ያንዱ ተሥፋ የሌላው ሥጋት-ጊቤ ሶስት | ኤኮኖሚ | DW | 21.12.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

ያንዱ ተሥፋ የሌላው ሥጋት-ጊቤ ሶስት

የአካባቢ ተቆርቋሪዎች የቱርካና ኃይቅ ሥጋት ነው ሲሉ የሚተቹት፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በአንፃሩ የአገሪቱን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ለማሟላት ከፍ ያለ ጠቀሜታ አለው ብሎ ተስፋ የጣለበት የጊቤ ሶስት የኃይል ማመንጫ ከተመረቀ ቀናት ተቆጠሩ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:16
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
08:16 ደቂቃ

የጊቤ ሶስት የኃይል ማመንጫ

ከደጋማው ማዕከላዊ ኢትዮጵያ የሚንደረደረው የኦሞ ወንዝ በኬንያው የቱርካና ኃይቅ ከመድረሱ በፊት በደረቃማው ደቡብ ምዕራብ የአገሪቱ ክፍል ይጥመዘመዛል።እስከ ከቱርካና ኃይቅ 760 ኪ.ሜ የሚፈሰው ኦሞ ከኦሮሚያ ክልል ከሸዋ ተራሮች ይነሳል። ጊቤ፤ ዋቢ፣ዴንጫያ፣ጎጀብ፣ሙኢ፣እና ኡስኖ የኦሞ ገባር ወንዞች ናቸው። ድንበር ከመሻገሩ በፊትም ሆነ በኋላ በመቶሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ኅልውና መሰረት የሆነው የኦሞ ወንዝ የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ሊያሟሉ ይችላሉ የሚል ተሥፋ ከተጣለባቸው መካከል አንዱ ነው።
ባለፈዉ ቅዳሜ በይፋ የተመረቀዉ የኃይል ማመንጫ 1,870 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም አለው ተብሏል። በጣልያኑ የሳሊኒ ኢምፕሬጊሎ ኩባንያ የተገነባው ኃይል ማመንጫ የአገሪቱን የኃይል ምርት በሁለት እጥፍ ያሳድጋል ተብሎለታል። 

ከ46 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማያገኙባት ኢትዮጵያ የጊቤ ሶስት ግድብ መጠናቀቅ የምሥራች ዜና ሳይሆን አይቀርም። ለዘመናት ከግብርና ጥገኝነት ፈቅ ማለት ለተሳነው የኢትዮጵያ ኤኮኖሚም አዎንታዊ ዜና ይመስላል። ለዓመታት ሲዳክር የቆየውን የማምረቻ ዘርፍ ለማዘመን አዲስ ውጥን ይዞ ብቅ ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት እና አቅርቦት አለመጣጣም ሁነኛ ፈተናው ሆኖ ቆይቷል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የሥራ አመራር ፅ/ቤት ኃላፊ። አቶ ጌታሁን ነጋሽ « እስካሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ትላልቅ የኤሌክትሪክ ማመንጫዎች እየተገነቡ ቢሆንም እንኳን ፍላጎት እና አቅርቦቱ የተመጣጠነ ነበር ማለት አይቻልም። በተለይም ደግሞ እየተገነቡ ያሉት ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ከሚፈልጉት ከፍተኛ ኃይል አንፃር ለኢንቨስትመንቱ እንደ አንድ ተዳሮት ሆኖ የሚታየው ኃይል አቅርቦት ችግር ነበር።» ሲሉ ያስረዳሉ። 

