ደቡብ ሱዳን እና የተመድ ተልዕኮ | አፍሪቃ | DW | 13.08.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ደቡብ ሱዳን እና የተመድ ተልዕኮ

የተ.መ.ድ. የሰላም አስከባሪ ኃይል ወደ ደቡብ ሱዳን ለመላክ ውሳኔ አሳልፏል። ውሳኔው ተጨማሪ 4,000 የተ.መ. ወታደሮችን በፖለቲካዊ ምስቅልቅል ወደ ምትታመሰው ደቡብ ሱዳን ለማሰማራት ያስችላል። የፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ቃል አቀባይ አቴኒ ዌክ አቴኒ ግን አገራቸው ተጨማሪ የሰላም አስከባሪ ወታደሮችን እንደማትቀበል እንደማትተባበርም አስታውቀዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:48

ደቡብ ሱዳን

ውጊያ እና ውዝግብ በቀጠለባት በደቡብ ሱዳን የተሰማራውን የተመድ ሰላም አስከባሪ ጓድ፣ በምህፃሩ «አንሚስ» ለማጠናከር ተጨማሪ ወታደሮች ወደሀገሪቱ ይላኩ መባሉ ተቃውሞ እና ክርክር አስነስቶዋል። በርግጥ፣ ሀገሪቱን ያረጋጋል የብዙዎች ጥያቄ ነው። ሆኖም፣ በአሁኑ ወቅት ግልጽ የሆነ አንድ ጉዳይ አለ። ይኸውም፣ የተመድ የደቡብ ሱዳን ጓድ፣ በምህፃሩ «አንሚስ» ተልዕኮ ሂደት አሁን ባለበት ሁኔታ ሊቀጥል አለመቻሉ ነው።

እርግጥ፣ 12,000 ወታደሮች እና የታጠቁ ፖሊሶችን ያሰለፈው የተመድ ተልዕኮ በጦር ሰፈሩ ከ200,000 ለሚበልጡ ሲቭሎች ከለላ የሰጠበት ድርጊት በቀላሉ የማይታይ መሆኑን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ይስማማበታል። ይሁን እንጂ፣ ደቡብ ሱዳን እጎአ ሀምሌ 2011 ዓም ነፃነቷን ካገኘች ወዲህ በዚያ የተሰማራውን «አንሚስ»በሀገሪቱ፣ በተለይም በመዲናይቱ ጁባ እና አካባቢዋ በተደጋጋሚ የሚካሄደውን ውጊያ እስካሁን ማስቆም አልተሳካለትም። ግን፣ ይላሉ በደቡብ ሱዳን የጀርመናውያኑ የፖለቲካ ጥናት ቡድን « ፍሪድሪኽ ኤበርት ተቋም» ዋና ስራ አስኪያጅ ሄንሪክ ማይሀክ ፣ ከ«አንሚስ» ብዙ መጠየቅ ትክክለኛ አይደለም።

« 12,000 ወታደሮች እና የታጠቁ ፖሊሶችን ያሰለፈ ሰላም አስከባሪ ጓድ በቆዳ ስፋትዋ ከፈረንሳይ በማታንሰዋ ትልቅ ሀገር ውስጥ ብዙ ለውጥ ያስገኛል ብሎ መጠበቁ ከገሀዱ የራቀ ምኞት ነው። ምክንያቱም ደቡብ ሱዳን በአካባቢው ካሉት ሀገራት መካከል በጣም ብዙ የታጠቁ ቡድኖች የሚንቀሳቀሱባት ሀገር ናት። »

ያካባቢውን ሁኔታ በቅርብ የሚከታተሉ አንዳንዶች ታዛቢዎች፣ ጓዱ የሚጠበቅበትን ለማሟላት የሚያስፈልገው በቂ ስልጣን እንደሌለው ነው የሚመለክቱት። ይሁንና፣ ብዙዎቹ የሱዳን አጥኚዎች ይህ እንደ መከራከሪያ የሚቀርበው ሀሳብ ያን ያህል አሳማኝ ሆኖ እንዳላገኙት በደቡብ ሱዳን ጊዚያዊ ሁኔታ ላይ የጀርመናውያኑን ግብረ ሰናይ ድርጅት፣ «ብሮት ፊውር ዲ ቤልት» አማካሪ የሆኑት ወይዘሮ ማሪና ፔተር ገልጸዋል።

