ዜና | DW
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዜና | 17.11.2018 | 00:00

አዲስ አበባ፤ በሙስና የተጠረጠሩ ባለሀብት ታሰሩ

ከብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የሙስና ክስ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ አንድ ባለሀብት ዛሬ በቁጥጥር ስር ዋሉ። ለመንግስት ቅርበት ያለው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደዘገበው አቶ ዓለም ፍጹም ገብረስላሴ የተባሉት ባለሀብት የታሰሩት የእርሳቸው የነበረን ሆቴል በተጋነነ ዋጋ ለሜቴክ ሸጠዋል በመባል ነው።ፋና ጠቅላይ አቃቤ ህግን ጠቅሶ እንደዘገበው ተጠርጣሪው ባለሀብት ከሜቴክ የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር ጋር የነበራቸውን ጥሩ ግንኙነት በመጠቀም ሪቬራ የተሰኘውን ሆቴል እጅግ በተጋነነ ዋጋ 128 ሚሊየን ብር ሸጠዋል። በባንክ ዕዳ ተይዞ ነበር የተባለው ሪቬራ ሆቴል ሲሸጥ ሜቴክ ዕዳውን እንዲሸፍን መደረጉንም በዘገባው ተጠቁሟል። ሜቴክ አሁን ጥያቄ የተነሳበትን ሆቴል ለመግዛት ከስምምነት ላይ የደረሰው የዛሬ ስድስት ዓመት ገደማ ነበር። ሆቴሉ አብዛኛው ድርሻው የአቶ ዓለም በሆነው ሪቬራ ኢንተርናሽናል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ስር ይተዳደር የነበረ ሲሆን ሜቴክ ሆቴሉን የገዛው ለሚያከናውናቸው ፕሮጀክቶች በየጊዜው ከውጭ የሚያመጣቸውን እንግዶች ለማሳረፍ በሚል ነበር። በዚህ ክስ ስማቸው የተነሳው የሜቴክ የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄነራል ክንፈ ዳኘው በሳምንቱ መጀመሪያ በቁጥጥር ስር ውለው ፍርድ ቤት መቅረባቸው ይታወሳል። ዛሬ የታሰሩት ባለሀብት አቶ ዓለም ፍጹም የዓለም ገነት ቆርቆሮ ፋብሪካ እና በግንባታ ላይ ያለው ፎር ፖይንት ሸራተን ሆቴል ባለቤት መሆናቸውንም የፋና ዘገባ ጨምሮ ገልጿል።

በደቡብ ክልል 25 ኤርትራውያን በቁጥጥር ስር ዋሉ

በደቡብ ክልል ኢትዮጵያን ከኬንያ ጋር የሚያዋስነውን ድንበር በህገ ወጥ መንገድ ሊሻገሩ ነበር የተባሉ 25 ኤርትራውያንን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የክልሉ ፖሊስ አስታወቀ። ወጣቶቹ በኬንያ አቋርጠው ኡጋንዳ የመግባት እቅድ እንደነበራቸው ፖሊስ ገልጿል። ኤርትራውያኑ ሐሙስ ዕለት የተያዙት በክልሉ በደቡብ ኦሞ ዞን፤ ሐመር ወረዳ ውስጥ ቱርሚ በተባለች አነስተኛ የጠረፍ ከተማ ላይ መሆኑን የዞኑ ፖሊስ ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ካሳ ካውዛ ዛሬ ለDW ተናግረዋል፡፡ ኤርትራውያኑ በወጣትነት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን ኃላፊው ገልጸዋል። “የተያዙበት ምክንያት ባልተለመደ ሁኔታ ወደዚያ በህዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ከደረሱ በኋላ ከምሽቱ ሶስት ሰዓት ላይ ወደ ጭነት መኪና ተዛውረው ሊጓዙ ሲሉ በፖሊስ ጥርጣሬ ተይዘዋል። ሲታዩ ያው በኬንያ በኩል ወደ ኡጋንዳ ካምፓላ መድረስ እንፈልጋለን የሚሉ ወጣቶች ነበሩ። ወጣቶቹ እነርሱ እንደሚሉት የኤርትራ ዜጎች ነን ነው። በእጃቸው ላይ የያዙት አንዳንድ መታወቂያዎችም ከኤርትራ ትምህርት ቤት የተነሱ መሆኑን የሚያሳዩ ናቸው። አሁን ወደ ዞናችን ፖሊስ መምሪያ አስመጥተን ወጣቶቹን በዚያው በዞናችን ፖሊስ መምሪያ ግቢ ውስጥ ይገኛሉ” ሲሉ የዞኑ የፖሊስ ኃላፊ ወጣቶቹ እንዴት ሊያዙ እንደቻሉ አስረድተዋል። ዋና ኢንስፔክተር ካሳ ወጣቶቹን በተመለከተ በቀጣይነት ምን ማድረግ እንዳለባቸው ከክልሉ መንግስት ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የኤርትራ ኤምባሲ እስከአሁን በፖሊስ እጅ በሚገኙት ኤርትራዊያን ጉዳይ  ላይ ያለው ነገር አለመኖሩን የሐዋሳው ወኪላችን ሸዋንግዛው ወጋየሁ ያደረሰን ዘገባ ያመለክታል፡፡

