ደማስቆ፤ የሶሪያ የአየር ድብደባ | ዓለም | DW | 14.11.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ደማስቆ፤ የሶሪያ የአየር ድብደባ

የሶሪያ መንግሥት ጦር የአማፅያን ይዞታዎችን ዛሬ በታንክና በጦር አውሮፕላኖች ደበደበ ። የሶሪያ ታንኮች መዲናይቱ ደማስቆ የሚገኙ ሁለት የስደተኞች መጠለያዎችን ማጥቃታቸውን የሶሪያ የሰብአዊ መብቶች ታዛቢ ድርጅት አስታውቋል ።

የሶሪያ የጦር አውሮፕላኖችም ባለፈው ወር በአማፅያን ይዞታ ስር የወደቀውን ሰሜን ምዕራባዊውን ከተማ ማሬት አልኑማንን መደብደባቸውንም ድርጅቱ ዘግቧል ። በሌላ በኩል ፈረንሳይ ለሶሪያ መንግሥት ተቃዋሚ ቡድን እውቅና መስጠቷን ሶሪያ የጦርነት እወጃ ስትል አወገዘች ። ፈረንሳይ ቃትር ዶሃ ውስጥ ለተመሰረተው ለአዲሱ የተቃዋሚዎች ህብረት እውቅና በመስጠት የመጀመሪያዋ ምዕራባዊት ሃገር ናት ። የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ፍርንሷ ኦሎንድ ፓሪስ ለተቃዋሚዎቹ ህብረት እውቅና የሰጠችው እንደ ብቸኛው የሶሪያ ህዝብ ተወካይና የዲሞክራሲያዊት ሶሪያ የወደፊቱ ጊዜያዊ መንግሥት መሆኑን ተናግረዋል ። አማፅያኑን ማስታጠቅን በተመለከተም ወደፊት ለተቃዋሚዎች እውቅና ከሚሰጡ ሃገራት ጋር የሚታይ ነው ብለዋል የሶሪያ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የዶሃውን ጉባኤ ጦርነት እወጃ ነው ፤ ተቃዋሚዎችም በተባበሩት መንግሥታት አሰራር ችግሩን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የማይፈልጉ ናቸው ብለዋቸዋል ።

ፈረንሳይም ለተቃዋሚው ብሄራዊ ህብረት እውቅና በመስጠት ገዳዮችንና ፣ አሸባሪዎችን በመደገፍ የሶሪያን ጥፋት ታበረታታለች ሲሉ ነቅፈዋል ። ፈረንሳይ ለተቃዋሚው ህብረት እውቅና ከሰጠች በኋላ ሩስያ ከተቃዋሚዎች ጎን የሚቆሙ ወገኖችን ተችታለች ። ሞስኮ በሶሪያ ጉዳይ በገልለተኛ አቋሟ እንደምትፀና ነው የተናገረችው ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በጦርነት ሰበብ የሚሰደዱት ሶርያውያን ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እያደገ ነው ። የሶሪያ ግጭት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ከሶሪያ የተሰደደው ህዝብ ቁጥር ወደ 700 ሺህ ይገመታል ። ከመካከላቸው አብዛኛዎቹ ሃገራቸውን ለቀው የወጡት ባዶ እጃቸውን ነው ። በዚህ የተነሳም ለችግር መዳረጋቸውን አንድ ግብፅ ውስጥ የተጠለሉ ሶሪያዊት ይናገራሉ ።
«ጦርነቱን ሸሽተን ነው የመጣነው ። ምንም ይዘን መውጣት አልቻልንም ። ለክረምቱ የሚሆን ልብስ አልያዝንም። »
ከሶሪያ ስደተኞች 300 ሺ የሚሆኑት ቱርክ ይገኛሉ ።