« እኔ በግሌ «አንሚስ» አሁንም ጠንካራ ስልጣን አለው ብዬ ነው የማስበው። ለምሳሌ፣ በ«አንሚስ» ስር የተሰማሩት ሰላም አስከባሪዎች፣ አሁንም እንኳን የሲቭሉን ሕዝብ ደህንነት መከላከል የሚያስችላቸው ስልጣን አላቸው። ግን ራሳችንን መጠየቅ ያለብን «አንሚስ» በቂ ሰላም አስከባሪዎች አሉት ወይ? እነዚህ ሰላም አስከባሪዎችስ የራሳቸው የተቀናቃኝ ወገኖች የሚያካሂዱት ውጊያ ሰላባ መሆን ብዙም የማያስጨንቃቸው ደፋሮች ናቸው ወይ? ይህ ነው ለኔ ትልቁ ጥያቄ። »

ይኸው የብዙዎች ጥያቄ የሚያሳየው በደቡብ ሱዳን ባፋጣኝ መረጋጋት ለማስገኘት ተጨማሪ ሰላም አስከባሪዎች ማሰማራት አስፈላጊ መሆኑን ነው። ለተመድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ሰሞኑን ዩኤስ አሜሪካ ያቀረበችው ረቂቅ ውሳኔ በደቡብ ሱዳን በ«አንሚስ» እዝ ስር የሚውል ጓዱን የሚያጠናክር ከአካባቢ ሀገራት የሚውጣጡ ተጨማሪ 4,000 ወታደሮችን የሚያጠቃልል የጦር ብርጌድ እንዲሰማራ ጠይቆዋል። ፈጣን ርምጃ ወሳጁ ተከላካይ ብርጌድ የሀገሪቱን መዲና ጁባን ፀጥታ የማረጋጋት እና በዚያ በተሰማራው የተመድ ተልዕኮ፣ በምህፃሩ «አንሚስ» ጦር ሰፈሮች ላይ የሚጣሉ ጥቃቶችን የማከላከል ስልጣን እንዲኖረው ነው የሚፈለገው።

የጦሩ ብርጌድ ተልዕኮውን በጁባ ብቻ ያድርግ መባሉን ማሪና ፔተርስ እንደ ትልቅ ስህተት ተመልክተውታል።

« ትኩረታችንን በጁባ ላይ ብቻ ማሳረፍ አይገባንም። ምክንያቱም ውጊያው በዚች ትልቅ ሀገር ውስጥ ተስፋፍቶዋል። እና በደቡብ ሱዳን የቀጠለውን ውጊያበጠቅላላ በዓለም ትልቅ የሚባል ሰላም አስከባሪ ጓድ በማሰማራት ለማብቃት አትችልም። ለውዝግብ መፍትሔው ከሀገር ውስጥ መምጣት አለበት። »

ሄንሪክ ማይሀክም ወደ ደቡብ ሱዳን ተጨማሪ ጦር የመላኩ ጥያቄ ብቻ አይደለም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ትልቅ ተግዳሮት የሆነው። ሰላም አስከባሪዎቹ ወታደሮች እና የታጠቁት ፖሊሶችም ስልጣናቸውን፣ እንዲሁም፣ መብት እና ግዴታቸውን በቅጡ አለማወቃቸውም ሌላ ችግር ፈጥሮዋል።

« በሰላም አስከባሪዎቹ ዘንድ፣ አዘውትሮ እንደሚታየው፣ የአቅም እጥረት እና ስልጣናቸውን በተመለከተ የግልጽ መረጃ ጉድለት አለ። በጎርጎሪያዊው 2016 ዓም መጀመሪያ ላይ በማላካል በተቀናቃኝ ቡድኖች መካከል ግጭት በተፈጠረበት እና በዚያ በሚገኘው የተመድ መጠለያ ጣቢያ ላይ ጥቃት በተጣለበት ጊዜ የ«አንሚስ» ወታደሮች ጣልቃ ገብተው ግድያውን እስኪያስቆሙ ድረስ ብዙ ጊዜ ነበር የወሰደባቸው። ከግጭቱ በኋላ የተካሄዱት ምርመራዎች ሰላም አስከባሪዎቹ ወታደሮች በንዲህ ዓይነት ጊዜ ምን ማድረግ እንደሚፈቀድላቸው እና እንደማይፈቀድላቸው በትክክል ባለማወቃቸው በጽሑፍ ግልጽ አድርገዋል። »

