ደቡብ ሱዳን በ6 ወራት ውስጥ | አፍሪቃ | DW | 11.05.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ደቡብ ሱዳን በ6 ወራት ውስጥ

የደቡብ ሱዳን ተፋላሚዎች ከዚህ ቀደም የተፈራረሙትን ሥምምነት ከዚሕ ቀደም በቆረጡት ጊዜ ገቢር ማድረግ ስላልቻሉ ተጨማሪ 6 ወር ተሰጥቷቸዋል። በድጋሚ በተሰጣቸው ቀነ-ገደብ ግን የደቡብ ሱዳን መንግሥት ከተቃዋሚዎች ጋር የተስማማውን መተግበር ግድ ይለዋል። ያን እንዲያደርግ ዩናይትድ ስቴትስ አጥብቃ ትሻለች። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 05:10

«6 ወሩን ጥበብ በተሞላበት መንገድና በንቃት ይጠቀሙበት»

በደቡብ ሱዳን የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሀገራቸው የደቡብ ሱዳን ተፋላሚዎች ቀደም ሲል የተስማሙበትን የሰላም ውል ከእንግዲህ አንዳችም ሳይዘገይ ገቢራዊ እንዲያደርጉ ትሻለች። ጊዜው «እየበረረ ነው» ይላሉ አምባሳደር ቶማስ ሁሽክ ስለ ደቡብ ሱዳን ተፋላሚዎች የሰላም ስምምነት ተግባራዊነት ሲያወሩ። የደቡብ ሱዳን ተፋላሚዎች በመስከረም ወር የደረሱበትን ስምምነት ያለአንዳች ማቅማማት ሙሉ ለሙሉ ገቢራዊ እንዲያደርጉ ሀገራቸው ዩናይትድ ስቴትስ አጥብቃ ትሻለች።

የደቡብ ሱዳን ተፋላሚዎች የብሔራዊ አንድነት መንግሥት ለመመሥረት እንደ ጎርጎሪዮሱ አቆጣጠር ለግንቦት 12 (ነገ ማለት ነዉ) የያዙት ቀጠሮ በስድስት ወራት እንዲራዘም የወሰኑት ባለፈዉ ሳምንት ዓርብ፤ አዲስ አበባ ውስጥ ባደረጉት ስብሰባ ነበር። በደቡብ ሱዳን ዋነኛ የተቀናቃኞች መሪ ሪያክ ማቻር ጥያቄ የተራዘመውን ቀነ-ገደብ የምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግስታት (IGAD) ማክሰኞ ዕለት ዕውቅና ሰጥቶታል።

አምባሳደር ቶማስ ሁሼክ በተለይ ከዶይቸ ቬለ (DW) ጋር ባደረጉት ቃለ-መጠይቅ የጊዜው መራዘም በደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ኃይላት ስምምነት ስለተደረሰበት ደስተኛነታቸውን ገልጠዋል። ኾኖም ሀገራቸው ዩናይትድ ስቴትስ ስምምነቱ ገቢራዊ የሚሆንበትን ተጨባጭ ነገር ማየት ትሻለች።

«ስድስት ወሩን ጥበብ በተሞላበት መንገድ እና በንቃት ይጠቀሙበት። በሽግግር ጊዜው መሠራት የሚገባቸውን ቀሪ ተግባራትን በመላ ያሳኩ። እንደውም ከዚያ ባሻገር ያስቡ።»

የደቡብ ሱዳን ተፋላሚዎች በተስማሙበት መሠረት ሥልጣን ተጋርተው የጋራ መንግሥት እስኪመሰረት ድረስ ጦራቸውን አረጋግተው ሒደቱ መጀመሩን በነገው ዕለት ማወጅ ነበረባቸው። ያ ሳይሳካ ሌላ ቀነ-ገደብ ተሰጥቷል። አምባሳደር ቶማስ ቀነ-ገደቡ መራዘሙ በሰላም ስምምነቱ ወቅት የተነደፉ የጊዜ ሠሌዳዎች ላይ አንዳችም ተጽዕኖ ማሳረፍ የለበትም ባይ ናቸዉ።

«ገና ከመነሻው ግልጽ አድርገናል። ምናልባት የሽግግር መንግሥት ምሥረታ ጊዜውን ስለማራዘም ቢያሰላስሉ እንኳ፤ በሽግግሩ ማክተሚያ ላይ በሚኖረው ምርጫ በምንም መልኩ ተጽዕኖ ማሳረፍ እንደማይገባው አስገንዝበናል።»

