ያልታበሰው የተፈናቃዮች እንባ | ኢትዮጵያ | DW | 14.11.2022
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

ያልታበሰው የተፈናቃዮች እንባ

ከኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ዞን ተፈናቅላ በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም የተጠለለች እናት እርዳታ በማጣቷ ለልመና ተዳርጋለች። የአካባቢው ባለሥልጣናት እንደሚሉት ግን እርዳታ ያጣችው ይኸች እናት ብቻ አይደለችም። ከሰባት ሺሕ በላይ የሚሆኑ ተፈናቃዮች እርዳታ እንደማይሰጣቸው በምዕራብ ጎጃም ዞን የሰከላ ተፈናቃዮች አስተባባሪ ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል።

የምዕራብ ጎጃም ዞን የሰካላ ተፈናቃዮች

ወርቃለም መላኩ ከ38 ዓመታት በፊት በሰፈራ ፕሮግራም ከቀድሞው ወሎ ክፍለ ሀገር ወደ ኦሮሚያ ክልል ሁሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን ጃርዴጋ ወደ ተባለ አካባቢ ከሰፈሩ ወላጆቿ የዛሬ 20 ዓመት ተወለደች። በአካባቢው፣ ቋንቋ፣ ባህልና ልምድ ታንፃ ነው ያደገችው። የወላጆቿን የትውልድ ቦታ በስም ካልሆነ በስተቀር በአካል አቅጣጫውን እንኳ አታውቀውም፡፡ 
በኦሮምያ ክልል ጅሬ ጉዳ ወደ ተባለ አካባቢ አንድ የጎጃም ተወላጅ አግብታ ትዳርን ሀ ብላ መጀመሯን ትናገራለች። በ2010 ዓ ም በአካባቢው በነበረው አለመረጋጋት ወደ ጎጃም ሰከላ ወረዳ መፈናቀሏንና ተመልሳ ወደ አደገችበት ቀየ መሄድ እንዳልቻለችም ገልፃልናለች፡፡ 

“ጊዳ ወረዳ ነው ጅሩ ጉዳ ትባል ነበር የምኖርበት አካባቢ፣ … ከዚያ ነው ተፈናቅለን የመጣነው፣ ከጎጃም የሄደ ልጅ ነበር እሱን አግብቼ ስኖር፣ ያኔ ደግሞ ጉልበቴ ደካማ ነበር (ነብሰ ጡር ነበርኩ) ተፈናቅለን ስንመጣ ወደ ቤተሰቦቼ እንዳልሄድ ዝግ ነው፡፡ ” 

በመፈናቀል ላይ በነበረችበት ጊዜ እርጉዝ እንደነበረች የምትናገረው ወርቃለም ጎጃም ከደረስን በኋላ ኑሮ ሲከብደን ባሌ ጥሎኝ ጠፋ ትላለች፣ የተረገዘው ልጅም ምንም በሌለበት ሁኔታ እንደተወለደ የምታስረዳው ተፈናቃዩዋ፣ ለነብሴ ያሉ ሰዎች አርሰውኛልም ብላለች፡፡ 

በጎጃም የሚገኙ ተፈናቃዮች

በጎጃም የሚገኙ ተፈናቃዮች

“እንደዚያ ሆኘ (ነብሰ ጡር ሆኜ) እሱን ተከትየ መጥቼ ስንኖር አገሬ አልሄድ አገሬን አላውቀው፣ ተወልጄ ያደግሁት ወለጋ ነው፣ ባሌ ገንዘብ እልቅ ስትልበት ሳያማክረኝ ጥሎኝ እልም አለ፣ የማውቃቸው ሰዎች ነበሩ እነሱን መጠጊያ የለኝ አገሬ አልሄድ አላውቀው፣ ዘመድ የለኝ ብየ ሳማክራቸው ቢርብሽም ቢጠማሽም ከእኛ ጋር ተጠጊና ሰው እስክትሆኝ ድረስ ( ወልዳ ነበር) ወይ መንገዱ ይከፈታል ከቤተሰቦችሽ ጋር ትቀላቄለሽ ብለውን መታሁኝ የማላውቃቸው ሰዎች እኛ ነን የምናርሳት ብለው ለነብሴ ብለው አረሱኝ፡፡ ” 