 መስሪያ ቤታቸው የአገሪቱን የማምረቻ ዘርፍ ለማበረታታት አስፈላጊ መሰረተ-ልማቶች የተሟሉላቸው የኢንዱስትሪ ዞኖች ማዘጋጀት ሁነኛው መፍትሔ ነው ብሎ ያምናል። አቶ ጌታሁን ከፍተኛ የኃይል ፍላጎት የሚኖራቸው ወደ አስር የሚሆኑ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በአገሪቱ በመገንባት ላይ መሆናቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። አዳማ፤መቀሌ ድሬ ዳዋ እና አረርቲን በመሳሰሉ አካባቢዎች አዳዲስ የማምረቻ ማዕከላት ለመገንባት የኢትዮጵያ መንግሥት ዝግጅት ላይ መሆኑን ተናግረዋል። አቶ ጌታሁን ባለፈው ዓመት 800 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የጀመረው የጊቤ ሶስት ኃይል ማመንጫ የአገሪቱ የማምረቻ ዘርፍ የገጠመውን አጣብቂኝ ሊፈታ ይችላል የሚል ተስፋ አላቸው።  
በ1.5 ቢሊዮን ዩሮ (1.57 ቢሊዮን ዶላር) በኦሞ ወንዝ ላይ የተገነባው የኃይል ማመንጫ የኢትዮጵያን የማምረቻ ዘርፍ እና ለጎረቤት አገራት የምትሸጠውን የኤሌክትሪክ ኃይል ያሳድጋል ተብሎ ተስፋ እንደተጣለበት የመንግሥት ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ ተናግረዋል። በገንዘብ እጥረት የተጓተተውን የኃይል ማመንጫ ግንባታ የቻይናው ኢምፖርት ኤክስፖርት ባንክ 60 በመቶ ወጪ በብድር መሸፈኑን ሬውተርስ ዘግቧል። ግንባታው በጎርጎሮሳዊው 2006 ዓ.ም. የተጀመረ ሲሆን የግንባታው ሒደት ለአስር አመታት ጥቂት ወራት ሲቀረው ተጠናቋል። 

የአካባቢ ተቆርቋሪዎች የጊቤ ሶስት የኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ እና በታችኛው ኦሞ አካባቢ ኢትዮጵያ የጀመረችው የመስኖ ልማት ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎችን የምግብ ዋሥትና አደጋ ላይ ይጥላል ሲሉ ይወቅሳሉ። ዓለም አቀፍ ወንዞች የተሰኘው ተቋም ኢትዮጵያ የግልገል ጊቤ ሶስትን ስትገነባ የራሷን የአካባቢ ጥበቃ አዋጆች እና ሕገ-መንግሥቷን ጥሳለች ብሎ እስከ መወንጀል ደርሷል። የዓለም አቀፍ ወንዞች የአፍሪቃ ቢሮ ኃላፊ ሩዶ ሳንያንጋ የግድቡ ግንባታ በቱርካና ኃይቅ የውሐ መጠን ላይ የከፋ ተፅዕኖ ያሳድራል ብለው ይተቻሉ።


«የጊቤ ኃይል ማመንጫ የተገነባበት የኦሞ ወንዝ ለቱርካና ኃይቅ የውሐ ፍሰት እስከ 85 በመቶ ድርሻ አለው። በአሁኑ ወቅት የቱርካና ኃይቅ የዓለማችን ትልቁ የበረሐ ኃይቅ ነው። ከሶስት መቶ ሺህ በላይ የአካባቢው ነዋሪዎች የዕለት ተለት ኑሮ በዚሁ ኃይቅ ላይ የተመሰረተ ሲሆን አብዛኞቹ የሰሜናዊ ኬንያ አርብቶ አደሮች ናቸው። ከቱርካና ኃይቅ የላይኛው ተፋሰስ አካባቢ በኦሞ ሸለቆ በርካታ ነዋሪዎች ኑሯቸው የተመሰረተው በወንዙ ፍሰት ላይ ነው። እናም ወደ ቱርካና ኃይቅ ያለውን ፍሰት መገደብ እና መቆጣጠር በአሳ አስጋሪዎቹ ላይ አደገኛ ተፅዕኖ ይኖረዋል። ከዚህ በተጨማሪ  አብዛኛው ውሐ በኢትዮጵያ በኩል ለመስኖ ይውላል። ለመስኖ ይውላል ተብሎ የሚገመተው የውሐ መጠን ወደ ታች የሚፈሰውን በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል። ይኸ ደግሞ ኃይቁን በመጠን እንዲቀንስ ያደርገዋል።» 