በስምምነቱ መሠረት ተፋላሚ ኃይላቱ ጦራቸውን ወደየጦር ሠፈሮች ማስገባት ይጠበቅባቸዋል። የተለያዩ ኃይላትንም አዋሕደው የጋራ ሥልጠና ሊሰጡ ይገባል። ከሌሎች ጉዳዮች ደግሞ ለአብነት ያህል እርስ በእርስ መተማመንን ማጎልበቱ እና ከባላንጣነት ራስን ማቀቡ ላይ የሰላም ስምምነቱ ፈራሚዎቹ ያሳኳቸው እጅግ ጥቂቶቹን ነው።

ተፋላሚ ኃይላቱ ያንን ላለማድረግ የገንዘብ ድጋፍ እጥረትን እንደ ዋነኛ ተግዳሮት አድርገው ያማርራሉ። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለዚያ እጁን እንዲዘረጋ ተደጋጋሚ ተማጽኖዖችን አሰምተዋል። የደቡብ ሱዳን መንግሥት ተወካዮች ለሒደቱ የሚውል 100 ሚሊዮን ዶላር መንግሥታቸው ለማቅረብ ተዘጋጅተል ሲሉ ቃል መግባታቸው ለጋሽ ሃገራት ቊጣቸው ረገብ እንዲል አድርጓል። ለጋሽ ሃገራቱ የደቡብ ሱዳን መንግሥት ለሰላም ሒደቱ ገንዘብ ለምንድን ነው የማያወጣው ሲሉ ሲወቅሱ ከርመዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት በዲፕሎማሲው ረገድ ብሎም ተፋላሚ ኃይላቱ የፈረሙት ስምምነት ተግባራዊነቱ እንዲረጋገጥ ላቅ ያለ ሚና ተጫውቷል። እስካሁን ድረስም ደቡብ ሱዳን ከፍተኛ የሚባል የርዳታ ገንዘብ አግኝታለች። አምባሳደር ቶማስ ሁሼክ መንግሥታቸው ከአሁን በኋላ በደቡብ ሱዳን ርዳታ የሚያደርገው በሰብአዊ ጉዳዮች እና ተፋላሚ ኃይላቱ የሰላም ስምምነቱን ገቢራዊ ማድረጋቸውን ለመቆጣጠሪያ ነው ብለዋል።

«ጦሩ የጸጥታ ክፍሉን ዳግም ለማዋቀር እና በተለይ የጦር ኃይላትን ወደየ ጦር ሠፈሮች ለመመለስ የሚደረገውን የቀጥታ ድጋፍ በተመለከተ ለጦሩ ከእንግዲህ ድጋፍ አናደርግም። ከገደብ ያለፈ ነው። ምክንያቱም፦ ይኸው ጦር ነው እኮ ባለፉት አምስት ዓመታት በሰላማዊ ዜጎች ላይ ጦርነት ሲያከናውን የነበረው። ስለዚህ ያን አንረዳም።»

ኾኖም ግን ቶማስ ሁሼክ የሰላም ስምምነቱን ሒደት በቅጡ ለማስኬድ ይቻል ዘንድ የደቡብ ሱዳን መንግስት ቃል የገባውን 100 ሚሊዮን ዶላር ፈሰስ ሲያደርግ ዩናይትድ ስቴትስ ማየት እንደምትሻ አስገንዝበዋል። ዩናይትድ ስቴትስ በገንዘብ እጥረትም ኾነ በሌላ ምክንያት የሰላም ሒደቱ ከእንግዲህ ተሰናክሎ ማየት አትፈልግም።

«በዚህም አለ በዚያ በተለይ የሰላም ሒደቱን ለማሰናከል መሞከር ሕጋዊ አይደለም፤ እኛም ኾንን ሌሎች በዚያ ጉዳይ ላይ ጥብቅ አቋም ነው ያለን።»

ደቡብ ሱዳን እንደ ጎርጎሪዮሱ አቆጣጠር ከ2013 ዓ.ም ታኅሳሥ ወር አንስቶ በእርስ በእርስ ጦርነት ተዘፍቃለች። የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ኃይላት የሰላም ስምምነቱን አኹን በተራዘመላቸው ቀነ-ገደብ ገቢራዊ ያድርጉ አለያም ዳግመኛ ቀነ-ቀጠሮ ይራዘምልን በማለት አቤት ይበሉ ለማወቅ ከእንግዲህ የመንፈቅ ጊዜ አለ።  

ማንተጋፍቶት ስለሺ  

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic