ደቡብ ሱዳን ከተኩስ አቁም ስምምነቱ በኋላ | አፍሪቃ | DW | 27.01.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ደቡብ ሱዳን ከተኩስ አቁም ስምምነቱ በኋላ

ቀድሞ የግብጹ መሓመድ ዓሊ ንጉሳዊ ግዛት አካል የነበረው የሱዳን ምድር እጎኣ በ1956 ዓም ነጻ መንግስት መሆኑን ተከትሎ በኣገሪቱ በተቀሰቀሰው የመጀመሪያው የሱዳኖች የእርስ በርስ ጦርነት ምክኒያት ደቡብ ሱዳን ያኔ የራስገዝ ኣስተዳደር ለመሆን በቅታ ነበር። በ 1972 ዓም።

ወዲያውኑ ግን ከ 11 ዓመታት በኃላ በ 1983 የራስ ገዝ መብቷ በኣዋጅ ተገፈፈ። ይህም ለሁለተኛው የሱዳኖች የእርስ በርስ ጦርነት መቀስቀስ ምክንያት ሆነና እስከ 2005 ዓም ድረስ ለ 22 ዓመታት የዘለቀው ኣውዳሚ ጦርነት ተካሄደ።

በእርግጥ እንደ ኣገር ነጻነቷን እስከተቀዳጀችበት 2011 ዓም ድረስ ባሉት 6 ዓመታት ግዛቲቱ ኣንጻራዊ እፎይታ ኣግኝታ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ግን 3ኛው የሱዳኖች የእርስበርስ ጦርነት ዳግም ተጫረ። እናም ካለፈው የየጎርጎሮሳውያኑ ታህሳስ ወር ኣጋማሽ ኣንስቶ እስካለፈው ሳምንት ማገባደጃ ድረስ በነበሩት 5 ሳምንታት በደቡብ ሱዳን ይስተዋል የነበረው ሁኔታ፤ የቅርብ ምንጮች እንደሚሉት፤ ያኔ ከ1983 – 2005 ባሉት 22 ዓመታት የነበረውን ይመስል ነበር።

ያኔ የካርቱሙ መንግስት ዋና ዋና ከተሞችን እና ኣውራ ጎዳናዎችን ብቻ ነበር የሚቆጣጠረው። የሱዳን ህዝብ ነጻ ኣውጪ ንቅናቄ SPLM እና ጦሩ SPLA ደግሞ የገጠሩ መንግስት ሲሆኑ በትልቁ የSPLA ይዞታ ውስጥም የየራሳቸውን የጎሳ ጎጥ የሚቆጣጠሩ በርካታ ትናንሽ የጎበዝ አለቆች ደግሞ ነበሩ። ሁሉም በያለበት ያሻውን ያደርጋል። ሲስማሙ በእርግጥ እነሱ ቅኝ ገዢ የሚሉትን የካርቱሙን መንግስት በጋራ ያጠቃሉ። ሲጋጪ ደግሞ እርስ በእርስ ከመዋጋት ኣልፈው ሰላማዊዉንም ህዝብ ይፈጁታል። ኣሁንም የሆነው ይኸው ነበር።