አዲስ አበባ ፤ የአፍሪካ ህብረት ማሻሻያ አንገብጋቢ ነው: ካጋሜ

የአፍሪካ ህብረትን የማሻሻል ጉዳይ “አንገብጋቢ ነው” ሲሉ የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ አሳሰቡ። የአፍሪካ መሪዎች በህብረቱ ማሻሻያ ላይ ከስምምነት እንዲደርሱም ጠይቀዋል። ፕሬዝዳንት ካጋሜ ይህን የተናገሩት ዛሬ በአዲስ አበባ በተጀመረው 11ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች አስቸኳይ ጉባኤ ላይ ነው። ጉባኤው በዋነኛነት ትኩረት የሚሰጥበት ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲንከባለል የቆየውን እና ብዙ ያከራከረው የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽንን የማሻሻል ጉዳይ እንደሆነ ተነግሯል። የማሻሻያ ዕቅዱን በበላይነት ሲመሩ የቆዩት ካጋሜ “በአህጉራችን እና በመላው ዓለም የሚከሰቱ ሁነቶች የእዚህን ፕሮጀክት አስፈላጊነት እና አንገብጋቢነት ማረጋገጣቸውን ቀጥለዋል” ብለዋል። የማሻሻያውን ግብ “ቀላል” ሲሉ የጠሩት ካጋሜ እርሱም “አፍሪካን ጠንካራ ማድረግ እና ለህዝቦቻችን የሚመጥናቸውን መጪ ጊዜ መስጠት ነው” ብለዋል። በሩዋንዳው ፕሬዝዳንትነት የተያዘውን የአፍሪካ ህብረት ተዘዋዋሪ የሊቀመንበርነት ስልጣን በመጪው ጥር ወር የምትረከበው ግብጽ ለማሻሻያው እምብዛም ፍላጎት አለማሳየቷ እያነጋገረ ይገኛል። የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ያነጋገራቸው አንድ የአፍሪካ ህብረት ኃላፊ ግን አለ የሚባለውን የግብጽ ተቃውሞ አጣጥለዋል። “እኔ እንደማስበው በዚህ ጉዳይ ላይ መቶ በመቶ ስምምነት አለን” ያሉት ኃላፊው በስብሰባው መጠናቀቂያ ስምምነት ላይ እንደሚደረስ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ዱባይ፤ ኢራን እና ኢራቅ የንግድ ትብብራቸውን ለማሳደግ ተስማሙ