የደቡብ ሱዳን የሽግግር ብሔራዊ አንድነት መንግሥት የዩኤስ ረቂቅ ውሳኔ የሀገሩን የግዛት ሉዓላዊነት የሚሸረሽር እና ሀገሪቱንም እንደገና ወደ ቅኝ አገዛዝ የምትመለስበትን ስጋት የሚደቅን ነው፣ ማለትም፣ የተመድ ሀገሪቱን እንዲያስተዳድር ስልጣን የሚሰጥ ነው በሚል ውድቅ አድርጎታል። እንደተሰማው፣ በደቡብ ሱዳን ውጊያው እንደገና ካገረሸ በኋላ አንድ የቀድሞ የዩኤስ አሜሪካ ልዩ ልዑክ የተመድ እና የአፍሪቃ ህብረት ደቡብ ሱዳንን በጋራ እንዲያስተዳድሩ ባለፈው ወር ሀሳብ ሰንዝረዋል። የደቡብ ሱዳን መንግሥት ሀሳቡን ውድቅ ካደረገች በኋላ የምክር ቤቱ ቤት ዲፕሎማቶች በደቡብ ሱዳን ተጨማሪ 4,000 ወታደሮች እንዲሰማሩ ቀደም ሲል ዩኤስ አሜሪካ ያቀረበችው ረቂቅ ውሳኔ ላይ ማሻሻያ አድርገው የጓዱን ተልዕኮ ለመጀመሪያ በአራት ወራት ለመገደብ መወሰናቸውን ገልጸዋል። በማሻሻያው መሰረት ይሰማራ የተባለው ጓድ ደቡብ ሱዳንን ለቆ የሚወጣበት ግልጽ እቅድም እንደሚኖር እና ከሀገሪቱ መንግሥትም ጋር ባንድነት እንደሚሰራ አመልክተዋል።

ከአካባቢ ሀገራት የሚውጣጣው የጦር ብርጌድ የሀገሪቱን መዲና ጁባን ፀጥታ እንዲያረጋጋ እና በዚያ በተሰማራው የተመድ ተልዕኮ፣ በምህፃሩ «አንሚስ» ላይ የሚጣሉ ጥቃቶችን እንዲያከላክል ታስቦዋል። የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ ዩኤስ አሜሪካ ባቀረበችው ረቂቅ ውሳኔ ላይ የፊታችን ዓርብ ሊሰጥበት እንደሚችል ተገልጾዋል። ከአካባቢ ሀገራት የሚውጣጡት እና በዚያ የተሰማራውን በምህፃሩ «አንሚስ» በተባለው የተመድ ሰላም አስከባሪ ጓድ እዝ ስር እንዲውል የታሰበው ጓድ ስምሪት እክል ከገጠመውም ምክር ቤቱ ከአንድ ወር በኋላ በደቡብ ሱዳን ላይ የጦር መሳሪያ ማዕቀብ እንዲጣል ጥሪ አስተላልፎዋል። የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ማዕቀብ እንደሚጥል ዛቻ ሲያሰማ ባለፉት 18 ወራት ውስጥ ማዕቀብ እንደሚጥል በተደጋጋሚ ዛቻ ቢያሰማም፣ እስካሁን ዛቻውን ተግባራዊ አላደረገም። ይህ ዓይነቱ ማዕቀብ የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ወገኖችን የሚጎዳ ሲሆን፣ በተለይ ፣ በከባድ የጦር መሳሪያ እና በተዋጊ አይሮፕላኖች በሚጠቀመው የመንግሥቱ ጦር ላይ የሚያሳርፈው ተፅዕኖ ከፍተኛ እንደሚሆን ተንታኞች ገልጸዋል።

አርያም ተክሌ

እሸቴ በቀለ

Audios and videos on the topic