ባለፈው ሐሙስ በእርግጥ ሁለቱ የደቡብ ሱዳን ባላንጣዎች በኢጋድ ኣደራዳሪነት በሸራተን ኣዲስ የመጀመሪያውን የሰላም ውል መፈራረማቸው ይታወቃል። ሆኖም ግን በዓማጺያኑ በኩል የቀድሞው ም/ፕ ሪክ ማቻር ሁሉንም ዓማጺያን ኣይወክክሉም ከሚለው ስጋት ኣንስቶ በሁለቱም ወገን የተኩስ ኣቁም ስምምነቱ ተጥሷል የሚለው ውንጀላ ማስተጋባቱ የመገናኛ ብዙኃን የሰሞኑ የዜና ርዕስ ሆኗል። በደቡብ ሱዳኑ ፕሬረዚደንት ሳልቫኪር ታማኝ ዋታደሮች እና በቀድሞው የኣገሪቱ ም/ፕሬዚደንት ሪክ ማቻር ደጋፊ ሰራዊት መካከል ባለፉት 6 ሳምንታት በተካሄደው ኣሰቃቂ እና ኣውዳሚ ጦርነት በትንሹ ከ 10 ሺህ በላይ ሰዎች ሲገደሉ 700 ሺህ ያህል ህዝብ ደግሞ ከቀኤው ተፈናቅሏል። በ ተመድ የሰላም ኣስከባሪ ጦር ሰፈር ብቻ 76 ሺህ ህዝብ ህይወቱን ለማትረፍ ተጠልሏል። በተለያዩ የጦር አበጋዞች የሚታዘዙ በርካታ ጥቃቅን የጎሳ ሚሊሺያዎች ኣንዱ የሌላውን ይዞታ እየወረረ፤ እየዘረፈ እና እየገደለ መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራዎች ደርሷል። ለኣስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ከተከማቸው የ ተመድ የእህል መጋዘን ሳይቀር 3,700 ሜትሪክ ቶን እህል ተመዝብሯል። የዚህ ሁሉ መዘዝ መነሻው ታዲያ በፕሬዚደንት ሳልቫኪር እና የእርሳቸውን ኣገዛዝ በሚቃወሙት የገዢው SPLM ፓርቲ ባለሥልጣናት መካከል የተፈጠረው ልዩነት ሲሆን በዚሁ ምክንያት ፕሬዚደንት ሳልቫኪር ባለፈው ነሓሴ ወር ም/ፕ ማቻርን ጨምሮ እነዚህን ባለስልጣናት ከስልጣን ማባረራቸው ይታወቃል። ይህም ይላሉ ከዓለም ዓቀፍ የጸጥታ ጥናት ተቐም ዶ/ር ሰለሞን አየለ ደርሶ፤ ደጋፊዎቻቸውን ኣስቆጥቶ እና የከረሙ ቁርሾዎችን ቀስቅሶ ሁኔታው በቀላሉ ወደ ጦርነት ሊያመራ ችሏል።

ኣሁንም ድረስ ኣንዱ ሌላውን የተኩስ ኣቁም ስምምነቱን ጥሷል በሚል መወነጃጀላቸው ባይቀርም ባለፈው ሀሙስ ግን ሁለቱ ወገኖች የሰላም ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።

የተኩስ ኣቁም ስምምነት ሲባል ዶ/ር ሰለሞን እንደሚሉት፤ ሁለቱም ወገኖች ባሉበት ቦታና ሁኔታ ምንም ዓይነት ተጨማሪ ቦታ ሳይዙና ውጊያ ሳያደርጉ ይቆያሉ ማለት ነው። ይህንኑ የሚቆጣጠር የኢጋድ ታዛቢ አካልም ይቐቐማል ተብሏል። ሌላው ኣወዛጋቢ ጉዳይ የኡጋንዳ ጦር ጣልቃ መግባት ሲሆን ከዚህ ስምምነት በኃላስ ምን ሚና ይኖረዋል? የሚሉ እና ሌሎች ገና ያልተቐጩ በርካታ ጉዳዮችም ኣሉ። በ SPLM ውስጥ የተፈጠሩ ችግሮችንም ሆነ ኣገሪቱ በምን መልኩ ትመራ በሚለው ዋና አጀንዳ ላይ ቀጣይ ድርድር ይኖራል። በድርድሩ መሰረትም የብሔራዊ እርቅ ጉባዔ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል። ይሁን እንጂ ዶ/ር ሰለሞን እንደሚሉት ይህ ፈተና እንዲህ በቀላሉ የሚታለፍ ሳይሆን ኣጣቃላይ ፍተሻን የሚጠይቅ ነው።