እንደሌሎች ተፈናቃዮች ላለፉት በርካታ ወራት እርዳታ እየተሰጣት ብትቆይም የሰከላ ወረዳ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና አስተባባሪ ኮሚቴ ወደ ወላጆችሽ የትውልድ ቦታ መሄድ አለብሽ በሚል እርዳታው መቋረጡን ለዶይቼ ቬሌ በስልክ የገለፀችው ወርቃለም አሁን ለልመና መንገድ ላይ መውጣቷን በሀዘን ስሜት አብራርታለች፡፡ 

“ስረዳ ነው የቆየሁኝ፣ … እየራበኝ ነው ስጡኝ ጨቅላ ልጅ ይዤ መጠጊያም የለኝ እየለመንኩ ነው የምበላ ብየ ወረዳው ጽ/ቤት (ሰከላ ወረዳ) ገብቼ አሪ ብየ ሳማክራቸው የሰከላን ተወላጆች እንጂ የምናስተናግድ ከዚያ ውጪ አናስተናግድም… አማራጭሽን መያዝ ትችለሽ እንጂ አንሰጥሽም አሉኝ፣ ብመላለስ የሚረዳኝ አታሁ፣ አሁን ሰከላ ውስጥ አንድ በአንድ ያውቁኛል እየለመንኩ ነው የምበላ፣ አገሬ አልሄድ መጠጊያ የለኝ፡፡” 

በጎጃም የሚገኙ ተፈናቃይ እናት

በጎጃም የሚገኙ ተፈናቃይ እናት

የምዕራብ ጎጃም ዞን የሰካላ ተፈናቃዮች አስተባባሪ አቶ የሮም ዳኛው ችግሩ በስፋት እንደሚታይ አመልክተው የአካባቢው ተወላጆች አይደላችሁም በሚል ሰበብ በወረዳው ከሚገኙ 26ሺህ ተፈናቃዮች 7 ሺህ የሚሆነው እርዳታው ተቋርጦበታል ብለዋል፡፡ “19ሺህ ብቻ ነው የሚረዳ እንጂ ወደ 7ሺህ 484 አይረዳም እንዲያውም የማይረዳው ሊጨምር ይችላል” ብለዋል፡፡ 

በምዕራብ ጎጃም ዞን የሰከላ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊና የወረዳው አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚቴ አስተባባሪ አባል አቶ ግራማ አጥናፉ፣ የሚመጣው እርዳታ ውስን በመሆኑ ከአካባቢው ተወላጆች በስተቀር ለሌሎች እርዳታው መቋረጡን አስረድተዋል፡፡ 

“አንዷ ከወለጋ ህፃን ልጅ ያዘለች ከእኔ ቢሮ መጥታ ነበር፣ አንዷ ደግሞ ደቡብ ጎንደር ዞን ተወላጅ ነኝ ባል አግብቼ ነበር አሁን ባሌ ፈትቶኝ የሚል ነገር አንስታለች፣ ወደ ዞንም የእኛን ወረዳ ኃላፊዎች ጭምር አግኝቼ ለማነጋገር ሞክሬያለሁ ይህንን አንችልም በሚል ደምድመናል፣ እኔም አልችልም ከአቅሜ በላይ ነው ብየ ነው የመለስኳቸው፡፡” 

የምዕራብ ጎጃም ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኃላፊ አቶ ተዋቸው ዓለማየሁ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ በተደረገ ማጣራት መሬት ያላቸው፣ በንግድ የተሰማሩና የተሸለ ኑሮ የሚኖሩ ተፈናቃዮች ተገኝተዋል ብለዋል፡፡ በመሆኑም እነኚህ አካላት ከተፈናቃይነት ባይሰረዙም እርዳታ ግን አያገኙም ነው ያሉት፣ ሆኖም በስራ ላይ የተከሰቱ ስህተቶች ካሉ እንደሚታረሙ ቃል ገብተዋል፡፡ 

በምዕራብ ጎጃም ከኦሮምያና ከቤኒሻንጉል ክልሎች 182 ሺህ ተፈናቃዮች በ14 ወረዳዎች በመጠለያ ጣቢያዎችን ከህብረተሰቡ ጋር ተቀላቅለው ይገኛሉ፡፡ 

ዓለምነው መኮንን 

እሸቴ በቀለ

ታምራት ዲንሳ
 

Audios and videos on the topic