ኢራን እና ኢራቅ የሁለትዮሽ የንግድ ግንኙነታቸውን አሁን ካለበት 12 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ መጠን ወደ 20 ቢሊዮን ዶላር ለማሳደግ ሀሳብ እንዳላቸው የኢራኑ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሮሃኒ ገለጹ። ፕሬዝዳንት ሮሃኒ ይህን የተናገሩት ከኢራቁ መሪ ባህራም ሳሊህ ጋር ዛሬ ከተገናኙ በኋላ ነው። የኢራቁ ፕሬዝዳንት ወደ ኢራን የተጓዙት አሜሪካ በኢራን ላይ የጣለችውን የኢኮኖሚ ማዕቀብ ባደሰች በሁለተኛው ሳምንት መሆኑ ትኩረትን ስቧል። አሜሪካ በኢራን የነዳጅ ኢንዱስትሪ፣ በባንክ እና ትራንስፖርት ዘርፍ ላይ ማዕቀብ ብትጥልም ኢራቅ ግን ከጎረቤቷ ጋዝ እና የኃይል አቅርቦቶችን አሁንም ማስገባት ትፈልጋለች። የኢራን እና ኢራቅ ፕሬዝዳንቶች በዛሬው ውይይታቸው በኤሌክትሪክ ኃይል፣ ጋዝ፣ የነዳጅ ውጤቶች እንደዚሁም በነዳጅ ዘይት ፍለጋ እና ማውጣት ዘርፎች መነጋገራቸውን ሮሃኒ ተናግረዋል። ኢራቅ ለአንድ ወቅት ባላንጣዋ ኢራን የምግብ ምርቶችን በማቅረብ ለኃይል ማመንጫ ጣቢያዎቿ ማንቀሳቀሻ የሚሆን ጋዝ በምትኩ ለመቀበል የአሜሪካንን ፍቃድ ማግኘት እንደሚያስፈልጋት ሮይተርስ ዘግቧል። ተግዳሮቱ የታያቸው የሚመስሉት የኢራቁ ፕሬዝዳንት በሀገራቸው እና ኢራን ድንበር ላይ ነጻ የንግድ ቀጠና መክፈት እንደሚያስፈልግ ዛሬ ተናግረዋል።

ዋሽንግተን፤ ሲአይኤ የሳዑዲው ልዑል ለኻሾጂ ግድያ ትዕዛዝ እንደሰጡ ያምናል ተባለ

የአሜሪካው የስለላ መስሪያ ቤት ሲ. አይ. ኤ ጋዜጠኛ ጀማል ኻሾጂ እንዲገደል የሳዑዲ አረቢያው አልጋ ወራሽ ልዑል ሞሐመድ ቢን ሰልማን ትዕዛዝ መስጠታቸውን እንደሚያምን የዜና ምንጮች ገለጹ። ሲ. አይ. ኤ ከዚህ ድምዳሜ የደረሰው በርካታ ምንጮችን አጣርቶ ነው ተብሏል። ከነዚህ መካከል በኻሾጂ እና የሳዑዲ አረቢያው አልጋ ወራሽ ወንድም ካሊድ ሰልማን መካከል የተደረገ የስልክ ጥሪ ይገኝበታል። ሲ. አይ. ኤ ይህን ድምዳሜውን ለአሜሪካ ኮንግረስ እና ለሌሎች የመንግስት አካላትም አሳውቋል ተብሏል።በመጀመሪያ በዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ አማካኝነት ይፋ የተደረገው ይህ የሲ. አይ. ኤ ግምገማ በሳዑዲ አዛዥ ናዛዥ ናቸው የሚባሉትን አልጋ ወራሽ ከግድያው ጋር ያቆራኘ የአሜሪካ ወሳኝ ግምገማ ተብሎለታል። ጉዳዩን በተመለከተ በጉብኝት ላይ ባሉበት ፓፓዎ ኒው ጊኒ የተጠየቁት የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ማይክ ፔንስ በምስጢራዊ መረጃ ላይ አስተያየት መስጠት እንደማይችሉ ተናግረዋል። የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤትም አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል። በዋሽንግተን የሚገኘው የሳዑዲ አረቢያ ኤምባሲ በበኩሉ በሲ. አይ. ኤ ግምገማ ተጠቀሰ የተባለውን የሞሐመድ ቢን ሰልማንን ተሳትፎ “ሀሰት” ሲል አጣጥሏል። የኤምባሲው ቃል አቃባይ ባወጡት መግለጫ “የዚህን ግምት የመጀመሪያ መነሻ ሳንመለከት የተለያዩ ንድፈ ሀሳቦችን እየሰማን እንገኛለን” ብለዋል። የሳዑዲ አቃቤ ህግ ኻሾጂን በመግደል በተከሰሱ አምስት ተጠርጣሪዎች ላይ የሞት ቅጣት ብይን እንደሚጠይቅ ባለፈው ሐሙስ ማስታወቁ አይዘነጋም። TW/LA