የጊቤ ሶስት የኃይል ማመንጫ ግንባታን ሲቃወሙ የከረሙት ሩዶ ሳንያንጋ እና ዓለም አቀፍ ወንዞች የተሰኘው ተቋም ብቻ አይደሉም። ኦክ ላንድ ኢንስቲቲዩት 243 ሜትር ወይም ወደ 800 ጫማ አካባቢ እርዝማኔ ያለው ግድብ በኦሞ ወንዝ የታችኛው ተፋሰስ ላይ ተገን አድርገው ህይወታቸውን በሚመሩ ዜጎች ላይ የከፋ ተፅዕኖ ያሳድራል ሲል በተደጋጋሚ ወቅሷል። የግድቡን ግንባታ የሚቃወሙት መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና የአካባቢ ተቆርቋሪዎች ጉዳዩን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስ እና የባህል ድርጅት የዓለም ቅርሥ ኮሜቴ ድረስ አቤት ብለው ነበር። ሙግታቸው በዓለም ቅርሥነት የተመዘገቡት የአካባቢው ባሕሎች እና ተፈጥሯዊ መሥሕቦች ኅልውና አደጋ ላይ ወድቋል የሚል ነበር። 

«ሙግታችን እነዚህ ባሕላዊ እና ተፈጥሯዊ መሥሕቦች አደጋ ከተጋረጠባቸው ጎራ ሊመዘገቡ ይገባል የሚል ነበር። ይኽ አልተሳካም። ተደጋጋሚ የውሳኔ ኃሳቦች ቢተላለፉም የኢትዮጵያ መንግሥት በቅርሥ ኮሚቴው የየተጠየቀውን የአካባቢ ተፅዕኖ ፍተሻ አልካሔደም። የውሳኔ ኃሳቦቹን ችላ በማለት ግንባታው እንዲቀጥል ተደርጓል።»

የጊቤ ኃይል ማመንጫ ባስነሳው ውዝግብ ከትችቱ ጎራ የተሰለፉ ዓለም አቀፍ ተቋማትን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ «የአፍሪቃን ልማት ለመዝጋት የተሰለፉ ኃይሎች» ሲሉ ይወርፏቸው ነበር። አቶ መለስ «አፍሪቃን የኋላ ቀርነት ሙዚየም» የማድረግ እቅድ ያላቸው እያሉ ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል እና ኦክላንድ ኢንስቲቲዩትን የመሰሉ ተቋማትን ይተቹም ነበር። በግልገል ጊቤ ሶስት የኃይል ማመንጫ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምም የአካባቢ ተቆርቋሪዎቹን በመወረፍ የመለስን ኃሳብ አስተጋብተዋል።  «የጊቤ ሶስት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ የአካባቢ ተቆርቋሪ ነን ባዮች ሲሉት ከነበረው በተቃራኒው ለአካባቢውም ሆነ በግቡ ዙሪያ ለሚገኙ ሕዝቦች በርካታ ጥቅሞችን በማስገኘት ላይ ይገኛል።» ያሉት ጠቅላይ ሚኒሥትሩ ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት በገጠማት ድርቅ ወደ ኃይል ማመንጫ ግድቦች በቂ ውሐ ባለመግባቱ ምክንያት ሊከሰት የነበረውን የነበረውን የኃይል እጥረት መፍታቱን አስታውሰዋል። 
ሩዶ ሳንያንጋ የግድቡ ግንባታ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ አሁንም ያሳስባቸዋል። የኢትዮጵያ እና የኬንያ መንግሥታት የግድቡን ተጽዕኖ በጋራ ሊፈትሹ ይገባል ሲሉም ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ተጨማሪ ሁለት የጊቤ ኃይል ማመንጫዎች የመገንባት እቅድ እንዳለው አስታውቋል። ኢትዮጵያ ወደ ኬንያ፤ ሱዳን እና ጅቡቲ የኤሌክትሪክ ኃይል የምትልክ ሲሆን፤ ከታንዛኒያ፣ርዋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን እና የመን ጋር ደግሞ ውል ገብታለች። 


እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ 

Audios and videos on the topic