የኣዲስ ኣበባው የሰላም ስምምነት በተፈረመበት ወቅት ዋና ኣደራዳሪውን አምባሳደር ስዩም መስፍንን ጨምሮ የተለያዩ ወገኖች ኣጽንዖት ሰተው እንደተናገሩት፤ የዚህ ኣይነቱ ኣሰቃቂ እልቂት እንዳይደገም እና በኣገራቱ ዳግም ቀውስ እንዳይከሰት ለማድረግ ሁሉን ኣቀፍ ኣገራዊ እርቅ ከማካሄድ ጎን ለጎን የደረሰውን ጉዳት የሚመረምርና የመፍትሄ ሀሳብ የሚያቀርብ የኣፍሪካ ህብረት መርማሪ ኮሚሺንም ይቐቐማል። የፈሰሰው ደም ከንቱ እንዳይቀርም የጦር ወንጀለኞች ለፍርድ የሚቀርቡበት ሁኔታም ሊመቻች ይገባል ተብሏል። በUS አሜሪካ ማሳቹትሴት ዩኒቨርሲቲ የዓለም ዓቀፍ ግኑኝነት መምህር የሆኑት የፖለቲካ ተንታኙ ሚ/ር ኤሪክ ሪቨስ ግን ወንጀለኞችን በፍርድ የመዳኘቱ ሂደት በዚያች ኣገር የማይታሰብ ነው ይላሉ።

የኃያላኑ መንግስታት በተለይም የአሜሪካና የቻይና የእጃዙር የኢኮኖሚ ፍልሚያ ነው ከሚባልለት የደቡብ ሱዳኑ ቀውስ ጋር በተያያዘ ሌላው ኣነጋጋሪ ጉዳይ የደቡብ ሱዳን ፕሬዚደንት ሳልቫኪር በ ተመድ ላይ የሰነዘሩት የሰላ ወቀሳ ነው። የጸጥታ ጥናት ተቐም ተንታኝ የሆኑት አቶ ሃሌሉያ ሉሌ እንደሚሉት ሁኔታው በዚያች ኣገር ለሚካሄደው የመልሶ እርቅ እና የጸጥታ ሂደት የሚበጅ ኣይደለም።

ከሜን ሱዳን፤ ኢትዮጵያ፤ ኬኒያ፤ ኡጋንዳ፤ ዲ ሪ ኮንጎ እና ማ ኣ ሪፐብሊክ ጋር የምትዋሰነው፤ የባህር በር ኣልባዋ፤ ደቡብ ሱዳን የነጭ አባይ ዱካን ተከትሎ በሚገኘው እና ባህር አል ጀበል በሚባለው ለምና ለምለም ሸለቆ ይበልጥ ትታወቃለች። እጎኣ ነሐሴ 9 2011 ነጻ መንግስት ሆኖ የተመዘገበው የደቡብ ሱዳን መንግስት ለጊዜው የሚቀመጠው ጁባ ላይ ሲሆን ወደፊት ግን ይበልጥ ኣማካኝ ወደሆነችው የራማሺየል ከተማ ይዛወራል የሚል እቅድ ኣላቸው። የህዝብ ብዛቷ 9 ሚሊየን ሲገመት ቱባዎቹን ዲንቃን እና ኑዌርን ጨምሮ ከ 60 በላይ የየራሳቸውን ቐንቐ የሚናገሩ የተለያዩ ብሄረሰቦች ይገኙባታል።አብዛኞቹ የየራሳቸውን ባህላዊ ልማዶች ሲከተሉ እስልምን እና ክርስትናም በስፋት ይገኛል። ከባህላዊ ዘዴ ያልተላቀቀው ግብርና እና ከብት እርባታ የህብረተሰቡ ዋና የኢኮኖሚ መሰረት ነው። ኣገሪቱ ከፍተኛ የደን ኃብት ሲኖራት በነዳጅ ዘይት ሀብቷም ከሰኃራ በታች ከሚገኙት የኣፍሪካ ኣገሮች በ 3ኛነት ትጠቀሳለች።

ጃፈር ዓሊ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic