ደቡብ ሱዳን እና የተመድ አጣሪ ቡድን | አፍሪቃ | DW | 09.12.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ደቡብ ሱዳን እና የተመድ አጣሪ ቡድን

ውጊያ በቀጠለባት በደቡብ ሱዳን የሰብዓዊ መብት ይዞታ እጅግ እያሽቆለቆለ መሄዱን የተመድ አስታወቀ ። በተለይ በሀገሪቱ ዘር ለይቶ የሚፈጸም ወሲባዊ ጥቃት መባባሱን በደቡብ ሱዳን የድርጅቱ የሰብአዊ መብቶች አጣሪ ቡድን ባለፈው ሳምንት ገልጿል ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:15
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:15 ደቂቃ

ደቡብ ሱዳን እና የተመድ አጣሪ ቡድን

ዴቼቬለ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ተንታኝ ይህን እና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲወገዱ ለደቡብ ሱዳን አዲስ ፖለቲካዊ መፍትሄ ሊፈለግ ይገባል ይላሉ ። በደቡብ ሱዳን የተመድ የሰብዓዊ መብቶች አጣሪ ቡድን ባለፈው ሳምንት እንዳስታወቀው በቀጠለው የደቡብ ሱዳን ጦርነት በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ የወሲብ ጥቃቶች ዘግናኝ ናቸው ። የቡድኑ አባላት እንዳሉት የደቡብ ሱዳን ወታደሮች በእድሜ የገፉ ሴቶችን እና ነፍሰ ጡሮችን ሳይቀር ነው የሚደፈሩት ።እንደ ቡድኑ መግለጫ በሰባት ወታደሮች የተደፈረች የአንዲት ነፍሰ ጡር ፅንስ ተጨናግፏል ። ይህን መሰሉን ከባድ ወንጀል የሚፈጽሙት ደግሞ ማናቸውም የታጠቁ ኃይሎች ናቸው ። ተፋላሚዎቹ በአንዳንድ አካባቢዎች የወሲብ ጥቃትን እንደ አንድ መሣሪያ እየተጠቀሙበት ነው ብሏል አጣሪው ቡድን። በደቡብ ሱዳን የጀርመኑ የፍሬድሪሽ ኤበርት ሽቲፍቱንግ የፕሮጀክት ሃላፊ እና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር  ሄንሪክ ማያሃክ በሀገሪቱ በተለይም በደቡባዊው ክፍል ለማጣራት አስቸጋሪ የሆኑ ልዩ ልዩ ጥቃቶች እንደሚፈጸሙ የሚያስረዱ መረጃዎች እንደሚደርሷቸው ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ አስታውቀዋል ። ለመሆኑ የተመድም ሆነ የአፍሪቃ ህብረት ቡድኖች

በሀገሪቱ የሚያካሂዷቸው ምርመራዎች ምን ፋይዳ አላቸው በተፋላሚ ወገኖችስ ላይስ ተጽእኖ ሊያሳድሩስ ይችሉ ይሆን ? ከዶቼቬለ የቀረበላቸው ጥያቄ ነበር ።ማያሃክ ሲመልሱ ፣
«ግጭቱ ተባብሶ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት ለማንኛውም የውጭ አካል ቀጥተኛ ተጽእኖ ለማድረግ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው።ሆኖም በአሁኑ ጊዜ እጅግ አስፈላጊው ነገር በደቡብ ሱዳን ሰላም ለማስፈን አዲስ ጥረት መጀመሩ ነው ። አሁን በተግባር የሰላም ስምምነት አለ ማለት አይቻልም ። የሚሊሽያዎች እና የአማጽያን ቁጥር እየጨመረ የመንግሥት ኃይሎች እርምጃም እየተጠናከረ መሄዱን ነው የምናየው ። እነዚህን ሁሉ የታጠቁ አካላትን እና ሰላማዊ ሰዎችን ወደ አንድ ጠረጴዛ የሚያመጣ አዲስ የሰላም ሂደት  ካልተጀመረ  በመካከለኛም ይሁን በረዥም ጊዜ ግጭቱን ማስቆም በጣም አስቸጋሪ ነው የሚሆነው ። »
በደቡብ ሱዳን የተመድ የሰብዓዊ መብት መርማሪ ቡድን  የደቡብ ሱዳን ጦርነት ከተጀመረበት ከ ዛሬ ሦስት ዓመት አንስቶ በርዕሰ ከተማዋ በጁባ ብቻ ከ70 በመቶ በላይ ሴቶች የወሲብ ጥቃት   እንደተፈፀመባቸው አንድ የተመድ ጥናት ማመልከቱን አስታውቋል ። በደቡብ ሱዳን ወሲባዊ ጥቃትን ለማስቆም መንግሥት ወታደሮቹ ሰብዓዊ መብት እንዲያከብሩ ቢያሳስብም ሄንሪክ

Henrik Maihack, Leiter der Friedrich Ebert Stiftung Süd Sudan (privat)

ሄንሪክ ማይሀክ

ማያሃክ እንዳሉት የሚሆነው ግን ከማሳሰቢያው በተቃራኒው ነው ።ባለፉት ሦስት ወራት ከ200 ሺህ በላይ ስደተኞች ድንበር አቋርጠው ዩጋንዳ የሚገኝ ቢዶ ቢዶ የተባለ አዲስ የተቋቋመ መጠለያ ሰፈር ገብተዋል ።ይህም የችግሩን ስፋት ያሳየናል ይላሉ ሄንሪክ ማያሃክ ። በርሳቸው አስተያየት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ዋና ዋና የሚሏቸው መሠረታዊ ጉዳዮች መከናወን አለባቸው ።
«እንደሚመስለኝ በደቡብ ሱዳን ትልቅ ሚና ያላቸው የታጠቁ እና ከዚህ ቀደም በሰላም ስምምነቱ ያልተካተቱ ወገኖች ስለ ወደፊቷ ደቡብ ሱዳን  የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት የሚያካሂዱበት የፖለቲካ ሂደት ካልተጀመረ  የምናክመው የግጭቶቹን ምልክቶች ብቻ ነው የሚሆነው ።ለዚህም ነው አዲስ የፖለቲካ አቀራረብ የሚያስፈልገው ። ለዚህም የየአካባቢው ሀገራት አስፈላጊ ናቸው ። በረዥም ጊዜ ፣ተጠያቂነትን ማረጋገጡም አስፈላጊ ነው ።በደቡብ ሱዳን ጦርነት ለተፈጸሙ ወንጀሎች እስካሁን ማንም ተጠያቂ አልተባለም ። በሀገሪቱ ያለመከሰስ መብት ያለ ነው የሚመስለው ።ስለዚህ ሊወሰዱ የሚገባቸው አንዳንድ እርምጃዎች አሉ ። ሆኖም አሁን እጅግ አስፈላጊው ፣ ለግጭቱ ፖለቲካዊ መፍትሄ ፍለጋው ላይ ማተኮር ነው ።»
 ለ10 ቀናት ደቡብ ሱዳንን የጎበኙት መርማሪዎቹ  ፣የደቡብ ሱዳን ግጭት ወደ ጎረቤት ሀገራት ኬንያ ኡጋንዳ እና ኢትዮጵያም ሊዛመት ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል ። 

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic