ደቡብ ሱዳንና ድንበር አያግዴው የሃኪሞች ድርጅት | አፍሪቃ | DW | 28.02.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ደቡብ ሱዳንና ድንበር አያግዴው የሃኪሞች ድርጅት

ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት (HRW) ደቡብ ሱዳን ውስጥ ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች የጦር ወንጀል በመፈጸም ላይ ናቸው ሲል አጋለጠ። በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር በሚመራው የደቡብ ሱዳን መንግሥት ወታደሮችና ፣ የቀድሞው ምክትል ፕሬዚዳንት ሪኤክ

ማቻር ታማኞች በሆኑ አማጽያን መካከል ባለፉት ሳምንታት፣ ጭካኔ የተመላበት ግድያ ሲካሄድ መሰንበቱን፤

ከ 2 ወር በላይ በሆነው ውጊያም በሺ የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ ቁጥራቸው ወደ 900 ሺ የሚጠጋ የደቡብ ሱዳን ተወላጆች ከቀየአቸው መፈናቀላቸው ነው የተነገረው። የደቡብ ሱዳን ህዝብ ይዞታ እጅግ የሚያስስብ መሆኑንም ድንበር አያግዴው ዓለም አቀፍ የሀኪሞች ድርጅት ገልጿል።

በደቡብ ሱዳን ፤ ታኅሣሥ 6 ቀን 2006 ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር በቀድሞው ምክትላቸው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከታራ ተቃጣብኝ ካሉበት ጊዜ አንስቶ ፣ በብዛት ረገድ ፣ አንደኛና ሁለተኛ የሆኑት የዲንካና ኑዔር ብሔሮች አባላት በተለይ መሣሪያ የታጠቁት ወገን ለይተው በሚያካሂዱት ውጊያ ፣ በሺ የሚቆጠር ህዝብ ከመገደሉም ፣ በሰፊው የሲቭሎችን ንብረት መመዝበራቸውና የእርዳታ ጣቢያዎችን መገልገያዎች መዝረፋቸው፣ ሲቭሎችን ሆን ብለው ዒላማ ማድረጋቸው ፤ አንዱ የሌላውን ጎሣ አባላት በጅምላ የረሸነበት ሁኔታ መኖሩንም HRW ገልጿል። ከዚያው ከደቡብ ሱዳን የተመለሱት ፣ ዓለም አቀፉ ድንበር አያግዴ የሀኪሞች ድርጅት ባልደረባ Heather Pagano በተለይ ማላካል አካባቢ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ እንዲህ ነው የገለጡት።

«አሁን ነው ከደቡብ ሱዳን የተመለስሁ፤ በዚያው ያለው ሰብአዊ ይዞታ አንገሽጋሽ ነው። በኒያርና ማላካል ዘግናኝ ሁኔታ ነው ያየነው። እጅግ የሚያስደነግጥ ዘረፋና ጥቃት ነው ደቡብ ሱዳን ውስጥ በተቋማትና መገልገያ ጣቢያዎች ላይ የተፈጸመው።

በማላከል ከተማ በቅርቡ በተካሄደው ውጊያ፣ ዘግናኝ ሁኔታ ነው የተመለከትን። ቤቶች በከፊል ተቃጥለው፤ የተገደሉ ሰዎች ፤ አስከሬናቸው ጎዳና ላይ ሳይነሣ ይታይ ነበር።

የእኛ ቡድን፣ ወደ ማላካል ትምህርት ወደ ሚሰጥበት ሆስፒታል በመጓዝ፣ ጀርባቸውን በጥይት የተመቱ ህሙማንን አግኝቷል።በ UNITY STATE አቅራቢያ በምትገኘው ከተማ ፣ ኒያር፣ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ሰዎች ተጨናንቀው ሕይወት መደገፊያ የህክምና መሣሪያም ሆነ አቅርቦት ሳያገኙ፤ እንዲሁ ነው ያገኘናቸው። ምክንያት ሆስፒታሉ ሙሉ-በሙሉ ስለተቃጠለ ነው። ከተማው ሰው ለቆት ባዶውን ቀርቷል። ሰው ወደ ጫካ በመሸሽ በዚያ በሚያሳዝን ሁኔታ ነው የሚገኘው። በአሁኑ ጊዜ የደቡብ ሱዳን ተጨባጭ ሁኔታ እጅግ የሚያሳስብ ነው።»

ለሀኪሞችና ፣ ለህክምና አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች ደንታቢስነቱ የውጊያውን አስከፊነት ነው የሚያመላክተው። ሆስፒታል ድምጥማጡ እንዲጠፋ እንዲቃጠል በተደረገበት አካባቢ የድንበር አያግዴው የሀኪሞች ድርጅት ፤ የተጎዱትንና ህክምና የሚያሻቸውን ሰዎች እንዴትና በምን አቅሙ በመርዳት ላይ እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ ፓጋኖ ሲመልሱ---

«ጥሩ ጥያቄ ነው። 240 የድርጅቱ አባላት ፣ከህዝቡ ጋር በጫካ ተደብቀው ነው የሚገኙት። ሠፈራቸውን ለቀው ሲሄዱም በመንገድ ታመው ነበር። በዚያ ጫካም ሆነው ሕሙማንን ለማግኘት እየጣሩ ነው። አቅርቦቱ ተሟጦባቸዋል። የቆሰለ አካልን የሚጠቀልሉበትን ጨርቅም ፣ እንደገና መልሰው እስከመጠቀም ነው የደረሱት።

የወባ መከላከያ አጎበር የላቸውም። በቂ ምግብና ንፁህ የሚጠጣ ውሃም የለም። በእርግጥ አሳዛኝ ሁኔታ ነው።»

ህዝቡ ቁሻሻ ውሃ በመጠጣት ለህመም መዳረጉን፤ በምግብ እጦትም ማንኛውንም የዱር ቅጠላ ቅጠል እስከመብላት መገደዱንም ነው ሂዘዘር ፓጋኖ የገለጡት፤ የፀጥታ ይዞታው ካልተሻሻለ ፤ ወደፊት ምን ማድረግ እንደሚችሉም ተጠይቀው ፣ መልሱ የሚገኘው በተፋላሚዎቹ በጎ ፈቀድ ብቻ መሆኑን ነው የጠቆሙት።

«የምንመለስበትንና ተገቢውን አገልግሎት መስጠት የምንችልበትን ሁኔታ እዚህ ላይ መናገሩ በጣም አስቸጋሪ ነው። ደቡብ ሱዳም ውስጥ 25 ዓመታት አገልግሎት ስንሰጥበት የነበረው ሆስፒታል ሙሉ በሙሉ ተቃጥሏል። ያሁን እንጂ፣ ከተፋላሚዎቹ ወገኖች በመላ ለደኅንነታችን ዋስትና ማግኘት ይኖርብናል። ይህ ይቻላል፣ አይቻልም፣ በዚህ ቅጽበት ይህ ነው ብሎ ለመናገር አዳጋች ነው። »

ደቡብ ሱዳን ውስጥ በሲቭሎች ላይ የሚወሰደው የኃይል እርምጃና የማውደም ተግባር ዘግናኝ መሆኑን ያስታወቀው HRW ፣ ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች፤ የግፍ ተግባር መፈጸማቸውን እንዲያቆሙና ፤ የፈጸሙት ወገኖችም በኃላፊነት እንዲጠየቁ አስስቧል።

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic