸዉን ከምስቅልቅሊቱ ሐገር ማሸሹን ነዉ-ያስቀደሙት።ከዋና ፀሐፊ ፓን ጊ ሙን እስከ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ ያሉ መሪዎች ተፋላሚ ሐይላት ከተጨማሪ ጦርነት ታቅበዉ ልዩነታቸዉን በሰላም እንዲፈቱ መጠየቅ-፥ ማሰሰባቸዉ አልቀረም።

የኢትዮጵያን ጨምሮ የአካባቢዉ ሐገራት ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ጠብ፥ ግጭት፥ ጦርነቱን በሰላም ለመፍታት ባለፈዉ ሳምንት የጀመሩት የድርድር ጥረት ፍሬማ ዉጤት ማሳየቱን ጠቁመዋል።የደቡብ ሱዳኑ ማስታወቂያ ሚንስትር ሚካኤል ማኩይ በፋንታቸዉ መንግሥታቸዉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን አስታዉቀዋል።

«የደቡብ ሱዳን መንግሥት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመደራደር ዝግጁ ነዉ።የምሥራቅ አፍሪቃ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ለድርድር የሚያስፈልጋቸዉን መረጃ ብቻ ሳይሆን ለጀመሩት ጥረት የደቡብ ሱዳን መንግሥትን ሙሉ ዉክልናም አግኝተዋል።»

ከምሥራቅ አፍሪቃ ሐገራት መካካል ዩጋንዳ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሯን ብቻ ሳይሆን ጦሯንም ነዉ-ጁባ ያዘመተችዉ።የሠላም፥ ዲፕሎማሲና የዉጊያ ዘመቻ!! «የደቡብ ሱዳን ማስታወቂያ ሚንስትር መንግሥታቸዉ «ያለ ቅድመ ሁኔታ ለመደራደር መዘጋጀቱን ሲገልፁ፥የሐገሪቱ የጦር አዛዦች ባንፃሩ አማፂያኑ የሚቆጣጠሩትን ቦርን መልሶ የሚይዝ ጦር እያዘመቱ መሆናቸዉን አስታዉቀዋል።

ደቡብ ሱዳን፥ የሚባል አይደረግባትም።ከፖለቲካ ዲፕሎማሲዉ ይልቅ፥ ጠመንጃ ጦርነትን ያደጉ የኖሩበት ሳልቫ ኪር የዲንካን፥ እንደ ፖለቲከኛ-ሻጥርን፥ እንደ ዲፕሎማት ግድምድሞሽ ዘይቤን፥ እንደ ታጋይ የጫካ ዉጊያ አጣምረዉ የያዙት ዶክተር ሪክ ማቼር የኑዌር ጎሳን፥ ከየጎናቸዉ አሰልፈዉ ተፋጠዋል።

የዚያች ሐገር አበሳ-በሁለቱ ታዋቂ ፖለቲከኞችዋ ጠብ፥ ግጭት አለማብቃቱ ነዉ ክፋቱ።

ከኑዌር የሚወለዱት እዉቅ ጄኔራል ፔተር ጋዴት፥በቅርቡ ከዩኒቲ ግዛት አስተዳዳሪነት የተሻሩት ታባን ዴንግ ጋይ፥ ከባሪ የሚወለዱት የቀድሞዉ ሚንስትርና ጄኔራል አልፍሬድ ላዱ ጎር፥የአናሳዉ የመርል ጎሳ አባል የሆኑት ዴቪድ ያዩ፥ እና በርስበርሱ ጦርነት ወቅት «ነጩ ጦር» በመባል የሚታወቀዉ ሚሊሺያ ሐይል ሁሉም እንደ ጋራ ጠላት በሚያዩት በሳልቫ ኪር መንግሥት ላይ ጠመንጃቸዉን አነጣጥረዋል።ይተኩሳሉም።አል በሽር አሁንስ ይፈግጉ ይሆን? ደቡብ ሱዳንስ ወዴት፥ እንዴት ትጓዝ ይሆን? ሥለ ማሕደረ ዜና ያላችሁን አስተያየት፥ ማሕደረ ዜና ቢቃኘዉ ጥሩ ነዉ የምትሉትን ጥቆማ በደብዳቤ፥ በስልክ፥ በፌስ ቡክ፥ በኢሜይል፥ በኤስ ኤም ኤስ ላኩልን።እስካሁን አስተያየት ጥቆማ የሰጣችሁኝን አመሰግናለሁ። ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰAudios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች